ምክር ቤቱ በአመፀኞች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰበ

0
712

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት ሰላምን በማወክ ሕይወት እስከመንጠቅ በደረሱት አመፀኞች ላይ የክልሉ ጸጥታ ኃይል ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰበ። የክልሉ ፀጥታ ኃይል ሕዝቡን ከጥቃት እንዲከላከል የጠየቀ ሲሆን ከፌደራል ፀጥታ አካላት ጋር እንዲተባበርም አስገንዝቧል።
ምክር ቤቱ ጥር 7/2011 ባወጣው መግለጫ በክልሉ ሰላምና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እየተሰራ ቢሆንም በየጊዜው እየባሰ የመጣው የማንአለብኝነት መንፈስ የክልሉን ሕዝብ ደኅንነት ለአደጋ ማጋለጡን አመልክቷል።
በቅርቡ በምዕራብና በማዕከላዊ ጐንደር ደግሞ ከሥጋት አልፎም የንጹኀንን ሕይወት የቀጠፈ ድርጊት መስተዋሉን ያስታወሰው መግለጫው፤ ‹‹በቅማንት ስም የተደራጀው የጥፋት ኃይል እና በአማራ ስም እየማሉ እየተገዘቱ አማራን ለጥቃት የሚያጋልጡ የታጠቁ ኃይሎች የሚፈጽሙት ድርጊት ነው›› ሲል ኮንኖታል።
የጥፋት እንቅስቃሴን ማስታመም በምንም ምክንያት ተቀባይነት የለውም ያለ ሲሆን አጥፊዎች ለሕግ እንደሚቀርቡም አረጋግጧል።
በክልሉ ውስጥ በርካታ ትጥቅ ያላቸው ወገኖች መኖራቸውን ያስታወሰው መግለጫው፤ ትጥቁ ሕዝቡን ለማሸበር መዋል እንደሌለበትም አስጠንቅቋል።
‹‹ለአማራ ሕዝብ መብትና ጥቅም መከበር እንታገላለን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ትንንሽ ችግሮችን በየአካባቢው አግዝፎ በማንሳት የክልላችን ሕዝብ በመሰረታዊ አጀንዳዎቹ ላይ እንዳያተኩር ከማድረግ ተቆጥባችሁ ህዝባችንን ከጥቃት ለመከላከል በጋራ እንድትሰለፉ›› ሲልም ጥሪ አቅርቧል።

ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here