የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉሕዴፓ) ሰሞኑን ባካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ግምገማ 55 አመራሮችን ከአመራርነት አባሯል።
11 አመራሮችም በክብር መሰናበታቸው ታውቋል።
ፓርቲው የደረሰበትን የግምገማ ውጤት መሰረት በማድረግ እርምጃውን የወሰደ ሲሆን፤ በክብር የተሰናበቱትና ከአመራርነት የተባረሩት አባላት በሚመጥናቸው ቦታ የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኛ ሆነው እንዲመደቡ ውሳኔ ተላልፏል ተብሏል።
በተሰናበቱና ከአመራርነት በተነሱ አባላቱ ምትክ የወጣቶችና ሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማረጋገጥ ያስችላል ያለውን አዳዲስ ምደባ ስለመስጠቱም ለመገናኛ ብዙኀን በላከው መግለጫ አመልክቷል።
ፓርቲው የሚያስተዳድረው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከአዋሳኝ የኦሮሚያና አማራ ክልል አካባቢዎች ጋር ተደጋጋሚ ግጭቶች ያጋጠሙት ሲሆን በቅርቡም ለግምገማ በተቀመጠበት ወቅት ሰላምን እያሳጡ ባሉ አመራሮችና ተባባሪ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ እወስዳለሁ፤ ለሕግ አሳልፌም እሰጣለሁ ሲል መዛቱ ይታወሳል።
ክልሉ ሰላም እንዲያጣ እንቅፋት የሆኑና ለመሆን እየጣሩ ያሉ ወገኖችን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡለት ያስጠነቀቀው ፓርቲው፤ የፀጥታ ኃይሉ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ሰላምን የማረጋገጥ ሥራውን በወጉ እንዲወጣም አሳስቧል።
ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011