በድሬዳዋ ትናንት ባገረሸው ግጭት ነዋሪዎች ስጋት ውስጥ ገብተዋል

0
381

በድሬዳዋ ትናንት አርብ፣ ጥር 17 ረፋድ ላይ ባገረሸውና ፖለቲካዊ መልክ በያዘው ግጭት በከተማዋ ሰላማዊ እንቅስቀሰሴዎች ከመገደባቸው ባሻገር ነዋሪዎቹ በስጋት ከቤት መውጣት እንዳልቻሉ ተገለጸ። አንድ ሕጻን ሲገደል አራት ሰዎች ተጎድተዋ ተብሏል።
አዲስ ማለዳ በከተማዋ ከሚኖሩ ምንጮቿ እንደተረዳችው ሰኞ፣ ጥር 13 የነበረው ግጭትና አለመረጋጋት መልኩን ቀይሮ ፖለቲካዊ ቀውስ ወደ መሆን ተሻግሯል።
ጥር 13 የእግዚአብሔር አብ ታቦትን አስገብተው በሚመለሱ የእምነቱ ተከታዮች ላይ ድንጋይ መወርወሩን ተከትሎ ግጭትና ኹከት ተፈጥሮ እንደነበር የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት አሳውቋል። ችግሩ ቀበሌ 09 በሚባለው አካባቢ የተፈጠረ እንደነበርም ተሰምቷል።
በወቅቱም ፖሊስ ተጠያቂ ናቸው በሚል የጠረጠራቸውን 84 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ ማድረግ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ማክሰኞ፣ ጥር 14 ˝የታሰሩ ልጆች ይፈቱ˝ በሚል የከተማዋ ወጣቶች ተቃውሞ እንዳሰሙ ምንጮች ተናግረዋል። በዚህም መንገድ ተዘግቶና እንቅስቃሴዎች ተገተው እንደነበር አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ወጣቶች ገልጸዋል። በዕለቱ ሱቆች ተሰብረውና አንድ መድኃኒት ቤትም በከፊል ተቃጥሎ እንደነበር ታውቋል።
ቀድሞ የነበረው ጥያቄ መቀየሩን የገለጹት ምንጮቻችን የፖለቲካ ቀውስ ወደመፍጠር መሻገሩን አንስተዋል። ከጥያቄዎቹ መካከል ˝የከተማዋ አመራሮች የሕዝቡን ጥያቄ ስላልፈቱ ከኃላፊነታቸው ይነሱ፣ ብሔርን መሠረት አድርጎ ለአመራሮች የሚሰጠው ኮታ ተገቢ አይደለም፣ የሥራ አጡ ቁጥር ጨምሯል፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አሉብን፣ የልማት ሥራው አርኪ አይደለም፣ በድሬ ዳዋ የለውጥ መንፈስ አይስተዋልም˝ የሚሉት ይገኙበታል።
ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ ከከንቲባው ጋር መወያየት እንደሚፈልግ ገልጾ ሲጠይቅ ነበር ተብሏል። ሐሙስ ጥር 16 በከተማዋ ቀበሌ 05 በሚገኝ ሜዳ ከንቲባው ተገኝተው እንደሚያወያዩ ተነግሮ ሕዝቡ ሲጠብቅ ቢያረፍድም ከንቲባው የሚችሉት ከ300 እስከ 400 ተወካዮችን አዳራሽ ውስጥ ማነጋገር መሆኑ ሲሰማ ሕዝቡ ተቆጥቶ ለተቃውሞ ዳግም ወደ ጎዳናዎች መውጣቱን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። በተቃውሞውም ጎማ እየተቃጠለና መንገዶች ሙሉ በሙሉ ተዘግተው መዋላቸው ታውቋል።
ይሁንና የክልሉ ፖሊስና አድማ በታኝ አስለቃሽ ጭስን በመተኮስ ተቃውሞውን ለማርገብ እየሞከሩ ነው ሲሉ ምንጮቻችን አስረድተዋል። ምንጮች ‹‹የፀጥታ ኃይሉ በወሰደው እርምጃ አንድ ሕፃን ሲገደል፣ አራት ሰዎች መቁሰላቸውንም አስተውለናል›› ብለዋል።
የከተማዋ ከንቲባ ኢብራሒም ኡስማን ሐሙስ ምሽት ለመገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ አንድ ሕፃን በተባራሪ ጥይት ተመትቶ መሞቱን እና ዐሥር ሰዎች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው ታክመው መውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ ሕዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እያነሳ መሆኑን ጠቅሰውም፣ ችግሩን ለመፍታት መጀመሪያ ሰላም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የቀበሌ አስተዳደር ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ የንብረት ውድመትና ቃጠሎ እየተካሄደ እንደነበርም ተነግሯል፡፡
በመላው ድሬ ዳዋ ተቃውሞው መስፋፋቱና ሕዝቡም ስጋት ውስጥ መውደቁን አዲስ ማለዳ ከቅርብ ምንጮቿ ተረድታለች። በሒደቱ የመንግሥት ሥራ እየተስተጓጎለ ነው የተባለ ሲሆን አርብ ጠዋት ሠራተኛው ወደ ቢሮው ገብቶ የነበረ ቢሆንም ረፋድ 5 ሰዓት ግጭትና ተቃውሞው ዳግም በማገርሸቱ ወደ የቤታቸው መበተናቸውን ለማወቅ ተችሏል። ዘገባው እስከተጠናቀረበት ትናንት አመሻሽም ነዋሪው ከቤት ለመውጣት እንዳልቻለና የተኩስ ድምጾች እንደሚሰሙ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸውልናል። ከክልሉ ፖሊስ በተጨማሪ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ስለመመልከታቸውም ነዋሪዎች ጠቁመዋል። መንግሥት ሰላም የማስከበር ሥራውን እንዲወጣ የጠየቁ ነዋሪዎች ሕዝቡም ጥያቄውን በሰላም እንዲያቀርብና አስተዳዳሩ ምልሽ እንዲሰጥ ሲሉ ጠይቀዋል።
አዲስ ማለዳ ወደአስተዳደሩ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽ ጉዳዮች ቢሮ ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪን ብታደርግም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።
የኮሙዩኒኬሽ ቢሮ ኃላፊው እስቅያስ ታፈሰ በረብሻዎች በሚሳተፍ በማንኛውም ሰው ላይ የፀጥታ ኃይሉ የሕግ የበላይነት የማስከበር ሥራውን እንዲወጣ አቅጣጫ መቀመጡንና ከተጠርጣሪዎች ጋር በተያያዘ ፖሊስ የማጣራት ሥራውን እንደጨረሰ ይፋ ይደረጋል ማለታቸውን ቢሮው ጥር 14 ባወጣው መረጃ አመልክቷል።
ለአሁኑ ተቃውሞ መነሻ ሆኗል በተባለው የሰኞው ድንጋይ ውርወራ ላይ መግለጫን የሰጡት የከተማዋ የሃይማኖት አባቶች ፀብ የማጫር ተግባርን እንደሚያወግዙ በመግለጽ፤ ማንኛውም አማኝ የሃይማኖት አባቶችን መስማት እንዳለበት መምከራቸው ታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here