ዩኒቨርሲቲዎቻችን የሐሳብ ፍጭት ማዕከላት ይደረጉ!

0
423

ከስድስት ዐሥርት ዓመታት ያልዘለለው የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም በዕውቀት፣ ክኅሎትና በአመለካከት የተገነቡ ብቁ ዜጎችን የማፍራት ተልዕኮ አንግቦ መነሳቱን መናገር ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል። ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ አፍርተው ለአገር በሚያበረክቱት የተማረ የሰው ኃይል አይተኬ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ የመጣው በቡድን እየተከፋፈሉ ኃይል የተቀላቀለበት ግጭት ውስጥ መግባታቸው የፈሰሰባቸውን የሕዝብ ሀብት፥ ሕዝብን በማገልገል እንዳይመልሱ እንቅፋት እየሆነ ነው።

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከተማረ ሰው ኃይል አበርክቷቸው በተጨማሪ ለ‘ሲቪክ’ (ሥልጡን ግንኙነት) እና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መገንቢያና የብሔራዊ መግባባት ዋነኛ ማዕከል መሆን ይጠበቅባቸዋል። ዴሞክራሲ በተግባር የሚገለጥባቸው የትልቋ ኢትዮጵያ ማሳያ ተደርገው ሊታነፁም ይገባል።
የ1960ዎቹ የኢትዮጵያ አብዮት የተማሪዎች የነቃ ተሳትፎ ራሳቸውን ከማንቃት በዘለለ ትልልቅ ርዕይዎችን ሰንቀው፣ የመላውን ኅብረተሰብ መብቶች በመንደፍ (የ“መሬት ላራሹ” ጥያቄን ማንሳት ይቻልለ) ተግባራዊ እንዲሆንና ግንዛቤ እንዲያድግ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነበር።

ስለሆነም፣ ከፍተኛ የትምህርት ማዕከላት ከተራ መማሪያ፣ ማስተማሪያ መድረክነት ወይም ዕውቀት በሽምደዳ ወይም ከመምህራን አዕምሮ ወደ ተማሪዎች የሚቀዳበት ተቋምነት ባሻገር ከግለሰባዊ እስከ ማኅበረሰባዊ ችግር ፈቺነት እና የንቃተ ሕሊና ማሳደጊያ ማዕከላት መሆን አለባቸው። የሐሳብ ፍሰት፣ ውይይት፣ ክርክሮችና የሐሳብ ፍጭት የሚካሔድባቸው መድረኮች መሆን ይገባቸዋል። የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች፣ የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክቶች፣ አይነኬ የሚመስሉ የማንነትና ቋንቋን መሠረት ያደረጉ ክርክሮችም ይሁኑ የትኞቹም ሐሳቦች የሚደፈሩባቸው፣ ተማሪዎች ያለ ፍርሐትና መሳቀቅ በሠለጠነ አግባብ የሚወያዩባቸው፣ ሐሳብ የሚለዋወጡባቸው፣ ዕውቀት የሚገበዩባቸው፣ አዳዲስ ኅልዮቶችን የሚያገኙባቸው እና የሚያስተዋውቁባቸው መሆን ይገባቸዋል። በዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ ሐሳብ ብቻ እንዲያሸንፍ በሐሳብ ብቻ የሚፋጩ፣ ነገር ግን በአካል እና በኃይል የማይጋጩ ዜጎች ሆነው የሚታነፁበት ተቋማት መሆን ይገባቸዋል። ተቋማቱ የዕውቀት መቅሰሚያና አዕምሮ መቅረጫ ብቻ ሳይሆኑ ሙሉ ስብዕና መገንቢያ፣ ዓለምን የመመልከቻ መነፅር ማስተካከያ መሆን ይገባቸዋል።

በተግባር የሚታየው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ተቋማቱ በሙሉ አቅም የተማሪዎች የሐሳብ ልዕልና የሚስተናገድባቸው እንዳይሆኑ በየጊዜው እየመጡ የሚሔዱ መንግሥታት የቁጥጥር ረጃጅም እጆቻቸው ተፅዕኖ ከማሳረፋቸውም ባሻገር፣ ርዕዮተ ዓለማቸውን ማጥመቂያ እና አባላቶቻቸውን መመልመያ በማድረግ ‘አካዳሚያዊ’ ነጻነታቸውን ይነፍጓቸው ነበር። ከዚህም በከፋ የስለላ ሠራተኞችን በተማሪዎቹ መሐል በማሠማራት ነጻ ውይይት እንዳያደርጉ እንቅፋት ሲሆኑባቸው ከርመዋል።
የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች ከመደበኛ የክፍል ትምህርት ባሻገር ልዩነትን መቀበል እና ብዝኃነት ማስተናገድ መማር አለባቸው። የሐሳብ ልዩነትን ተቀብሎ አብሮ መኖር መለማመድ መቻል አለባቸው። የአገሪቱ ዩንቨርስቲዎች ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ተማሪዎች የሚመደቡባቸውም ይህንኑ ግብ ለማሳከት ነው። ይሁን እንጂ ይህ አሰባጥሮ በማስተማር እና ቀይጦ በማኖር ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ አቻችሎ የመኖር ባሕል የመገንባቱ ሒደት በጥቂት ዓመታት የዩንቨርስቲ ቆይታዎች ብቻ አይሳካም። ከከፍተኛ ተቋማት ውጪ ባሉ ማኅበራዊ ተቋማት እና ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ድረስ ቢያንስ በትርክት ደረጃ ማስተማር ይገባል።

ከተማሪዎቹ በተጨማሪም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሪዎች በፖለቲካ ታማኝነት እና የትውልድ ቦታ መሥፈርት ብቻ የሚመረጡበት ያልተጻፈ ሕግ ዩንቨርስቲዎቹ ብቃት ባላቸው ሰዎች እንዳይመሩ እና ለግጭቶቹም ሁነኛ መፍትሔ እንዳይበጅላቸው መንሥኤ ሆኗል እና መስተካከል አለበት ብላ አዲስ ማለደ ታምናለች።
በርግጥ የፖለቲካ ለውጥ መከሰቱን ተከትሎ ገዢው ግንባር ያለከልካይ ለፖለቲካ ዓላማ በማዋል ይፈነጭባቸው የነበሩትን ከፍተኛ ተቋማት በያዝነው የትምህርት ዘመን መጀመሪያ ላይ በግልጽ ቋንቋ ለማንኛውም አካል የፖለቲካ መጠቀሚያ መድረክ መሆን እንደሌለባቸው መንግሥት አስታውቋል፤ ይሁንና ለተግባራዊነቱ መሬት የወረደ ሥራ መሥራት ይገባል። አዲስ ማለዳ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፖለቲካ መድረክ በመሆን ማገልገል እንደሌለባቸው እና ‘አካዳሚያዊ’ ነጻነታቸውም መከበር እንዳለበት ታምናለች።

ዩንቨርስቲዎች በቀለሙ መስክ ተማሪዎችን ከማስመረቅ ባሻገር፥ በሐሳቦች ላይ የንግግር፣ የውይይት፣ የክርክር ባሕሎች እንዲስፋፉ በሁሉም ደረጃ ያሉ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን ሊያንፁበት የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው። አዲስ ማለዳ እነዚህ ባሕሎች በተማሪዎች ብቻ ሳይወሰኑ በአጠቃላይ በማኅበረሰቡ ዘንድ ባሕል እንዲሆን የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት ሰጥተው መሥራት ከቀዳሚ ኃላፊነታቸው ይመደባል ብላ ታምናለች። አሁን በአገራችን በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ‘ሲቪክ’ ማኅበራት ጠንክረው የውይይት፣ ክርክር እና የመቻቻል ባሕል ሥር እንዲሰድ መሥራት አለባቸው፤ ይህ ሥራቸውም ዩንቨርስቲዎችንም ሊያዳርስ ይገባል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በመጨረሻም አዲስ ማለዳ በአጠቃላይ ትውልዱ ላይ በተለይ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በምክንያትና በዕውቀት የሚያምኑ፣ ስሜታዊነት ያልተጫናቸው፣ ከምንም በላይ በራሳቸው የሚተማመኑ እንዲሆኑ የሁሉንም አካለት የተቀናጀ ሥራ እንደሚያስፈልግ በማመን ትኩረት እንዲሰጠው ጥሪ ታቀርባለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here