የቀድሞው የሱማሌ ልዩ ኃይል አዛዥ እየተፈለጉ ነው

0
505

በሶማሌ ክልል ከሐምሌ 28 -30/ 2010 በተከሰተው ሕገ መንግሥትን ማፍረስ ተግባር ላይ እጃቸው አለበት የተባሉት የቀድሞው የሱማሌ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ጀነራል አብድረህማን አብዱላሂ በሕግ እየተፈለጉ እንደሆነ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አርብ፣ ጥር 17 ከሰዓት በኋላ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው ጄኔራሉ በአሁኑ ሰዓት ከአገር እንደወጡ ገልፆ በየት አገር እንደሚገኙ መረጃው እንዳለው እና ተላልፈው ለሕግ እንዲቀርቡ የመንግሥት ለመንግሥት ድርድር እየተካሄደ እንደሆነ አሳውቋል።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ በመግለጫው እንዳስታወቀው በክልሉ በተጠቀሱት ጊዜያት ብሔርን መሠረት ያደረገ ግጭት እና የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች መከሰታቸውን ጠቅሶ በወንጀሉም የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እጅ እንዳለበት ገልጿል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በክልሉ ከሱማሌ ክልል ተወላጆች ውጭ በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ላይ የተነጣጠረ ጥቃት ተሰንዝሯል ሲል መግለጫው ያትታል። አቃቤ ሕግ ከክልሉ መንግሥት፣ ከፌደራል ፖሊስና ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ጋር በመሆን ለ5 ወራት ባካሄደው ምርመራ ከሐምሌ 28-30/ 2010 በተፈጠሩ ጥቃቶች 58 ሰዎች ለሞት ሲዳረጉ ከ266 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል። በዚህም ጋር ተያይዞ በ10 ሴቶች ላይ የመደፈር ጥቃት የተፈፀመባቸው ሲሆን የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት በወንጀሉ ተሳታፊ እንደነበሩ ተገልጿል።

ከንብረት ጋር በተያያዘ ከ412 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል። በተፈጠሩት ጥፋቶችና ግጭቶች እጃቸው አለበት በተባሉ 46 ግለሰቦች ላይ የእስር ማዘዣ የወጣባቸው ሲሆን ስድስት የሚሆኑት በእስር ላይ መሆናቸውን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዝናቡ ቱኑ ገልጸዋል። ስለቀሪዎቹ 40 ግለሰቦት ሲናገሩ ዝናቡ በሦስት ተከፍለው እንደሚታዩ ገልፀው አንዳንዶች ከአገር ወጥተዋል፣ በአገር ውስጥ የተደበቁ ተጠርጣሪዎች ያሉ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ያለመከሰስ መብት ስላላቸው ከክልሉ ምክር ቤት ጋር በመተባበር ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here