በአዲስ አበባ ከተማ በተሽከርካሪዎች ግጭት ምክንያት ከ 9.1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመንገድ ሀብት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለፀ

0
607

በተጠናቀቀው 2013 በጀት ዓመት ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በቀለበት መንገድ እና ከቀለበት መንገድ ውጭ ባሉት መንገዶች ላይ በተሽከርካሪዎች ግጭት ምክንያት ብቻ ከ 9.1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመንገድ ሀብት ላይ ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በበጀት ዓመቱ 12 ወራት ውስጥ 62 ግጭቶች በቀለበት መንገድ በሚገኙ ሀብቶች ላይ ሲደርስ 310 ግጭቶች ደግሞ ከቀለበት መንገድ ውጪ በድምሩ 372 የሚሆኑ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት መድረሱም ተገልጿል፡፡

ከፍተኛ የሀገር ሀብት ፈሶባቸው በተገነቡ የመንገድ አውታሮች ላይ በየጊዜው በተሸከርካሪዎች ግጭት እየደረሰ ያለው ጉዳት በአጠቃላይ የትራፊክ እንቅስቃሴው ላይ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ በተጨማሪ የሀገርን ኢኮኖሚ ለኪሳራ መዳረግ እንደሆነም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አሳስቧል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ በግጭት ጉዳት እየደረሰባቸው የሚገኙት የመንገድ ሀብቶች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተገዝተው በምሽት አገልግሎት እንዲሰጡ በተተከሉት የመንገድ ዳር መብራት ምሰሶዎች፣ የትራፊክ ምልክቶች፣ የአቅጣጫና ርቀት አመላካች ሰሌዳዎች፣ የእግረኛ መከላከያ አጥሮች፣ የመንገድ ማካፈያ ግንቦችና የውሃ መውረጃ ቱቦዎችና ክዳኖች ላይ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን መንገዶቹ ላይ የደረሰውን ጉዳት መልሶ በመጠገን ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ ስለሚኖርበት ተመጣጣኝ የሆነ የካሳ ክፍያ ጉዳት አድራሾቹ ሙሉ በሙሉ እንዲከፍሉ ማድረጉንም አስታውቋል፡፡

በከተማዋ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ በአግባቡ ለማሳለጥ እና የከተማዋን ገፅታ ለማሻሻል መንገዶች ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ የመንገድ ሀብቶችን ከጉዳት በመጠበቅና በመንከባከብ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበትም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መልዕክቱን አስተላልፋል፡፡

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here