የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ በ10 በመቶ ቀነሰ

0
725

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ከባለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ10 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ ተገለፀ። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2011 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት አፈፃፀሙን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት እንዳስታወቀዉ በተያዘው በጀት ዓመት የወጪ ንግድ መቀዛቀዙን ጠቁሟል። ምንጮች እንደሚያመለክቱት ባለፈው በጀት ዓመት ከነበረው 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በዚህ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ላይ 10 በመቶ ቀንሶ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት እንደተቻለ ለማወቅ ተችሏል። ይህም ለማግኘት ታቅዶ ከነበረው 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር 62 በመቶ የሚሆነውን ለማሳካት እንደተቻለ ተገልጿል።

በዋናነት ለወጪ ንግድ የሚቀርቡት ምርቶች ከግብርና ዘርፍ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን ከዚህም በመነሳት ቡና፣ ጫት እና የቅባት እህሎች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ያለውን ይይዛሉ። በዚህም መሠረት በተገባደደው ግማሽ ዓመት ከጫትና ከቡና በድምሩ 480 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰብ እንደተቻለ ታውቋል።

በዘርፉ ለታየው መቀዛቀዝ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ለወጪ ንግድ መቀነስ ምክንያት የሚሉትን እየነቀሱ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል። ለውጭ ገበያ የሚሆኑ ምርቶችን በሥፋት አለማቅረባችን የመጀመሪያው እንደ ችግር የሚጠቀስ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል። ምርቶቻችን በዓለም ዐቀፋ ደረጃ ተዋዳዳሪ ቢሆኑም በሥፋት ከማቅረብ አንፃር ችግሮች አሉብን ብለዋል።

ኮንትሮባንድን እንደ ሁለተኛ ምክንያት ያስቀመጡት ፈትለወርቅ ዋና ዋና የወጪ ንግድ ዕቃዎች በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር እንደሚወጡ ተናግረው ወጪ ንግዱ በተበታተነ መልኩ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች መመራቱ ለሕገ ወጥ ንግዱ ትልቅ ክፍተት እንደሆነ አክለዋል።

‹የሎጅስቲክ› ዋጋ ውድ መሆንን እንደምክንያት ያነሱት ሚኒስትሯ ምርቶችን ወደብ ድረስ የማጓጓዝ ሒደት ባለሀብቱን ለተጨማሪ ወጪ እየዳረጉት እንደሆነ ተናግረው በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት በወጪ ንግዱ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ መሳደሩንም ጨምረው ተናግረዋል። ከፋብሪካ ምርቶች ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ በአገሪቱ ከተፈጠረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ ፋብሪካዎች የጥሬ ዕቃ እጥረት እንዳጋጠማቸው ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መረጃ መሠረት በ2010 በጀት ዓመቱ ቡና፣ የቅባት እህል እና ጥራጥሬ ቀዳሚውን የወጪ ንግድ ገቢ እንዳስገኙ ለማወቅ የተቻለ ሲሆን በዚህም ረገድ ቡና 839 ሚሊዮን ዶላር በማስመዝገብ ቀዳሚውን ደረጃ እንደሚይዝ ለማወቅ ተችሏል። ባለፈው የበጀት ዓመት 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ገቢ ለመሰብሰብ ታስቦ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቶ በ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ተጠናቋል። እንደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ መሠረት በ 2012 በጀት ዓመት 10 ቢሊዮን ዶላር ከዘርፉ ለመሰብሰብ እንደታቀደ ታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here