የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ቀውስ

0
1255

በኢትዮጵያ ባሉ የተለያዩ ዩንቨርስቲዎች ውስጥ ግጭቶችን መስማት አዲስ ነገር አይደለም። የግጭቶቹ መንስዔዎች ምንም ሆኑ ምን የብሔር ገጽታ እንደሚሰጣቸውም ይነገራል። ይህንን ጉዳይ መነሻ ያደረገው ስንታየሁ አባተ፣ በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ላይ ተጨማሪ ሕመም ስለሆነው እና የትምህርት ሒደትን እስከማስተጓጎል የደረሰውን የዩንቨርስቲዎች ቀውስ መንሥኤ፣ የችግሩን ጥልቀት እና መፍትሔ በመዳሰስ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎ አቅርቦታል።

ከዓመት በፊት ነው፤ በአንዱ ቀን አመሻሽ 12፡00 ሰዐት ገደማ። ጀምበር አዘቅዝቃለች፤ ቀለሟም ወደ ቀይነት እየተለወጠ ከዕይታ ለመሰወር ትጣደፋለች። የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ከሥራ ባልደረባው ጋር ላምበረት አካባቢ በእግሩ እየተጓዘ ሳለ የገጠመው ነገር ለዚህ ጽሑፍ ጥሩ መንደርደሪያ ይሆናል። በዚያን ወቅት አንድ ወጣት መንገደኛውን ለእርዳታ ይማፀናል። “የአዳማ ዩኒቨርሲቲ አንደኛ ዓመት ተማሪ ነኝ። በረብሻው ምክንያት ከአዳማ በእግሬ ነው እዚህ የደረስኩት፤ እባካችሁ መሳፈሪያ ገንዘብ ተባበሩኝ፣ ወደ ቀወት [ሰሜን ሸዋ] የሚገኙት ቤተሰቦቼ እየሔድኩ ነው” እያለ ነበር።

ይህ ገጠመኝ የጽሑፉን አቅራቢ ሌላ የግል ገጠመኝ አስታውሶታል። በዩንቨርስቲ የኹለተኛ ዓመት ተማሪዎች በነበሩበት ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ግቢ መጋቢት 26/2002 በመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች መኝታ ክፍል ሞባይል ‹ጠፋ፣ ሰረቅከኝ› በሚል በኹለት ተማሪዎቸ መካከል የተነሳው ግጭት፥ በፍጥነት ወደ ትግራይና ኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ግጭት ተዛምቶ ነበር። እንዲህ ያለው እንደዋዛ የሚቀሰቀስ ቀውስ፥ ከላይ የተጠቀሰውን መሰል ተማሪዎች ሕይወት ከማመሳቀሉም ባሻገር፣ በድምሩ አገራዊ ኪሳራን ያስከትላል።

ዘንድሮ ብቻ “የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (አስቱ)” አጋጠመው በተባለው ሁከትና አለመረጋጋት ምክንያት ለኹለተኛ ጊዜ ትምህርት ከማቋረጡም ባሻገር እና “ከአቅሙ በላይ በሆነው የተማሪዎች ፍላጎት” ሳቢያ በመቸገሩ ዩንቨርሲቲው የቅድመ ምረቃ (የመጀመሪያ ዲግሪ) መደበኛ ተማሪዎቹን ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

ዩኒቨርሲቲው ጥር 12/2011 “ለአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የቅድመ ምረቃ መደበኛ ተማሪዎች በሙሉ” ሲል ባወጣው ማስታወቂያ “…በሴኔት ሕጉ መሠረት አንድ ተማሪ በሴሚስተር መከታተል ያለበትን ቢያንስ ሰማንያ ከመቶ (80%) የትምህርት ሽፋን በጋራ እንዲጣስ ተደርጓል። በዚህ ምክንያት በሴሚስተሩ ከተቀመጠው የትምህርት ቀናት ውስጥ ሠላሳ አራት ነጥብ አራት ከመቶ (34.4 %) ያልተከታተላችሁ ስለሆነ በሴኔት ሕጉ አንቀጽ 101.2 አንቀጽ 231.3 ተንተርሶ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ውሳኔ መሠረት እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ስለዚህ ከዛሬ ጥር 12 ጀምሮ እስከ ጥር 14/2011 ሁሉም የቅድመ ምረቃ መደበኛ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲውን ለቃችሁ ወደ ቤተሰቦቻሁ እንድትሔዱ ተወስኗል። ከጥር 15 ጀምሮ ማንኛውም አገልግሎት የሚቋረጥ መሆኑን እያሳወቅን ሕግና ደንብ አክብሮ መማር ለሚፈልጉ ተማሪዎች የአንደኛ ሴሚስተር ዳግም ምዝገባ ከየካቲት 25 እስከ 26/ 2011 መሆኑን እናሳውቃለን” ሲል ያትታል። የቅድመ ምረቃ መደበኛ ተማሪዎቹ ቁጥር 580 አካባቢ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

አስቱን ለዚህ ቀውስ ምን ዳረገው?
የአዲስ አበባ እና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች የተገቡልን ቃሎች አሉ በሚል ኅዳር ወር መጨረሻ ላይ ጥያቄ ማንሳታቸውና መልስ እስከሚያገኙ ድረስ በትምህርት ገበታችን ላይ አንገኝም በማለት ለሳምንታት አድማ መምታታቸው ይታወሳል። የኹለቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጥያቄያቸው የአገሪቱን አቅም ያልተረዳና አድማ ማድረግም ሕገወጥነት መሆኑ ተገልጾ በፍጥነት ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ከሚሉ ማስጠንቀቂያዎች ባለፈ ምክክር ተደርጎባቸው የተቋረጠው ትምህርት እንዲጀመር ሆኗል።

ተማሪዎቹ ‘ቃል ተገብቶልናል፤ ልንከለከል አይገባም’ በሚል ሲሰነዘሩ ከነበሩት ጥያቄዎች መካከል ከ97 እስከ 100 በመቶ የሚሆኑ ተመራቂዎች ከተመረቁ በኋላ የሥራ ዕድል እንዲመቻችላቸው፣ ከ90 እስከ 100 በመቶ የሚሆኑት ተመራቂዎች በውጪ አገራት እና በአገር ውስጥ የድኅረ ምረቃ ትምህርት (ኹለተኛ ዲግሪ) እንዲመቻችላቸው፣ እንዲሁም 54 በመቶዎቹ ደግሞ የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ የኢ-ለርኒንግ (የበይነ መረብ ትምህርት) ተግባራዊ እንዲደረግ እና ተማሪዎች በመኝታ ክፍላቸው ሆነው ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ እንዲደረግ፣ ለተማሪዎች የኢንተርንሺፕ ፕሮግራም የሚሰጠው ክፍያ ማሻሻያ እንዲደረግበት፣ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲዎቹ ተጠሪነት ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ወደ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መዛወር የለበትም የሚሉት ይታወሳሉ።

በተጨማሪም የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለእያንዳንዱ ተማሪ በነፍስ ወከፍ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር እንዲታደል እና ለሁሉም ተማሪዎች ዓለም ዐቀፍ ተቀባይነት ያለው ዲግሪ እንዲሰጥ ሲሉ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር አይዘነጋም። በእነዚህና መሰል ጥያቄዎች ዙሪያ የመንግሥት ተወካዮች በተገኙበት ተማሪዎቻቸ ውን ያወያዩት ዩኒቨርሲቲዎቹ ምላሾችንም በጽሑፍ ጭምር ሲያሳውቁ ነበር። የአብዛኞቹ ጥያቄዎች ምላሽ ጥያቄው አገሪቱን ያላወቀና የተለጠጠ እንደሆነ ተጠቅሶ ተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲዎቹ ባላቸው አቅም እንዲማሩና አድማውን ትተው ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ የሚሉ ነበሩ።

ተማሪዎቹ ጥያቄ ማቅረባቸው ነውር እንዳልሆነ ተገልጾ፣ ግን ደግሞ ትምህርቸውን ሳያቋርጡ ጥያቄያቸውን ማቅረብና ውይይት እየተደረገ አቅም በሚፈቅደው ልክ የተማሪዎችን ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሞከር በወቅቱ ኹለቱ ዩኒቨርሲቲዎች በተደጋጋሚ ይለጥፏቸው በነበሩ ማስታወቂያዎች ሲያሳውቁ ነበር።

በአዳማ ከዚያስ ምን ሆነ?
የኹለቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ትምህርታቸው ተመልሰዋል። ይሁንና ታኅሣሥ 25 እና 26/2011 በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ያልታሰበ ኹነት ተከሰተ። ዩኒቨርሲቲው በወቅቱ እንዳሳወቀው ሦስት ተማሪዎች ሕይወታቸው አልፎ ተገኙ። ይህም ተማሪዎቹን ዳግም ወደ አድማ መለሰ። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ለሚ ጉታ (ዶ/ር) እንደሚሉት የተማሪዎቹን ሕልፈት ተከትሎ ተማሪዎቹ የምርመራ ውጤቱ ካልተገለጸልን ትምህርት አንከታተልም በሚል አድማ መተው ሰንብተዋል። ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የተገኘው የአስከሬን ምርመራ ውጤቱ ጥር 4/2011 ቢገለጽላቸውም ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ እንዳልፈቀዱ ፕሬዘዳንቱ ለመገናኛ ብዙኃን አውታሮች በሰጡት መገለጫ አመልክተዋል። ከመግለጫዎቹ መረዳት እንደተቻለው በተማሪዎቹ ሕልፈት ዳግም የተነሳው የተማሪዎች ቅሬታ የቀደሙ ጥያቄዎችን እንደ አዲስ እንዲነሱ አድርጓል። ፕሬዘዳንቱ ተማሪዎቹ ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ እየተሰጣቸው ቢሆንም የመማር ማስተማር ሒደቱን ለማስቀጠል አለመቻሉንና ተማሪዎቹ ከአቅም በላይ እየሆኑ መምጣቸውን በመግለጽ በአስቸኳይ ትምህርታቸውን መቀጠል ካልቻሉ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠነቀቁ። ይህን ተከትሎም የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ቀደም ብለን የጠቀስነውን ውሳኔ አሳልፎ ተማሪዎቹ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ አሳሰበ።

ዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ማስታወቂያው ከተለጠፈ በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት ተማሪዎቹ እየጠየቁ ያሉት በቀደመው የዩኒቨርሲቲው አመራር (የውጭ ዜጋ የነበሩ) ቃል የተገባውን ነው ያሉ ሲሆን፥ ግለሰቡ የገቡት ቃል የግል አቋም እንጂ የመንግሥት አለመሆኑን ፍንጭ ሰጥተዋል። ለዚህ አንድ ማሳያ የሚሉት ደግሞ ቃል ገብተዋል የተባሉት ግለሰብ በነበሩባቸው ሦስት ዓመታት የፈፀሙት አንድም ቃል አለመኖሩን ነው።

የሆነው ሆኖ በተማሪዎቹና በዩኒቨርሲቲው መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ተማሪዎች ስድስት ወራትን ያለትምህርት እንዲያባክኑና የመጀመሪያ መንፈቅ ትምህርትን ወደፊት እንደ አዲስ እንዲጀምሩ አስገድዷል። ይህም በተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች ላይ ትልቅ ጫና እንደሚያሳድር ያነጋገርናቸው ተማሪዎችም ጠቅሰዋል።
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዘዳንት ከአዲስ ማለዳ ጋር በስልክ በነበረው ቆይታ ግቢውን ለቆ ወደ ቤተሰቦቹ መመለሱን በመግለጽ ምንም ዓይነት ሐሳብ ባይሰጥ እንደሚመርጥና ጥሩ ስሜት ውስጥ አለመሆኑን ተናግሯል። “የዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት እና መንግሥት ለተማሪዎች ጥያቄ ጆሮ መስጠት አለባቸው፣ አሁን ያለንበት ዘመን ተማሪን በአፍ ሸውዶ ማለፍ የሚቻልበት አይደለም፤ ተማሪውም በበኩሉ ጥያቄውን ትምህርት ሳያቋርጥ መጠየቅ አለበት። የተማሪ ጥያቄ ወደ ሌላ አጀንዳና አቅጣጫ ባይወሰድ መልካም ነበር፤” በማለት ከዚህ በላይ ማውራት እንዳማይችል ገልጿል።

ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ ኹከት ቀጣናነት ምን ከተታቸው?
ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችን በዋናነት ለሦስት ዓላማ በመቅረፅ ቁጥራቸውን ከ40 በላይ አድርሳለች። በዚህም መንግሥት በየአካባቢው ዩኒቨርሲቲዎችን በማስፋፋት በትምህርት ተደራሽነት በኩል ለሠራው ሥራ ውዳሴ ሲቸረው፣ ራሱም ራሱን ሲያሞጋግስ ይሰማል።

ሦስቱ የከፍተኛ ትምህርት ዓላማዎች በጥቅሉ ሲታዩ የመማር ማስተማር ሥራውን ማሳለጥ፣ የጥናትና ምርምር ማዕከላት መሆን እና የማኅበረሰብ አገልግሎትን መስጠት ናቸው። ይሁንና በትምህርት ጥራት፣ በትምህርት የታነፀ የሰው ኃይል ማፍራትና በማኅበረሰቡ ላይ ጠብ የሚል ውጤት በማስመዝገብ በኩል ዩኒቨርሲቲዎቹ “እምብዛም አልተሳካላቸውም” እየተባሉ በሚወቀሱበት በዚህ ዘመን ሌላ የራስ ምታት ተጨምሮላቸዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዩኒቨርሲቲዎች አንድም በውስጣቸው በሚፈጥሩት ችግር ከዚህ ሲያልፍም በሚገኙበት አካባቢ በሚፈጠር ግጭት “እንዲሸበሩ” እየሆኑ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ።

ይህንን ጉዳይ የማይክደው መንግሥትም የአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ሁኔታ ዩኒቨርሲቲዎችን የግጭት ማዕከል ለማድረግ በር እየከፈተ ነው ሲል “ግጭት ቀስቃሾችና ጠላት” የሚላቸውንም ይወቅሳል።

በተያዘው የትምህርት ዘመን ኅዳር መጀመሪያ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ አለመረጋጋት ገብተው እንደነበር ይታወሳል።
ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገቡበት ጊዜ በተቃረበበት ቀናት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአገሪቱ እያጋጠሙ ያሉ ግጭቶች ሰለባ እንዳይሆኑና ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዲከታተሉ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለተማሪዎች መልዕክት ማስተላላፋቸው አይዘነጋም።

ይሁን እንጂ ተማሪዎች ወደ ግቢያቸው በተመለሱባቸው ቀናት አሶሳ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ተከስተዋል። በወቅቱም የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚንስትሯ ሒሩት ወልደ ማሪያም (ዶ/ር) በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች “ሴት ተደፈረችና ተሰወረች” በሚል የሐሰት ወሬ ተማሪዎች ሰልፍ እንዲወጡ በማድረግ ግጭት ለመቀስቀስ መሞከሩን መግለጫ ሰጥተው ነበር።

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የመታጠቢያ ቦታዎች አካባቢ ኅዳር 10/2011 በኹለት ተማሪዎች መካከል የተነሳው ግጭት በፀጥታ ኃይል ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ቢደረግም በማግስቱ ግጭቱ አገርሽቶ ለሦስት ተማሪዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑንም ሚንስትሯ ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም።

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ “አንዲት ተማሪ በብዙ ሰው ተደፍራለች የሚል ሪፖርት [ሐሰተኛ ወሬ] መጥቶ ብዙ ሰዎች ጥቁር ለብሰው ሰልፍ እንዲወጡ ተደርጓል” ያሉት ሚንስትሯ፣ ነገሩ ሲጣራ ግን ተደፈረች የተባለችው ተማሪም ሆነች የመኝታ ክፍል ቁጥሩ ውሸት ሆኖ መገኙቱን መግለጻቸውን አዲስ ማለዳ በወቅቱ ዘግባ ነበር። በሰመራ ዩኒቨርሲቲም ሴት ተደፍራ ተሰወረች በሚል የሐሰት ወሬ ኅዳር 8/2011 ነውጥ ለማስነሳት ተሞክሯል ያሉት ሚንስትሯ፥ ነገሩ ሲጣራ ልጅቱ ቤተሰቦቿ ጋር ሔዳ መገኘቷን አረጋግጠዋል። በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ነውጥ ለማስነሳት ተመሳሳይ ወሬዎች እየተሰራጩ ተማሪዎችን ሰልፍ እንዲወጡና ወደ ግጭት እንዲገቡ ለማድረግ እየተሞከረ ነው ሲሉ ያማረሩት ሒሩት መንግሥት “በዩኒቨርሲቲዎች ግጭት ለመቀስቀስ በተደራጀ መንገድ እየሔዱ ያሉ አካላት አሉ” ለሚለው አንዱ ማሳያ እንደሆነ አመልክተውም ነበር።

በጊዜው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድረ ገዱ አንዳርጋቸው “የግለሰቦችን ችግር በግለሰብ ደረጃ መጨረስ ሲገባ ወደ ቡድንና ሌላ ቅርፅ እየለወጡ ለጋ ወጣቶችን መጠቀሚያ ማድረጉ” ተቀባይነት የለውም ሲሉ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል። የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ታደሰ ቀነዓ (ዶ/ር) “አጠገባችሁ ያለው ተማሪ ወንድማችሁ፣ እንደናንተው ከምስኪን ቤተሰብ የተገኘ ነው” በማለት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በጋራ በመሆን ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ እንዲፈልጉ ጥሪ ያቀረቡበት መልዕክትም በብዙዎች ዘንድ ሲወደስ ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ኅዳር 13/2011 በሕዝብ ተወካዮቸ ምክር ቤት ተገኝተው ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት ሊያጋድሏቸው የሚፈልጉ አካላት መጠቀሚያ እንዳይሆኑ “ራሴ ደብዳቤ ጽፌ መልዕክት አስተላልፌ ነበር” ካሉ በኋላ በዩኒቨርሲቲዎች የግጭትና አለመረጋጋት ስሜት ስላለ ተማሪዎች ከግጭት እንዲርቁ ጠይቀው ነበር።

ይሁን እንጂ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ዛሬም ጥሩ ነፋስ የለም፤ ይልቁንም ከውስጥም ሆነ ከውጭ ባለ አለመረጋጋት ተማሪዎች በስጋት ውስጥ ያሉባቸው ዩኒቨርሲቲዎች አሉ። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ግን አሁን ላይ ከኹለት ዩኒቨርሲቲዎች (አዳማ ሳንስና ቴክኖሎጂ እና ቡሌ ሆራ) ውጪ የመማር ማስተማር ሒደቱ እንደተሳለጠ ይገኛል ብሏል። ሰሞኑን በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአንደኛ ዓመት የእንግሊዘኛ ቋንቋ ፈተናን የብቃት መመዘኛ (ሲኦሲ) ነው በሚል ረብሻ ለመፍጠር ተሞክሮ ቶሎ መረጋጋቱንም አሳውቋል።

በቴፒ ከተማ በነበረው አለመረጋጋት ዩኒቨርሲቲው ነባሮቹንም ሆነ አዳዲስ ተማሪዎቹን ለመጥራት እስከ ጥር 8/2011 ድረስ ለመጠበቅ መገደዱም ይታወሳል።
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥር 16 ባወጣው የጥሪ ማስታወቂያ በአንዳንድ ጊቢዎቹ ትምህርት ተቋርጦ እንደነበር ጠቅሶ፣ እስከዛሬ ወደ ትምህርታቸው ያልተመለሱትን ተማሪዎች ጠርቷል፡፡

ሌላው የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ነው። በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የሚገኘው ዩኒቨርሲቲው ባጋጠመው አለመረጋጋት ከታኅሣሥ 19 እስከ ጥር 1 ተማሪዎቹ ወደ የቤተሰቦቻው ሔደው እንዲያርፉና ዩኒቨርሲቲውም የፀጥታ ችግሩን ለመፍታት ፋታ እንዲያገኝ በሚል ውሳኔ ማሳለፉ የቅርብ ትዝታ ነው።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ጫላ ዋታ (ዶ/ር) ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ግጭትና አለመረጋጋቱ ከዩኒቨርሲቲው የተነሳ ሳይሆን ከአካባባው የጀመረና ከሌሎችም ቀድሞ አለመረጋት ገጥሟቸው ከነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች ተዛምቶ የደረሰ መሆኑን አስቀድመው ያነሳሉ። በነበረው አለመረጋት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሰው ሕይወት መጥፋትም ሆነ የአካል ጉዳት አለመድረሱን በመግለጽም ተማሪዎቹ በሥነ ልቡና በመረበሻቸውና መረጋጋት ባለመቻላቸው ከቤተሰባቸው ጋር እንዲመክሩና እንዲረጋጉ በሚል የኹለት ሳምንቱ እረፍት መሰጠቱን አስረድተዋል። የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የነበረውን አለመረጋጋት ለማርገብ “የሰጠነው እረፍት ያሰብነውን ለማድረግ ተሳክቶልናል” ይበሉ እንጂ፥ ለዐሥር ቀናት ያክል ወደ ቤተሰቦቻቸው ከሔዱት ውስጥ ትምህርታቸውን ለመቀጠል እስካሁን ያልተመለሱት 20 በመቶ (2 ሺሕ ገደማ) የሚሆኑት ተማሪዎች መኖራቸውንም አልሸሸጉም።

በቅድመ ምረቃ መደበኛው ዘርፍ ከ10 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ያሉት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ለእረፍት የላካቸው ተማሪዎቹ ጥር 2 እና 3 ዳግም ተመዝግበው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ አሳስቦ ነበር። ይሁን እንጂ ጥር 6 እና 7ትም በቅጣት እንዲመዘገቡ የተደረጉት ተጨምረው የመጨረሻ ቀን እስከተባለው ማክሰኞ ጥር 14 የተመዘገቡት 80 በመቶ ተማሪዎቹ መሆናቸውን ፕሬዘዳንቱ ለአዲስ ማለዳ አሳውቀዋል። “ከአማራ፣ ከምዕራብ ኦሮሚያና አፋር የሚመጡ ተማሪዎቸ ናቸው የዘገዩብን” የሚሉት ፕሬዘዳንቱ፥ “እየመጡ ያሉና መንገድ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች እየደወሉልኝና እንድንጠብቃቸው እየጠየቁኝ ነው” ያሉም ሲሆን “እስከ ዛሬ (ጥር 14) ድረስ ነው ገደብ ያስቀመጥነው፤ በጣም የሚዘገዩ ከሆነ ለመቀበል እንቸገራለን” ሲሉም አክለዋል።

ከስድስት ዓመት በፊት (2005) “Causes of Ethnic Tension and Conflict among University Students in Ethiopia” በሚል ርዕስ በፊንላንድ ቴምፐር ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪው አበባው ይርጋ ያደረጉት ጥናት በዋናነት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ላይ አትኩሯል። የጥናቱ ግኝትም የብሔር ፌደራሊዝምን የተከተለው መንግሥት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥና ውጭያዊ ዐውዶች ተማሪዎችን ወደ ብሔር ግጭት እንዲገቡ አድርጓል ይላል። የዚህ ምክንያት ደግሞ ጠርዝ የረገጠ ብሔርተኝነት፣ በብሔሮች መካከል ያለው የፖለቲካ ተቀናቃኝነት እና የታሪክ ግንኙነት እንደሆነ ያትታል።

መንግሥት ከዚህ ቀደም ምን ሲሠራ ነበር?
በዩኒቨርሲቲዎች ግጭት ማጋጠም የጀመረው ዘንድሮ አይደለም፤ ይልቁንም በ2010 በራሳቸው የውስጥ ችግርም ይሁን በአካባቢው (አጠቃላይ አገሪቱ በነበረችበት የፖለቲካ አለመረጋጋት) የከፋ ችግር ውስጥ የገቡ ዩኒቨርሲቲዎች ነበሩ፣ ከዚያ በፊትም ብልጭ ድርግም የሚሉ ግጭቶች ዩኒቨርሲቲዎቹን ያላስጨነቁበት ጊዜ የለም።
በአንፃሩ መንግሥት ግጭቶች ቀድሞ መለየትና መከላከል ላይ ደካማ ነው ሲባል ይሰማል። ይልቁንም ዩኒቨርሲቲዎችን የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ከማድረግ ይልቅ የመከፋፈያ መድረክ አድርጓቸዋል የሚሉ ወገኖች በየዩኒቨርሲቲው የብሔር (በፖለቲካም ጭምር) ማኅበራት እየተደራጁ ልዩነት እንዲሰፋ ሆኗል ይላሉ። በእርግጥ በዘንድሮው ዓመት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ደመቀ መኮንን ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ የትምህርት ማዕከል እንዲሆኑ በሚል በዩኒቨርሲቲዎች የኢሕአዴግን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅት ክንፎችን ማደራጀት እንደማይቻል የትምህርት ዘመኑ ከመጀመሩ በፊት ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

በሌላ በኩል በኹለት ክልሎች አዋሳኝም ሆነ በሌላ ደረጃ በሚፈጠሩ ግጭቶች የየክልሉ ተማሪዎች “ፀበኛ ናቸው” ወደሚሏቸው ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሔዶ ለመማር ሲፈሩ፥ መንግሥት ተማሪዎችን አሳምኖና ሁኔታዎችን አረጋግቶ ኢትዮጵያን በዩኒቨርሲቲዎች በኩል ከማጠንከር ይልቅ አካባቢያዊ ምደባን ይሰጣል በሚልም ይተቻል። ለአብነትም ባለፈው ዓመት ትምህርት ሚኒስቴር የኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ ጊዜ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በ2010 ከክልሉ ወደ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው የነበሩ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች፣ በአገሪቱ ውስጥ ባሉ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመደቡ ሲደረግ፣ ከሱማሌ ክልል በኦሮሚያ ውስጥ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው የነበሩ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች በአገሪቱ ባሉ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መመደባቸው እየተነገረ ወቀሳ ሲሰነዘርበት ነበር።

ይህም ሌላ መዘዝ ይዞ ስለመምጣቱ የሚናገሩ ወገኖች በ2011 የትምህርት ዘመን መግቢያ ላይ መቀሌ ላይ በነበረ ሰልፍ ተማሪዎች ከክልላቸው ወጥተው መማር እንደማይፈልጉ መፈክር ሲያሰሙና ወላጆችም ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውን ሲገልጹ ነበር። በአዲስ አበባ የሚኖሩትም ቢሆኑ ጭንቀት ውስጥ ነበሩ። መስከረም 11/2011 ቢቢሲ በሠራው ዘገባ ያናገራቸውና በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የኹለተኛ ዓመት ተማሪ ልጅ ያላቸው አባት “ባለፉት ዓመታት የተፈጠረውን አይተናል፤ ብዙዎች ለመማር ሔደው ሞተዋል። ይህ ችግር አሁንም እየቀጠለ ነው። በዚህ ሁኔታ ልጆቻችን የኛን ተስፋ እንዲሞሉ ብለን ሬሳቸውን መቀበል አንፈልግም፤ ለመላክም ፍቃደኛ አይደለሁም” እንዳሉትና ልጃቸው ወደ ተመደበበት ዩኒቨርሲቲ እንዳይሄድ ስለመወሰናቸው ጽፏል።

በቅርቡ ደግሞ ከቡሌ ሆራ ወደ ባሕር ዳር የሔዱ 2500 የሚሆኑ ተማሪዎች በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው እንዲማሩ ጠይቀው አይቻልም በመባላቸው በከተማዋና ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አመፅ ለመቀስቀስ እንደሞከሩ፣ ከተማው ላይ ዝርፊያ እስከመፈፀም እንደደረሱም ከተማ አስተዳደሩና ክልሉ መግለጻቸው ይታወሳል። ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በፌደራል መንግሥት ሥር ያሉና ጥበቃውንም የሚያደርገው የፌደራል መንግሥት በመሆኑ ወደ ተመደቡበት ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ አንሔድም በማለት ጥያቄያቸውን በኃይል ለማስፈፀም የተንቀሳቀሱት ተማሪዎች በአስቸኳይ ባሕር ዳርን ለቀው እንዲወጡ (ወይም ወደ ዩኒቨርሲቲያቸው አልያም ወደ ቤተሰባቸው እንዲሔዱ) ውሳኔ ስለመተላላፉ የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አሰማኸኝ አስረስ ለአዲስ ማለዳ መናገራቸው ይታወሳል።

የግለሰብ ግጭት ስለምን ወደ ብሔር ያድጋል?
በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች በግለሰብ መካከል የሚነሱ ግጭቶች ፈጥነው ወደ ቡድንና ብሔር ከፍ ሲሉ ይስተዋላል። መንግሥትም ይህንኑ እንደሚል ቀድመን ያነሳነው የሚኒስትር ሒሩት መግለጫ አንድ ማሳያ ነው። መንግሥት “ፀብ አጫሪና ኢትዮጵያን በግጭት ቀጣና ውስጥ እንድትኖር የሚፈልጉ ጠላቶች” በዩኒቨርሲቲዎች የብሔር ግጭትን ለመቀስቀስ ተኝተው እንደማያድሩ ነው በተደጋጋሚ ሲነገር የሚሰማው። ጥር 15/2011 ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ የሰጡት ሒሩት በዩኒቨርሲቲዎች ግጭት ለመቀስቀስ የሚሠሩ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እንዳሉ መረጃ መያዛቸውንም ተናግረዋል።

ጫላ በዩኒቨርሲቲዎች የግለሰብ ፀብ ለምን ወደ ብሔርና ቡድን ከፍ ይላል ለሚለው ጥያቄ መታየት ያለበት ተማሪዎቹ ከልጅነታቸው ጀምሮ ዩኒቨርሲቲ እስከገቡበት ድረስ (በወላጅና መምህሮቻቸው) ምን እየተባሉ ነው ያደጉት የሚለው እንደሆነ በማሥመር ስለኢትዮጵያዊነት ዕድሜውን [ሙሉ] ያልተነገረውን ሰው በሦስት ዓመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታ ኢትዮጵያዊነትን ሰብኮ ማሳመን እንደማቻል ይገልጻሉ።

ጫላ ያለንበት የፖለቲካ፣ ምጣኔ ሀብት፣ ቴክኖሎጂና ሌሎችም ሁኔታዎቸ ታሳቢ መደረግ እንዳለባቸው ያነሱም ሲሆን፣ በሽግግር ላይ ያለ ማኅበረሰብ የሚገጥመው ፈተና አለ፣ ወጣቱም በተለይ ዩኒቨርሲቲ ያለውና ዕውቀት ቀመሱ ያለ ልፋት በአቋራጭ የሚፈልገውን ለማግኘት የመጓጓት ውጤትም እንደሚሆን ሐሳባቸውን ያክላሉ።

የዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንቶች ሹመት
ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር የዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንትነት ብቃትን፣ ልምድንና የትምህርት ደረጃን መሠረት አድርጎ ከሚደረግ ውድድር ይልቅ ዩኒቨርሲቲው የተገነባበት አካባቢ ተወላጅነትን የበለጠ ዋጋ መስጠቱ ዩኒቨርሲቲዎችን ዓላማ አስቷል ከሚባሉት መካከል እንደሆነ የሚያምኑ አሉ። ስለዚህ ጉዳይ ሐሳባቸውን የጠየቅናቸው ጫላ የትምህርት ተቋምን ለመምራት ቢያንስ ዝቅተኛው መሥፈርት መሟላት እንዳለበት ያምናሉ። ይሁንና የአካባቢው ተወላጅ መሆኑ ዩኒቨርሲቲው በሚሰጠው የማኅበረሰብ አገልግሎትም ሆነ በሚኖረው ኅብረተሰባዊ መስተጋብር ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በቀላሉ በሥነ ልቡና ለመግባባት እንደሚያግዝ ያነሳሉ፤ ይሁን እንጂ አቅምና ልምድ መቅደም እንዳለበት አፅንዖት ይሰጣሉ። “በደፈናው የአካባቢው ሰው መሆን አለበት፣ አይ መሆን የለበትም ሊባል አይገባም” በማለትም ቁርጠኝነቱ ካለ መሥራት ስለሚቻል የውጭ ዜጋ ሳይቀር በብቃቱ ተወዳድሮ ቢመራ፥ ውጤት ካመጣ ችግር እንደሌለውና ይህንን የሞከሩ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳሉ ይጠቅሳሉ። “እንዲያው የአካባቢው ተወላጅ ይምራ እየተባለ ሀብትና ንብረት ሲዘረፍ ማየትም አያስፈልግም፤ ይህ ሲሆን ስታይ ታዝናለህ” ሲሉም ያክላሉ።

መፍትሔው ምንድነው?
ጫላ እንደሚሉት መፍትሔው ትውልዱን ለዓላማ ስለመኖር ማስተማር ያስፈልጋል። ልጆች ሲያድጉ አገራቸውን፣ ሥራንና ሰውን እንዲወዱ ማስተማርና ኢትዮጵያዊነትን ማስረዳት ያስፈልጋል። ወላጅና የታችኛው የትምህርት መዋቅር ላይ ተማሪዎች ምን እየተሰበኩ እንደሆነ በወጉ መፈተሽ እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ።

National Center for Conflict Resolution Education (NCCRE) and Richard Bodine የተሰኘ ድርጅት ዳይሬክተር ዶና ክራውፎርድ በትምህርት ተቋማት ተማሪዎቸ መካከል ትንሽ ነገር ትልቅ ግጭት እንደሚያስነሳ በማስገንዘብ በሚጀምረው ጽሑፋቸው አንድ ተማሪ ያለፈቃድ የሌላውን የትምህርት መሣሪያ ተጠቀመ በሚል ሌላ ቅርፅ ይዞና ትልቅ የግጭት መነሻ ሆኖ የሚመጣበት አጋጣሚ እንዳለም ያስረዳሉ። ግጭትን በእንጭጩ ለመቅረፍ በጽሑፋቸው አራት ዋነኛ መፍትሔዎች ብለው ከጠቀሷቸው መካከል ኹለቱ ፈጥኖ ኃላፊነትን መወጣት እና ማዳመጥ ናቸው። የግጭቱ ተሳታፊዎች የሚሰማቸውን እንዲናገሩ ዕድል መስጠትና ተገቢ እርምጃ መውሰድ ትኩረት እንደሚፈልግም ያሠምሩበታል።

“Conflict in higher education and its resolution” በሚል ርዕስ የእንግሊዙ ስትራትክላይድ ዩኒቨርሲቲው ፒተር ዌስት ባደረጉት ጥናት ማጠቃለያ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚነሱ ግጭቶች ከተቋማቱ አልፈው እንደሚወጡና አውዳሚ እንደሚሆኑ ሊሰመርበት እንደሚገባ ይመክራሉ። መፍትሔውም የግሉን ዘርፍ አመለካከትና ዘዴ በመበደር የሚመጣ አለመሆኑን፤ ይልቁንም የራሳቸውን አስተዳደራዊና ትምህርታዊ እሴቶች ታሳቢ ያደረጉ አዳዲስ መላዎችን ፈጥኖ በማፍለቅ እርቅን እየፈፀሙ አንድነትን ቶሎ መመለስ እንደሆነ ይገልጻሉ።

የአበባው ጥናት የግጭቶቹ መነሻዎች ከመንግሥት የፖለቲካ ፍላጎት ጋር እስከመያያዝ እንደሚደርሱ ያሳያል። የብሔር ግጭቶችንና ስጋቶችን ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርት ሒደታቸው፣ በባሕል ትውውቅና ቅርርብ መድረኮች እንዲሁም በጠንካራ ሕግ ገቢራዊነት መከላከል ይገባቸዋል፤ ይላል ጥናቱ። ከዩኒቨርሲቲ ውጭ እየተነሱ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ግጭቶችን ደግሞ ከማኅበረሰቡና መንግሥት ጋር በሚኖር ጠንካራ ትብብር ለመከላከል መሞከር አዋጭ መሆኑን ይጠቁማል። የውስጡም ሆነ የውጭው ግጭት በአንድም ሆነ በሌላ ከመንግሥት ፖሊሲዎች ጋርም የሚገናኙ በመሆኑ መንግሥት ራሱን ሊፈትሽ እንደሚገባ ማጠቃለያው ላይ ሰፍሯል።

ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here