ጥቅምት 30 በማይካድራ በተፈጸመው ጭፍጨፋ ከ 1 ሺህ 644 በላይ ሰዎች ሰለባ መሆናቸውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው በማይካድራው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ላይ ስድስት ወራት የፈጀ ጥናት ማድረጉ ገልጿል።
የጥናቱ ዓላማ ድርጊቱን ለዓለም አቀፍ ማኀበረሰብ ማሳወቅ፣ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡና የተጎዱ ወገኖች እንዲካሱ ማድረግ ሲሆን፤ በጥናቱ መንግስት በአሁኑ ወቅት በአሸባሪነት የፈረጀው የትህነግ ቡድን ለዓመታት በወልቃይት ጠገዴና በጠለምት አካባቢ በአማራዎች ላይ የፈጸመው ግፍ መዳሰሱም ታውቋል።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኀላፊና መምሕር ባምላክ ይደግ (ዶ.ር) ጅምላ ጭፍጨፋው በ1968 ዓ.ም አሸባሪው የትህነግ ቡድን ያዘጋጀው ፍኖተ መርህ አካል እንደሆነ ገልጸዋል።
ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ በድምጽ አልባ መሳሪያ ጅምላ ጭፍጨፋ ለሚፈጽሙ ወጣቶችና ለፖሊስ አባላት ስልጠና ተሰጥቷል፤ የባለሀብቶችን አስከሬን ለማመላለስ ዝግጅት ሲያደርጉ እንደነበርም በጥናቱ ተረጋግጧል። ከድምጽ አልባ መሳሪያ የሚያመልጡትን በመሳሪያ የሚገድል ቡድንም ተዘጋጅቶ እንደነበር አስታውቀዋል።
ከዚያም በማይካድራ ከተማ የሚኖሩ አማራዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ማሳሰቢያ ተሰጠ፤ መታወቂያና ሲም ካርዳቸውን በመሰብሰብም ማንነታቸውን የመለየት ሥራ ተከናወነ፤ ለቀናት በቂ ዝግጅት ከተደረገ በኋላም ጥቅም 30 እስከ ለሊቱ 9:00 ድረስ በአሰቃቂ ሁኔታ ጭፍጨፋው ተፈጽሟል ሲሉ አስረድተዋል።
ሰነዶችን ዋቢ በማድረግ፣ የአካባቢውን ነዋሪዎች በመጠየቅና የመስክ ምልከታ በማድረግ በተሠራው ጥናት በወልቃይት ጠገዴና በጠለምት አካባቢዎች በርካታ ጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል። የጥናት ቡድኑ አባል ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ አስራደ በርካታ ወጣቶችና ታሪክ አዋቂዎች ተገድለው በጅምላ ተቀብረዋል ሲሉ ገልፀዋል።
ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም በማይካድራ በተፈጸመ የዘር ጭፍጨፋ ብቻ ከ 1 ሺህ 644 በላይ ሰዎች ሰለባ ሆነዋል። 1 ሺህ 563 ሰዎች በጅምላ መገደላቸው በጥናቱ ተረጋግጧል። 81 ሰዎች ደግሞ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል። ከ50 በላይ ሕጻናትም ያለ ወላጅ ቀርተዋል። ከዚህ ውስጥ ዘጠኙ ሴቶች መሆናቸውም ተገልጿል።
መረጃው ከተጠናቀረ በኋላ ተጨማሪ 31 ሰዎች ተገድለው መገኘታቸውን የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ ይህም የሟችና የተጎጂዎች ቁጥር ከዚያ በላይ እንደሚሆን ማሳያ ነው ብለዋል። የተጨፈጨፉ ሰዎች አማካይ ዕድሜም 31 መሆኑንም ጨምረው አስታውቀዋል።
የጥናቱ ግኝት የመጀመሪያው ዙር የአማርኛ ጽሑፍ እየተጠናቀቀ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን መረጃው በተለያዩ ዘዴዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀው ይደረጋል ተብሏል። ወደ እንግሊዘኛ ቋንቋ በመተርጎምም ለዓለም አቀፍ ተቋማት፣ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የውጪ ሀገራት ኢምባሲዎች እንዲሁም ለልዩ ልዩ ሀገራት እንዲደርስ ይደረጋል ሲሉ አስታውቀዋል።
የ41 ዓመታት ችግር በአንድ ጥናት ብቻ ስለማይመለስ ሌሎች ተቋማት ተጨማሪ ጥናት እንዲያደርጉም መምህራኑ መጠየቃቸውን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘግቧል።



