የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አሸብር ሉታ እንደተናገሩት ጊቤ የተሰኘችው የኢትዮጽያ የመጀመሪያዋ መርከብ ከ 20 ቀናት በፊት 11ሺሕ 200 ሜትሪክ ቶን የፍጆታ ዕቃ ለሱማሌ ላንድ ገበያ ማጓጓዟን ማወቅ ተችሏል፡፡
አሸብር አክለውም ሸበሌ ተብላ የተሰየመችው የኢትዮጵያ ኹለተኛዋ መርከብ በተጨማሪ ከ11ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ ስኳርና ሩዝ ይዛ በርበራ ወደብ መድረሷን ያነሱ ሲሆን፣ መርከቧ ከሕንድ የጫነችውን ስኳርና ሩዝ በመያዝ የበርበራ ወደብ ላይ ማራገፍ እንደቻለች ተጠቁሟል።
በበርበራ ወደብ ላይ የተጀመረው አገልግሎት የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ያነሱት አቶ አሸብር፣ ከዚህ በተጨማሪ የሱማሌ ላንድ ነጋዴዎች ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸውን ተከትሎ ድርጅቱ አገልግሎት መስጠቱን በመደበኛነት እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
ጊቤና ሸበሌ የተባሉት መርከቦች በኮሪደሩ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ መሆናቸውን የገለፁት ዳይሬክተሩ፣ በነሐሴ ወር አጋማሽ ጊቤ መርከብ 15ሺ ሜትሪክ ቶን ሩዝ በመጫን በርበራ ወደብ እንደምትገባም ተናግረዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013


