የአዲስ አበባ አስተዳደር በሰንዳፋው ቆሻሻ ማስወገጃ ላይ ፍላጎት የለውም ተባለ

0
964

ከአዲስ አበባ አስተዳደር በ37 ኪሎ ሜትር ርቀት ሰንዳፋ ላይ ተገንቶ የነበረውና በአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ ገጥሞት ሥራ ያቆመው ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ ላይ ብዙም ፍላጎት እንደሌለው ታወቀ፡፡

አዲስ ማለዳ ከአንድ የከተማዋ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ እንደሰማችው አስተዳደሩ በተቃውሞ የተቋረጠውን ማስወገጃ ወደ አገልግሎት የመመለስ ፍላጎት የለውም፡፡

የአዲስ ማለዳ ምንጭ እንዳሉት አንድ የአሜሪካ ኩባንያ በስፍራው ጥናት እያደረገ ይገኛል። በጥናቱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴርም እየተሳተፈ ስለመሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ጥናቱም ከዚህ ቀደም የተደፋው ቆሻሻ በአካባቢው ላይ ተፅዕኖ ይሩረው፣ አይሩረው ለማወቅ እና መፍትሔውስ ምንድን ነው የሚሉትን ለመለየት የሚካሄድ ነው ተብሏል፡፡

ይሁንና የጥናቱ ውጤት ሲታወቅ በቀጣይ ምን ይሁን የሚለው ላይ እንደሚመከርበትም ምንጫችን ገልጸዋል፡፡ ውጤቱ ምንም ይሁን አስተዳደሩ ግን ከዚህ በኋላ ቆሻሻን ወደዚያ የመወሰድ ፍላጎት እምብዛም እንደሌለው ምንጫችን አክለዋል፡፡

ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ በቅርቡ የቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራውን ጎብኝተው እንደነበር እና በወቅቱም ከስፍራው መጥፎ ጠረን ይወጣ እንደነበር ታዝበናል ያሉት ምንጫችን ነዋሪውም ቆሻሻው ወደ ስፍራው ሔዶ እንዲደፋ ፍላጎት የለውም ብለዋል፡፡ ዘመናዊ ነው በሚል በተገነባው የቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራ የሚገኙት ነዋሪዎች በአብዛኛው አርሶ አደሮች ሲሆኑ ይወጣል ከሚባለው መጥፎ ጠረን ባሻገር ‹የካሳ አንሶናል› ጥያቄ እንደሚያነሱም ምንጫችን ገልጸዋል፡፡

ተቃውሞ ያነሱት ነዋሪዎቹ ከፊሉን የፕሮጀክት ክፍልና ማሽሪዎች ማቃጠላቸውን አክለዋል። ከቆሻሻ ማስወገጃው የሚወጣን መጥፎ ጠረንና ፍሳሽ ለመቀነስ በሚል ተገዝተው የነበሩ ማሽነሪዎች የዛሬ ዓመት አካባቢ በነበረው የኦሮሚያ አለመረጋጋት ወቅት መቃጠላቸውንም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በቅርቡ ፕሮጀክቱን ወደ ሥራ ለመመለስ እየተሰራ ነው የሚል ዘገባ በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ መተላለፉን ተከትሎ ነዋሪው ዳግም ወደ ተቃውሞና አላስፈላጊ ነገር ሊገባ ነበር ያሉት ምንጫችን ከተማ አስተዳደሩ ወደዚህ ችግር ውስጥ መግባት እንደማይፈልግም ጠቁመዋል፡፡

ሥራ በጀመረ ገና በሰባት ወሩ ሐምሌ 7/2008 ባጋጠመው ተቃውሞ ሥራውን ለማቆም የተገደደው የማስወገጃ ስፍራው በወቅቱ የተነሳበት ጥያቄ የተከፈለው ካሳ አንሷል የሚል ጭምር እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይሁንና ከተማ አስተዳደሩ ከነዋሪዎቹ ባሻገር እስከ ኦሮሚያ ክልል ባሉ የተቋማት እርከኖች በመደራደር ሥራውን ዳግም ለማስጀመር ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም እስካሁን አዎንታዊ ምላሽ አለመገኘቱ ተሰምቷል፡፡

ባለፈው ግንቦት 2010 የማስወገጃ ሥፍራውን ወደ ሥራ ለመመለስ እንዲቻል ከተማ አስተዳደሩ ከኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናትና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር አቋርጦት የነበረውን ውይይት ሊጀምር እንደሆነ ገልጾ ነበር፡፡

አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ የወጣበት ‹‹የሰንዳፋ ዘመናዊ የቆሻሻ ላንድ ፊል›› ከፈረንሳይ መንግሥት  በተገኘ ገንዘብ የተገነባ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

መጀመሪያ ሲገነባ የአዋጭነት ጥናትና ከማኅበረሰቡ ጋር መግባባት ያስቻሉ ውይይቶች አልተደረጉም ነበር ወይ ያልናቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊው በወቅቱ ተደርጓል በሚል ወደሥራ መገባቱን ጠቅሰዋል፡፡

በሐምሌ 2008 ባጋጠመው ተቃውሞ አገልግሎቱ ሲቋረጥ የከተማዋ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጆች የፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጀመር መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር አስታውሰው ተቃውሞው የመጣው ቆሻሻ መድፋት ሲጀመር እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቷ አልዘምን ያላትና የራስ ምታት የሆነባት አዲስ አበባ ዛሬም 60 ዓመታትን ለሚጠጋ ጊዜ ባገለገለው ረጲ እየከመረች ትገኛለች፡፡ ከወራት በፊት ተጠናቀቀ በሚል የተመረቀውና 50 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ የነበረው የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ ሲጀምር የከተማዋ ቆሻሻ በወጉ እየተለየ ከቀረበለት ሙሉ ቆሻሻውን ይጠቀማል ተብሎ የነበረ ቢሆነም እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቷል፡፡

አስተዳደሩ በ500 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ የሚርፉ 85 የቆሻሻ ቅብብሎሽ ጣቢያዎችን ለመገንባት እቅድ ካወጣም ከራርሟል፡፡ ለማሳያ በሚልም በ2010 ለኹለተኛ ጊዜ ወር በገባ በመጨራው ቅዳሜ እንዲካሄድ ታስቦ በተጀመረው የፅዳት ዘመቻ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ዳሰለኝ እና የቀድሞው ከንቲባ ድሪባ ኩማ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠው ነበር፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here