ኢሰመኮ ተገቢውን ምላሽ እየሰጠ አይደለም ተባለ

0
383

የኦሮሚያና ሱማሌ ልዩ ሪፖርት አወዛገበ

በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ስለተከሰተው የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ለኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሪፖርት ቢደረግም እስካሁን በኮሚሽኑ በኩል ምንም ዓይነት ምላሽ አለመሰጠቱ ተገለጸ።

በዞኑ ከመስከረም 3/2011 ጀምሮ እስካሁን መቋጫ ባላገኘው ግጭት ከ34 ሺሕ በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን ኮሚሽኑ የምርመራ ሥራም ሆነ የዕርዳታ ድጋፍ ለማድረግ አለመሞከሩ ተነግሯል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ሁሴን ዳሪ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት በመስቃንና በማረቆ ወረዳ መካከል የተፈጠረው ግጭት በየጊዜው እየተባባሰ መጥቷል። ሰብኣዊ መብት ኮሚሽንም መረጃው በተደጋጋሚ ቢደርሰውም በሕፃናትና በአረጋዊያን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በዝምታ እያለፈው እንደሚገኝ ነው የተገለጸው።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በመስቃን ወረዳ በኢንሴኖ ከተማ በቅርብ ቀን በአንድ ታዳጊ ልጅ ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ በብልቱ ላይ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን የአርሶ አደሮችን ማሳ ጨምሮ በርካታ ንብረቶች በእሳት መቃጠላቸውና መውደማቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናግረዋል። ከግጭቶቹ እልባት አለማግኘት ጋር ተያይዞ የሰዎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት እየተገደበ ሲሆን የሕዝብ መጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ላይም ጥቃት እየተፈፀመ እንደሆነ ታውቋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ሁሴን ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ በጥር 18 ኮድ ሦስት 12789 ደቡብ ሕዝቦች የሆነ የሕዝብ ማመላለሻ ከሐዋሳ ወደ ቡታጅራ መንገደኞችን ጭኖ በመጓዝ ላይ እንዳለ ማረቆ ወረዳ ልዩ ሥሙ ወርካ በሚባል ቦታ ላይ ሲደርስ የተደራጁ ቡድኖች ባደረሱት ጥቃት በተሽከርካሪው ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱንና በመንገደኞችም ላይ መጠነኛ ጉዳት ማጋጠሙን ለማወቅ ተችሏል። ይህንንም ተከትሎ ወዲያውኑ ለኢሰመኮ በስልክ ጥቆማ ቢደረግም የተገኘው ምላሽ ዝምታ ብቻ ነው ሲሉ ሁሴን ጨምረው ገልጸዋል።

የኮሚሽኑ የ2011 በጀት ዓመት የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀረበበት ወቅት እንደተገለጸው የኢሰመኮ ከሕዝብ የሚቀርብለትን ጥቆማ ተቀብሎ ተገቢውን የማጣራት ሒደት እና የዕርዳታ እንቅስቃሴ ከማድረግ አንፃር ደካማ ነው ተብሏል።
የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶችን አስመልክቶ ኮሚሽኑ በጥር 26/2011 በሱማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች ላይ ልዩ ሪፖርት እንዲያቀርብ አጀንዳ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም ሪፖርቱ እንዳልደረሰለት ገልጾ ሳያቀርብ ቀርቷል በሚል ከቋሚ ኮሚቴው ቅሬታ ተነስቶበታል። በሌላም በኩል በኮሚሽኑ የጅግጅጋ ቅርንጫፍ በሐምሌ 28/2010 በደረሰ ውድመት እና የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ታፍነው ሲወሰዱ ኮሚሽኑ ምንም ማድረግ አልቻለም የሚሉ አስተያቶች ተሰንዝረዋል። በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር እሸት ገብሬ ምላሽ ሲሰጡ ኮሚሽኑ እንዲያቀርብ የታዘዘውን ልዩ ሪፖርት በተገቢው ሰዓት ለምክር ቤት መላካቸውን ገልጸዋል። ምክትል ኮሚሽነሩ ይህን ይበሉ እንጂ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ጣልቃ በመግባት ተላከ የተባለው ሪፖርት አለመኖሩን እና አሁን እየቀረበ ያለው ሪፖርት ክህደት የተሞላበት ነው ማለታቸውን አዲስ ማለዳ ለመታዘብ ችላለች።

በጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ላይ ለተነሳው ጥያቄ እሸት ምላሻቸውን ሲሰጡ ዋናው መሥሪያ ቤት ጥሪ በደረሰው ሰዓት ጊዜ ሳያጠፋ እንደተንቀሳቀሰ እና መረጃዎችን አሰባስቦ ለፌደራል ፖሊስ እንዳስተላለፈ አንስተዋል። በመሆኑም ኮሚሽኑ የአቅሙ ጥረት አድርጓል ብለዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ አክለውም ኮሚሽኑ “ከለውጡ በፊት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት አለ እያለ ሲጮህ እንደነበር”› አውስተው “ግኝቶችን ለአስፈፃሚ አካል ስናቀርብ እንደዚህ ዓይነት የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም እንባል ነበር” ሲሉ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

የኢሰመኮ ከሚሸነር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር በአሁኑ ሰዓት ከቦታቸው ተነስተው የአምባሳደርነት ሥልጠና ላይ ሲሆኑ፣ የኮምሽነርነት ቦታው በይፋ ክፍት መሆኑ ተመልክታል። የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንዳመላከቱት፣ ምንም እንኳን ኮሚሽነሩ በሕዝብ ታጭተው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሾም ቢኖርባቸውም፣ የቀድሞው የሂዩማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ዳይሬክተር ዳንኤል በቀለ የኮሚሽንርነቱን ቦታ ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here