ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ሊተገበር ነው

0
409

የኢትዮጵያ መንግሥት በኢንዱስትሪዎችና በተለያዩ ተቋማት የሚታዩ የሠራተኛ ፍልሰትን ለመቀነስ እንዲሁም የሠራተኞችን መብት ለማስጠበቅ የደመወዝ ወለል ለመተግበር መስማማቱን የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ገለፀ።

በሚኒስቴሩ፣ በአሠሪዎችና በሠራተኛ በተደረገ ውይይት የደመወዝ ወለል በእያንዳንዱ ዘርፍ መወጣት እንዳለበት የተወሰነ ሲሆን ጥናት ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል። ከወር በፊት ለተወካዮች ምክር ቤት የተላከው የሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ ላይ መካተቱንም የሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አሰፋ ይርጋለም ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

የእያንዳንዱ ዘርፍ የደመወዝ ወለል በረቂቅ አዋጁ ላይ ባይጠቀስም፤ ሕጉ በፓርላማ ከፀደቀ በኋላ መመሪያ እና ደንብ በግልፅ እንደሚቀመጥ ታውቋል። ፓርኮችና ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ የሠራተኛ ፍልሰት እየፈተናቸው መሆኑ እና የሠራተኞች ደምወዝ አነስተኛ ለአዋጁ መውጣት እንደ ዋነኛ ምክንያት የተገለፁ ሲሆን አዋጁን በዚህ በጀት ለማፀደቅ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ሲል ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ለ3 ተከታታይ ዓመታት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ያደረገው የክዋኔ ኦዲት ግኝት እንደሚያሳየው በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሠራተኞች ፍልሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። ለአብነትም በቦሌ ለሚ ቁጥር አንድ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ በ2008 የመጀመሪያ ሦስት ወራት ከተቀጠሩ ሠራተኞች 42 ነጥብ 5 በመቶ ለቅቀዋል።

በ2009 ደግሞ በዚሁ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሥራ ዕድል ካገኙት 72 ነጥብ 3 በመቶዎቹ ሥራውን ትተው ሔደዋል፡፡ በቀጣይ ዓመት ደግሞ፤ የለቀቁት ሠራተኞች ቁጥር 98 ነጥብ 9 በመቶ መድረሱን የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የክዋኔ ኦዲት ግኝት ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን የሠራተኛው የደመወዝ ወለል በአዲሱ የሠራተኛና አሰሪ አዋጅ ላይ ይካተት የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ ቢያቀርብም ለዓመታት አጥጋቢ ምላሽ ከመንግሥት አለማግኘቱ ይታወሳል።

አሁን ላይ መካቱቱን የደገፉት የኮንፌዴሬሽኑ የኮሚኒኬሽን ኃላፊ ማዕሾ ገብረመድህን የደመወዝ ወለሉ ከተተገበረ የሠራተኞች የኑሮ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ገልፀዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች፤ ምግብና ትራንስፖርት አማካይ ደመወዝ 700 ብር የሚሆን ሲሆን በሌሎች ኢንዱስትሪዎችም የሚከፈለው ከዚህ ብዙም የማይሻል መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አሕመድ አርብ፣ ጥር 24 ከፓርላማ ጋር በነበራቸው መርሃ ግብር፤ የፋብሪካ ሠራተኞች በሚያገኙት ገቢ እራሳቸውን ለመቻል መቸገራቸውን ገልጸዋል።

የደመወዝ አነስተኛ መሆኑን ተከትሎ ብዙዎች እንደሚለቁና ፋብሪካዎች ከአቅማቸው በታች እንዲሠሩ መገደዳቸውን ይገልፃሉ። ይህም ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ዕድገት ትልቅ እንቅፋት መሆኑን ባለሙያዎች ያነሳሉ።

የአምራች ዘርፉ ወደ 200ሺሕ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን በሚቀጠሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ቁጥሩን ወደ ኹለት ሚሊዮን ከፍ ለማድረግ በኹለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ታቅዷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here