ከሰሜን ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ቤት ተከራይተው የሚገኙ ግለሰቦች መንግሥትና በጎ አድራጊዎች በሚያደርጉት ድጋፍ ላይ አድሎ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በድጋፍ አሰጣጡ አድሎዓዊ አሠራር አለ የሚሉት ተፈናቃዮቹ፣ በጦርነቱ በተፈናቀሉበት ወቅት ሕፃናትን ይዘው ስለነበር በፍጥነት መጠለያ እንደሚያስፈልጋቸው በመገንዘባቸው ለጊዜው ቤት ተከራይተው ነበር። ሆኖም አሁን ያላቸውን ገንዘብ ስለጨረሱ ለሌሎች ተፈናቃዮች የሚደረገውን ድጋፉ እያገኙ አለመሆናቸውን ነው የጠቆሙት።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ የሚናገሩት የእርዳታ ድጋፍ የሚያገኙት በከተማው ባሉ የተለያዩ መጠለያዎች የሚገኙ ሰዎች በመሆናቸው ወደ መጠለያዎቹ መቀላቀል ቢፈልጉም መጠለያዎቹ በመሙላታቸው መጠጋት እንዳልቻሉና ከመንግሥትም ሆነ ከበጎ አድራጊዎች የሚመጣውን ድጋፍ እንደሌሎች ተፈናቃዮች እያገኙ አለመሆናቸውን ነው።
የመጠለያ ቦታው ቢሞላም በተከራየንበት ሆነን ድጋፍ ሊሰጠን ይገባል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ከየአካባቢው የተፈናቀሉትን የእርዳታው ተካፋይ ለማድረግ የሚመዘግቡ አካላት ዘንድ ሔደው ቢመዘገቡም፣ በመጠለያ ያሉት ተፈናቃዮች እንጂ እነርሱ እስካሁን እርዳታ እንዳላገኙ አብራርተዋል።
ተፈናቃዮቹ እስካሁን ድረስ ከአንዳንድ ቤተሰቦቻቸው በሚላክላቸው የብር ድጋፍ ቤት ተከራይተውና የዕለት ምግባቸውን ገዝተው ሲኖሩ የቆዩ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ምንም አይነት የድጋፍ ምንጪ ስለሌላቸው ከሕፃናት ልጆቻቸው ጋር የመጠለያና የምግብ ዕጥረት እንደገጠማቸው ነው ለአዲስ ማለዳ ያስረዱት።
“አፍና ዘመድ ያላቸው ግለሰቦች ከኹለትና ሦስት ጊዜ በላይ ከምግብ ጀምሮ እስከ የቁሳቁስ ዕርዳታ አግኝተዋል’’ በማለት ለአዲስ ማለዳ የገለጹት ዘውዲቱ አያሌው የተባሉት ተፈናቃይ፣ እስካሁን አንድ ጊዜ ብቻ የሩዝ ዕርዳታ ቢያገኙም ከዚያ ወዲህ ሌሎች በመጠለያ ያሉት ሰዎች የሚያገኙትን ዕርዳታ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በመጠለያ ጣቢያዎች ከሚገኙት ግለሰቦች ይልቅ ተከራይተው የሚኖሩ ብዙ ወጪ ይኖርባቸዋል የሚሉት ዘውዲቱ፣ በመጠለያ ያሉ ከመንግሥትም ሆነ ከበጎ አድራጊዎች በሚደረግላቸው ዕርዳታ ወደ ቀያቸው ቢመለሱ እንኳን እንዳይቸግራቸው ሙሉ የቤት ዕቃ ያሟሉ ብዙ ግለሰቦች እንዳሉ እና በተቃራኒው እነሱ ግን ለኪራይ የሚከፈል ብርና ለምግብ የሚሆን በቂ ዕርዳታ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ዘውዲቱ አያይዘውም፣ “ከመጠለያ ውጭ ያሉ ተፈናቃዮችም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፤ ተከራይተዋል ማለት ገቢ አላቸው ማለት አይደለምና አስተባባሪዎች ይህን ግምት ውስጥ እንዲያስገቡልን እንጠይቃለን’’ ሲሉ ነው ሐሳባቸውን ያስረዱት።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደተናገሩት ከሆነ፣ ዕርዳታ ለማግኘት በደሴ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ መጠለያዎች በተደጋጋሚ ቢመላለሱም፣ ያገኙት ትርፍ ’’ድካምና ሕመም’’ እንጅ በመጠለያ ጣቢያዎቹ እንደሚገኙት ተፈናቃዮች ተመሳሳይ ድጋፍ እንዳልሆነ ነው።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ከመርሳ ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ቤት ተከራይተው የሚገኙ ሌላኛዋ ግለስብ፤ “ዕርዳታ አለ ተብሎ ልጄን አዝዬ ጧት ተነስቼ ሔድኩ፤ ሙሉ ቀን ፀሐይና ንፋስ ሲፈራረቁብኝ ቆይቼ ተመለስኩ። ሌላ አማራጭ ስለሌለኝ በማግስቱ ተመልሼ ብሔድም ያገኘሁት ትርፍ ሕመም ነው። አሁን ላይ እራሴን እያዞረ እየደፋኝ ነው’’ ሲሉ ነው የተናገሩት።
አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ከደሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ ሰይድ የሱፍ ጋር በነበራት ቆይታ አለ የተባለውን “አድሎዓዊ” አሠራር ለማረጋገጥ ችላለች።
በደሴ ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከሦስትና አራት ጊዜ በላይ ዕርዳታ የተደረገበት ኹኔታ እንዳለ የጠቆሙት ምክትል ከንቲባው፣ በየአካባቢው ያሉት መዝጋቢዎች የሚያውቋቸውን ብቻ ደጋግመው ስለሚመዘግቡ የዕርዳታ ክፍፍሉ አስቸጋሪ እንደሆነባቸውና በተለይም ከመርሳና ከቆቦ ለመጡት ተፈናቃዮች ዕርዳታ በሚደረግበት ወቅት ችግር እንደገጠማቸው ገልጸዋል።
አክለውም፣ በደሴ ከተማ ተጠልለውና ተከራይተው የሚኖሩትን ጨምሮ ከኹለት መቶ 80 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች እንዳሉ ገልጸው፣ በየዕለቱ ቁጥራቸው እየጨመረ በመምጣቱ ትርምስ ስላለ እርዳታውን በትክክል ለማዳረስ መቸገራቸውን አብራርተዋል።
ከሰይድ የሱፍ አስተያየት አዲስ ማለዳ መረዳት የቻለችው ድጋፉ የሚሰጠው በምዝገባ ቢሆንም ተመዝግበው ድጋፍ ያላገኙ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ነው። ምክትል ከንቲባው አክለውም መዝጋቢዎች እንደፈለጉ መዝግበው ስለሚያቀርቡ እና በተፈናቃዮች መካከል መተዛዘን ስለሌለ አቅም የሌላቸው አዛዉንቶችም ጭምር ዕርዳታ ሳያገኙ እንደሚቀሩ ነው የጠቆሙት።
ምክትል ከንቲባው ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት ከምንም በላይ መተዛዘን ያስፈልጋል በማለት ነው ለአዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት።
ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014



