የባሕላዊ ዳንስ ማንሰራራት እና ዕጣ ፈንታ

0
787

ባሕላዊ ዳንስ የኢትዮጵያውን የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ በሰፊው ከሚተገበር ተግባራት መካከል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይሁን እንጂ፤ ይህ ለብዙ ሺሕ ዓመታት የቆየ ልማድ ቢሆንም፤ እንደ ጥበብ ተቆጥሮ መተግበር ከጀመረ፤ አንድ ምዕተ ዓመት አልሞላውም።

በርግጥ፤ ከ1920ዎቹ አንስቶ ቴአትር ቤቶች ባሕላዊ ዳንሶችን ለተለያዩ የዓለም ክፍሎች በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው። ከዚያም በኋላ፤ በ1980ዎቹ እና 1990ዎቹ፤ ይህን ልማድ ለሕዝብ እና ለተለያዩ አገራት ማስተዋወቁንና ማስተማሩን ቀጥለውበት ነበረ። ይህ ግን ሊቆይ አልቻለም።

በተለይ ባለፉት 15 ዓመታት፤ የቴአትር ቤቶች ሚና በከፍተኛ ሁኔታ ሲወርድ ተስተውሏል። ይባስ ብሎ፤ ለባሕላዊ ዳንስ ሙያ ትልቅ አስተዋፅዖ የነበራቸው እንደ ሜጋ አምፊ ቴአትር ቤቶች ሲዘጉ፤ ሌሎቹ ደግሞ፤ የቀድሞ ተግባራቸውን ከመዘንጋትም አልፈው ትተውታል ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ይሁን እንጂ፤ እንደ ፌስቡክ ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ምስጋና ይገባቸውና፤ ባሕላዊ ዳንስን እንደ ሙያ መቀበል ጋር ተያይዞ ለውጥ ተስተውሏል። ይህንንም ተከትሎ፤ ብዙዎች ሙያውን በመማር የገቢ ማስገኛ መንገድ እያደረጉት ይገኛል።

በተጨማሪም፤ በፊት በጥቂት መዝናኛ ቦታዎች ላይ ይደረግ ከነበረው ለየት ባለ መልኩ፤ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሬስቶራንቶችና ባሮች ሲተገበር በስፋት ይስተዋላል። ለ 20 ዓመታት በባሕላዊ ዳንስሙያ ልምድ ያካበተችው ሜሮን ፀጋዬ፤ ይህን ለውጥ ከተረዱት መካከል ትመደባለች። ከዛሬ አምስት ዓመታት አንስቶ ባሕላዊ ዳንስን ማስተማር የጀመረችው ሜሮን፤ ‹‹የሙያውን ማደግ ተከትሎ የተማሪዎቿ ቁጥር በየዓመቱ ለውጥ እያሳየ መምጣቱን›› ትገልፃለች።

በኅብረተሰቡ ዘንድ ባሕላዊ ዳንስን እንደ ሙያ እንዲቀበል የማሳመን ሥራ ቢኖሩም፤ ስለ ሙያው ያለው አመለካከት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ይታያል። ኢትዮጵያ ካሏት 80 በላይ ባሕላዊ ዳንሶች መካከል በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል በበለጠ የሚተገበረውን እስክስታ ላይ ሙያዋን ያዳበረችው ሜሮን፤ ባሕላዊ ዳንሶችን የለመደችው ከልጅነት ጊዜ አንስቶ በአካባቢዋ እና በተለያዩ መድረኮች ላይ በማሳየት ነበረ።

ለእርሷ ብቻ ሳይሆን፤ ለሌሎች ዳንሰኞች በተለያዩ የዓለም አገራት ዝና ያተረፈው እስክስታ ለባሕላዊ ዳንስ ሙያ መስፋፋት ትልቅ ሚና ነበረው። ይሁን እንጂ፤ አሁንም ሆነ በፊት፤ ይህንን ሙያ የበለጠ ከማሳደግ ይልቅ፤ የቱሪስት አይን መሳቢያ መንገድ ብቻ አድርጎ የመውሰድ ችግር እንዳለ ባለሙያዎች ያነሳሉ። ባለሙያው መልሰው መንበሩ ለዚህ ምስክር ነው።

የባሕላዊ ዳንስ አስተማሪ ሆኖ ለኹለት ዐሥር ዓመታተት የዘለቀው መለሰው፤ ሙያው ለቱሪስቶች እና ለሕዝብ መዝናኛነት ባለፈ ለባለሙያዎች በባሮች እና የመዝናኛ ተቋማት የሚከፈለው ክፍያ አናሳ መሆን ሙያው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መምጣቱን ይገልፃሉ። ሙያው የተከበረ መሆን ሲገባው እንዲሁም ለባለሙያዎች በቂ ገቢ የሚያስገኝ መሆን ቢኖርበትም፤ አንድ ዳንሰኛ በወር ከ 2 ሺሕ ብር የዘለለ አለማግኘቱ የወደፊቱን የሙያውን ዕድገት አጠራጣሪ ያደርገዋል ይላል መለሰው።

የፈንድቃ ባሕል ማዕከል ባለቤት እና መሥራች የሆኑት መላኩ በላይ በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። በድሮ ጊዜ ባሕላዊ ዳንስን እንደ ተሰጥኦ እና ሙያ ክፍተት መኖሩን ያወሱት መላኩ፤ ‹‹በቅርቡ ዓመታት የታየውን ለውጥ ተከትሎ ሙያው የገቢ ምንጭ ሆኖ መምጣቱን›› ይገልጻሉ። ይህ ቢሆንም፤ ሙያው ግን ከችግር ነፃ እንዳልሆነ መላኩ ያነሳሉ። ለአብነትም፤ መንግሥት ሙያውን ለማሳደግ የሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን መላኩ ያሳያል። የአዲስ አበባ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ዋና ኃላፊ የሆኑት ነብዩ ባዬ በዚሀ ሐሳብ ይስማማሉ።

‹‹ሰዎች ባሕላዊ ዳንስ ለመመልከት መሽቶ ባርና ሬስቶራንቶች እስኪከፈቱ መጠበቃቸው፤ ሙያውን ከመዝናኛነት ባለፈ ሚና የዘለለ እንደለሌለው አስመስሎታል›› ይላሉ ነብዩ። ለዚህም እንደ ምክንያት፤ ‹‹ከምዕራቡ የዓለም ክፍል ያልተቀላቀለ፤ የአገራችን የባሕላዊ ዳንስ ማዕከል አለመኖርን›› ነብዩ ያነሳሉ።

ይህንንና መሰል ውስብስብ ችግሮች ሙያውን ለማሳደግ እንቅፋት ቢሆንም፤ ትንሽም መንሰራራት ማሳየቱ ለጊዜውም ቢሆንም ከምንም ይሻላል የሚሉት ባለሙያዎች፤ ባሕላዊ ዳንሶችን የሚያጠና እና ለቀጣይ ትውልድ ሳይበረዝ የሚያስተላልፍ ተቋም መኖር አለበት ይላሉ።

ከአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት ‹ኢትየጵያን ቢዝነስ ሪቪው› ተተርጉሞ ለአዲስ ማለዳ ማለዳ በሚመች መልኩ የቀረበ። ሳምሶን ብርሃኔ ለጽሑፉ መዳበር አስተዋጽኦ አድርጓል።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here