አራተኛው ዙር የሕዝብና ቤት ቆጠራ መጋቢት 29 ይጀምራል

0
575

ብሔራዊ የፕላንና ልማት ኮሚሽን እና የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ እንዳስታወቁት ቆጠራው ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 20/2011 የሚከናወን ነው።
አሁን ላይ ለቆጠራው የሚያስፈልገው የዝግጅት ሥራ መጠናቀቁም ተገልጿል።

አራተኛው ዙር ቆጠራ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሒደቶች የኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀሙ ባሻገር በቆጠራው ሒደት አምስት ቋንቋዎች ጥቅም ላይ የሚውሉበት በመሆኑ የተለየ ያደርገዋል ተብሏል።

በቋንቋ በኩል የሚገጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ መጠይቆች በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ አፋርኛ እና ሶማሌኛ እንዲዘጋጁ ተደርጓል።
ከዚህ ቀደም በነበሩ ቆጠራዎች ከመረጃ ሐቀኝነት ጋር ተያይዞ ዛሬም ድረስ የዘለቁ ክርክሮች አሉ። በዘንድሮው የቆጠራ ሒደት ችግሮች ቢከሰቱ ቶሎ ማስተካከል የሚያስችል የበይነ መረብ ቁጥጥር ስርዓት እንደሚተገበር ተነግሯል።

ከዚህ ቀደም የነበረው ቆጠራ በአርብቶ አደር እና በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ከተያዘው የመደበኛ ጊዜ ዘግይቶ የሚደረግ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን በዚህኛው ዙር ግን በተመሳሳይ ጊዜ ለማስኬድ ዝግጅት መጠናቀቁ ተወስቷል።

የሕዝብና ቤት ቆጠራ በየ10 ዓመቱ የሚካሄድ መሆኑን ተከትሎ አራተኛው ዙር መርሀ ግብር ባለፈው 2010 መካሄድ የነበረበት ቢሆንም፣ በነበሩ ችግሮች በአንድ ዓመት እንዲዘገይ የቀረበውን ሐሳብ የሕዝብ የተወካዮች ምክር ቤት በማጽደቁ ቆጠራው ወደ 2011 መራዘሙ አይዘነጋም።

ለሕዝብና ቤት ቆጠራው ማሳለጫነት ታስበው የተገዙ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ዋጋና የግዥ ሒደት ሲያወዛግቡ እንደነበር ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here