አንጋፋው የፊልም ሰሪ ኃይሌ ገሪማ የኦስካር ሽልማትን በመስጠት የሚታወቀው ‘ዘ አካዳሚ ኦፍ ሞሽን ፒክቸር አርትስ ኤንድ ሳይንስስ’ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን ሙዝየም መክፈቻ በማስመልከት ባዘጋጀው መድረክ ላይ ከፍተኛ ሽልማቱን አበርክቶላቸዋል።
በጥቁሮች የሲኒማ ታሪክ ላይ ከፍተኛ ስፍራ ያላቸው ኢትዮጵያዊው ኃይሌ ገሪማ ‘ዘ አካዳሚ ሙዝየም ኦፍ ሞሺን ፒክቸርስ’ የቫንቴጅ ሽልማት የመጀመሪያው ተሸላሚ መሆናቸውም ታውቋል።
እንደ ‘ሳንኮፋ’ እና ‘አሽስ ኤንድ ኤምበርስ’ ከሚባሉ ምርጥ ፊልሞች በስተጀርባ ያሉት አንጋፋው የፊልም ዳይሬክተር ኃይሌ የሎስ አንጀለሱ ሙዝየም መክፈቻን አስመልክቶ ቅዳሜ ዕለት ባደረገው ሥነ ሥርዓት ላይ ነው ሸልማቱን የሰጣቸው።
ኢትዮጵያዊው ኃይሌ ገሪማ ‘ቫንቴጅ’ የተባለውን ሽልማት የተሸለሙበትን ምክንያት አስመልክቶ ሙዝየሙ እንዳስታወቀው “በሲኒማ ዙሪያ ዋነኛ ትርክቶችን በመገዳደርና አውድ በማስያዝ የረዳ አርቲስትና ምሁር” በሚል እንዳከበራቸው አስታውቋል።
ነፃነታቸውን ያላስነኩና ባለራዕዩ ዳይሬክተር ኃይሌ ገሪማ ጥናታዊ፣ ታሪካዊና፣ ልብወለድ ፊልሞች ውስጥ በመመላለስ ለአምስት አስርት ዓመታት ያህል ፓን አፍሪካዊነትና የጋራ ትውስታን በፊልማቸው መግለፅ ችለዋልም ሲል ሙዝየሙ በድረ-ገጹ ባሰፈረው ማስታወሻ አሞካሽቷቸዋል።
እንዲሁም ለበርካታ አስርት ዓመታት በዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ የፊልም ፕሮፌሰር ሆነው በፊልሙ ዘርፍ ስመ ጥር የተባሉ ሲኒማቶግራፈሮችን ማፍራት ችለዋል።
ከእነዚህም ውስጥ ማሊክ ሰይድ፣ ብራድፎርድ ያንግ እና አርተር ጃፋ ይጠቀሳሉ።
ከሙዝየሙ ድረገፅ በተገኘውም መረጃ መሠረት የኃይሌ ታሪክ ምጥቀትና የሲኒማ ጥልቀት የታየባቸው በርካታ ፊልሞች እንዲሁም እሳቸው ያስተማሯቸውና ተፅእኖ ያሳረፉባቸው ፊልሞች ለዕይታ ይቀርባሉ።
ሙዝየሙ ዛሬ መስከረም 20/2014 ለሕዝብ ክፍት የሚደረግ ሲሆን ኃይሌ ከሠሯቸው ፊልሞች መካከልም ምርት ሦስት ሺህ፣ ሳንኮፋ፣ ጤዛ፣ ቡሽ ማማ፣ አሽስ ኤንድ ኤምበርስ፣ አድዋ፣ ዊልሚንግተን 10- ዩኤስኤ 10,000 እና ሌሎቹም ፊልሞቻቸው ይታያሉ።
በዚህ ወር የኃይሌ ገሪማ ሳንኮፋ ፊልም የማርቲን ሉተር ኪንግን ትግል የሚያሳየውን ‘ሴልማ’ንና ሌሎች ፊልሞችን በመስራት ታዋቂነት ባተረፈችው የፊልም ባለሙያ ኤቫ ዱቨርኔይ ኩባንያ በአራይ አማካኝነት በኔትፍሊክስ ለዕይታ እንደሚቀርብ ቢቢሲ ዘግቧል።
ከኃይሌ በተጨማሪ ጣሊያናዊቷን የፊልም ባለሙያ ሶፊያ ሎሬንን ሙዚየሙ ‘ቪዥናሪ አዋርድ’ የተባለ ሽልማቱን አበርክቶላታል።
ጣሊያናዊቷ ሶፊያ የሁለት ጊዜ የኦስካር ሽልማት አሸናፊ ስትሆን ሙዝየሙም “ሥራዋ የሲኒማ ጥበብን በማላቅ ላደረገችው አስተዋፅኦ” መሸለሙን አስታውቋል።
የአካዳሚው ሙዚየም ዳይሬክተር እና ፕሬዝዳንት ቢል ክሬመር “ለኃይሌ ገሪማም ሆነ ለሶፊያ ሎረን ተፅእኖ ፈጣሪ እና አነቃቂ ሥነ ጥበባት እውቅና መስጠት ክብር ነው” ብለዋል።



