ምርጫው ‘በጊዜው ይካሄድ ወይስ አይካሄድ’ የሚለው ሊጠና ነው

0
579

ዓለም አቀፉ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ኢንስቲትዩት ከአገር በቀል አጋሮቹ ጋር በመሆን በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በ2012 ስለሚካሔደው ምርጫ ያላቸውን አመለካከት በተመለከት ጥናት ለማድረግ ዝግጅት ላይ መሆኑን ምንጮች ገለፁ።

ምርጫው በጊዜው ይካሄድ ወይስ አይካሄድ የሚለውን ለማወቅ ይረዳል የተባለው ጥናት እንዲካሄድ ድርጅቱ ኢትዮጵያ ከሚገኙ አጋሮቹ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱ ታውቋል። በተለይም፤ ቀጣዩን አገር ዐቀፍ ምርጫ በተመለከተ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ምሁራን ኹለት ዓይነት አቋም እንደማንፀባርቃቸው፤ ጥናቱን የበለጠ አስፈላጊ እንደሚያደርገው ኢንስቲትዩቱ ጠቁሟል።

ጥናቱን ለማካሄድ በባለፈው ወር ጨረታ ያወጣው ድርጅቱ፤ ዜጎች በአገሪቷ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ በተመለከተ ያላቸውን አመለካከት ለማወቅ ጥናቱ ወሳኝ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ ከተቋቋመ ከአንድ ዓመት በኋላ ጀምሮ እስካሁን አምስት ተከታታይ ምርጫዎች ጊዚያቸውን ጠብቆ በ1987፣ 1992፣ 1997፣ 2002 እና 2007 ተካሒደዋል። ይሁን እንጂ የምርጫዎቹ ተአማኒነት በሕዝብም ሆነ በተቃዋሚዎች ዘንድ አናሳ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህንን ለማስቀረት ትልቅ ሚና ይጫወታል የተባለው ጥናቱ፤ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎቸ በሚኖሩ 1500 ዕድሜያቸው ለምርጫ የደረሱ ሰዎች ላይ የሚከናወን ሲሆን፤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከመጋቢት 2019 እስከ ጥቅምት 31 2019 ድረስ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ ጎዳና እያመራች መሆኑን የገለፀው ተቋሙ ጥናቱ ለውጡን በመደገፍ አኳያም ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ግልጿል።

ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ከማጎልበት አኳያ ብዙ የሚሠሩ ሥራዎችን ከመጠቆም አንፃር ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ያለው ኢንስቲትዩቱ፤ ግልፅ እና ተጠያቂነት ያለበት ምርጫ ለማድረግ የሕዝብ ፍላጎት ማወቁ ወሳኝ ስለሆነ ጥናቱ እንደ ግብዓትነት ለመንግሥትም ሆነ ለሌሎች ተቋሞች እንደሚያገለግል ጠቁሟል።

ጥናቱን ለማከናወን በአሁን ሰዓት አጥኚ ድርጅት መረጣ ላይ የሆነው ኢንስቲትዩቱ፤ አዲስ አበባ እና ዋሽንግተን ዲሲ ያሉት ሠራተኞቹ ጥናቱን እንደሚከታተሉት ገልጿል። በተጨማሪም የጨረታው አሸናፊ የሚሆነው ድርጅት ጥናቱን ለማከናወን በአማርኛ፣ በእንግሊዘኛ እና በኦሮሚኛ ቋንቋዎች መጠይቅ ማዘጋጀት እንዳለበት ታውቋል።

የሚመረጠውም ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ማግኘት እንዳለበት የገለፀው ድርጅቱ፤ የትኩረት ቡድን ውይይትም የጥናቱ አካል እንደሚሆን መታወቅ ተችሏል። በተጨማሪም፤ የጨረታው አሸናፊን በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ይፋ የሚያደረገው ተቋሙ፤ የጥናቱን ወጪ ሙሉ ለሙሉ እንደሚሸፍን ምንጮች ገልጸዋል።
የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ኢንስቲትዩት ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሲሆን ከተመሰረተ 36 ዓመታት ሆኖታል። በምሥራቅ አፍሪካ ኬኒያ ላይ ቢሮውን ከከፈተ ዓመታት የሆነው ተቋሙ፤ ከተመሰረተ ጀምሮ የፖለቲካ እና የሲቪክ ድርጅቶችን ማጠናከር፣ ምርጫን በተለያዩ አገራት ላይ በተገቢ መልኩ እንዲከናወን በመርዳት እና መንግሥታት ግልጽነት እና ተጠያቂነትን እንዲያጎለብቱ ጥናት እና የተለያዩ ምርምሮች በማድረግ ይታወቃል።

ከሳምንት በፊት አዲስ ማለዳ በወጣችው ሐተታ፤ ምርጫው በጊዜ ገደቡ መሠረት መካሔድ አለበት እንዲሁም በተቃራኒው ደግሞ ጊዜው ቢራዘም ይሻላል የሚሉ ፖለቲከኞች እንዳሉ መጠቆሟ አይዘነጋም። የኦፌኮ ሊቀመንበር እና የመድረክ ከፍተኛ አመራር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) “ምርጫው በተሻለ ፍጥነት መካሔድ” እንዳለበት ሲያስረዱ “27 ዓመታት በአምባገነንነት ሲመራ የነበረው ኢሕአዴግ አሁን ካለንበት የበለጠ አመቺ ጊዜ ሊፈጥር አይችልም” በማለት ከአዲስ ማለዳ “ምርጫው የተሻለ ጊዜ እስኪመጣ ይራዘም ወይ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተው ነበር።

በተመሳሳይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሥራ አስፈፃሚ አባልና የፓርቲው የሕግ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ጥበበ ሰይፈ ምርጫው በሕግ በተደነገገው መሠረት በየአምስት ዓመቱ መካሔድ አለበት የሚል መከራከሪያ ነጥብ አንስተው ነበር።

በሌላ በኩል የአርበኞች ግንቦት 7 የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ኤፍሬም ማዴቦ ፓርቲያቸው ምርጫው መራዘም አለበት የሚል አቋም እንዳለው ሲገልጹ “ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ለማስፈፀም የሚችሉ ተቋማት በሌሉበት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንደልብ ተዘዋውሮ የፖለቲካ ሥራ መሥራትና ሕዝብ ማደራጀት በማይቻልበት እንዲሁም በበርካታ የአገሪቱ ክፍል የሰላምና መረጋጋት እጦት ባለበት ሁኔታ ምርጫው መካሔድ የለበትም” በማለት መግለፃቸው አይዘነጋም።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here