የ40/60 ተመዝጋቢዎች ተጨማሪ ክፍያ እንደሚጠበቅባቸው ተገለፀ

0
459

40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማድረስ በተገባው ውል መሰረት የቤቶቹን ዋጋ ሙሉ በሙሉ የከፈሉ ሰዎች ተጨማሪ ክፍያ እንደሚጠበቅባቸው ተገለፀ። በግንባታ ግብዓት ዋጋ መናር ምክንያት የቤቶች ዋጋ ላይ ጭማሪ በማሳየቱ በአሁኑ ወቅት መቶ በመቶ ክፍያ የፈፀመ ሰው እንደሌለ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታውቋል። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የግማሽ ዓመት ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት ሚኒስትሩ ጃንጥራር አባይ እንደገለፁት መጀመሪያ ላይ መመሪያው ሲዘጋጅ የቤቱን ጠቅላላ ዋጋ መቶ በመቶ የቆጠበ ቅድሚያ እንደሚሰጠው የሚገልፅ መመሪያ እንዳለ ገልፀው፤ አሁን ላይ የቤቶችን ዋጋ ጭማሪ ተመርኩዞ ማንም ግለሰብ የሙሉ ክፍያ ቁጠባ የፈፀመ እንደሌለ አስታውቀዋል።

ከሚኒስትሩ መግለጫ መረዳት እንደተቻለው ከጅምሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ደንበኞች ውል ሲፈፅሙ 3 ሺሕ 300 ብር ገደማ በካሬ ታስቦ የነበረው የቤቶች ዋጋ አሁን ላይ በግንባታዎች መጓተት ምክንያት የዋጋ ንረት በማጋጠሙ የቤቶች ዋጋ በካሬ ወደ 4918 ብር ማሻቀቡን ለማወቅ ተችሏል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ጃንጥራር ሲገልፁ የዋጋ ልዩነቱን በሚመለከት ከደንበኞች በኩል ቅሬታ ካለ ከንግድ ባንክ ጋር በተገባው ውል መሰረት መፍታት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሚኒስትሩን መግለጫ ተከትሎ ከምክር ቤቱ ጥያቄ የተነሳ ሲሆን ዜጎች መንግሥትን አምነው ውል ፈፅመው እንዲህ ሊደረጉ አይገባም የሚል አስተያየት ከምክር ቤት አባል ጌታቸው መለሰ ተሰምቷል። ጌታቸው አያይዘውም በውጭ አገራት የሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን በኢምባሲዎችና በቆንስላ መስሪያ ቤቶች ተመዝግበው እየተጠባበቁ ባሉበት ሁኔታ እንዲህ በመንግሥት ላይ እምነት የሚያሳጣ ተግባር መፈፀም በዲያስፖራ ትረስት ፈንድ አፈፃፀም ላይ ትልቅ ችግር ይፈጥራል ብለዋል። ከምክር ቤቱ ለተነሱት አስተያየትና ጥያቄዎች ጃንጥራር ምላሽ ሲሰጡ ደንበኞች ከንግድ ባንክ ጋር ውል የፈፀሙት በመነሻ ዋጋው ሒሳብ እንጂ በማስረከቢያ ዋጋ እንዳለሆነ ገልፀው የተደረገው የዋጋ ማሻሻያ ሕጋዊና የመንግሥትን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት አለመሆኑን ለምክር ቤቱ አሰረድተዋል።

ጃንጥራር በማጠቃለያ ንግግራቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ተገንብተው ወደ ተጠቃሚዎች ሲከፋፈሉ ሙሉ ክፍያ የቆጠበ ባለመኖሩ ሁሉም ተመዝጋቢዎች ፍትሓዊ በሆነ የዕጣ አወጣጥ ስርዓት ቤቶችን እንደሚረከቡ ጨምረው ገልፀዋል። ሚኒስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ በግማሽ ዓመቱ ተጠናቀዋል የተባሉትን 17 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የከተማ ልማት ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ቋሚ ኮሚቴ በመስክ ምልከታው ወቅት ለመታዘብ እንደቻለው ገና በርካታ መሟላት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉና ለኑሮ አመቺ እንዳልሆኑ ገምግሟል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ደግሞ በበኩሉ የአሳንሰር ገጠማ ብቻ እንደሚቀረው እና ቀሪዎችን ጥቃቅን የማጠቃለያ ሥራዎችን ተጠቃሚዎች እንዲሰሩ እንደሚያደርግና በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ 30ሺሕ የ40/60 መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች እንደሚያከፋፍል አስታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here