የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አስተዳዳሪ ታገዱ

0
1019

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩንቨርሲቲ ኮሌጅን ለኹለት ዐሥርት ዓመታት የመሩት ብጹእ አቡነ ጢሞቴዎስ በተማሪዎች የተነሳውን ተቃውሞን ተከትሎ ከሥልጣን መታገዳቸውን አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ አመላከተ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽህፈት ቤት ጥር 27/2011 በፃፈው ደብዳቤ፤ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች አማካኝነት የቀረበ አቤቱታን መሠረት ባደረገ የማጣራት ሥራ አቡነ ጢሞቴዎስ ከአስተዳደሪነት እንዲነሱ መወሰኑን ገልጿል።
ከ1990 ጀምሮ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ዲን እና የበላይ ኃላፊ በመሆን ያገለገሉት አቡነ ጢሞቴዎስ፤ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ተማሪዎች ላለፉት ሦስት ወራት የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለባቸው ተገልፆ ቅሬታ ቀረቦባቸው ነበር።

በዚህም የተነሳ እስከ ጥር 29/ 2011 ድረስ የመደበኛ መርሃ ግብር ተማሪዎች አድማ ምክንያት በኮሌጁ ለሦስት ወራት ትምህርት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፤ ኮሌጁ የገነባቸውና ያከራያችው ሕንፃዎች ክፍል ብዛት በውል አለመታወቁ፤ የተከራዩት በሕግ አግባብም በውል መከራየታቸውና አለመከራየታቸው የተጣራ አለመሆኑና ኮሌጁ ኦዲት አለመደረጉ አስተዳደሩ ከተነሱባቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች መካከል ናቸው።

በተጨማሪም፤ የተማሪዎች ማደሪያ የሆኑ ክፍሎች ሳይቀሩ፤ ከተሰሩበት ዓላማ ውጪ ለንግድ ሥራ አስተዳዳሪው ማከራየታቸው አግባብ እንዳልሆነ ቅሬታ ያቀረቡት ተማሪዎቹ፤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁን በበላይነት ሲመሩ የነበሩት አቡነ ጢሞቴዎስ ተቋሙን ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ መምራት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር፤ ዘጠኝ የሚሆኑት የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ አስተዳደሮች ምክትል አካዳሚክ ዲን የሆኑትን መምህር ግርማ ባቱን ጨምሮ፤ የሥራ ብቃታቸው የወረደ መሆኑን በመግለፅ፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲነሱ የጠየቁት ተማሪዎቹ፤ ጥያቄያቸው በሲኖዶሱ ተቀባይነት ማግኘቱን ምንጮች ገልፀዋል።

ሲኖዶሱ ባደረገው ማጣራት፤ የተማሪዎቹን ቅሬታ ከመቀበል ባሻገር፤ በታኅሣሥ 4/ 2011 ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት፤ ለመማር ማስተማር ተግባር እንዲውል በዋና መሥሪያ ቤቱ የሚፈቀደው በጀት ለሌላ ተግባር እንዲውል መደረጉ አግባብ አይደለም በማለት፤ በየዓመቱ ለ204 እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ተማሪዎች የሚሆን በጀት የሚፈቀድ ቢሆንም፤ ገንዘቡ ግን ለ145 ለሚሆኑ ተማሪዎች የሚውል መሆኑ ስለተረጋገጠ ቀሪውን በሚመለከት ማጣራት እንዲደረግ ወስኗል።

ይህንን እና ሌሎች ቅሬታዎችን ያጤነው ሲኖዶሱ፤ ጥር 8/ 2011 በወሰነው ውሳኔ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የበላይ ጠባቂና ዲን በመሆን ኮሌጁን ያገለገሉት አቡነ ጢሞቴዎስ ምልዓተ ጉባኤ እስኪሟላ፤ ማለትም ከውጭም ሆነ አገር ውስጥ ያሉ ጳጳሳት ውሳኔ እስኪወስኑ እና ጉዳያቸው እስኪታይ በኮሌጁ ማንኛውም የአስተዳደር ሥራ ውስጥ እንዳይገቡ አግዷቸዋል፤ በምትካቸውም የኮሌጁ ጊዜያዊ ምክትል የአካዳሚ ጉዳዮች ዲን ቀሲስ መብራቱ ኪሮስ (ዶ/ር) ኮሌጁን እንዲያስተዳድሩ ሲኖዶሱ የወሰነ ሲሆን፤ መምህር ፍርድአወቅ አለማየሁን ደግሞ የኮሌጁ ጊዜያዊ ምክትል አስተዳደር ዲን ሆነው እንዲሠሩ ወስኗል።

የሲኖዶሱን ውሳኔ በፅኑ የተቃወሙት አቡነ ጢሞቴዎስ በበኩላቸው፤ የቀረበባቸውን ቅሬታ ውሸት ነው ሲሉ አጣጥለዋል። በተማሪዎችም ሆነ በአጣሪ ኮሚቴው የቀረበው ሪፖርት ከቤተ-ክህነት ጋር ባላቸው አለመስማማት የተፈጠረ ነገር እንጂ፤ ትክክለኛ ነው ብለው እንደማያምኑ አቡነ ጢሞቴዎስ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። ይሁን እንጂ፤ ሲኖዶሱ አስተዳደር ሥራ ውስጥ ሳይገቡ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የበላይ ጠባቂ ሆነው እንዲያገለግሉ፤ ማለትም ቡራኬ ከመስጠት ባሻገር ሥልጣን እንዳይኖራቸው አግዷቸዋል።

ከ50 ዓመታት በላይ የቆየው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አዲስ ተማሪዎች የመቀበል አቅሙ በዓመት 204 መደበኛ ተማዎች እንደሆነ መረጃዎች ቢያሳዩም፤ ባለፈው ዓመት የተቀበላቸው አዲስ ተማሪዎች ብዛት 25 ብቻ ነበር። በአጠቃላይ 204 የመደበኛ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ተማሪዎች ያሉት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በሥነ መለኮት እስከ በማስተርስ ዲግሪ ደረጃ ያስተምራል።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here