ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ስድስት ወራት የሰበሰበው ገቢ በ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ቅናሽ ማሳየቱ ታወቀ። በ2011 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ለማግኘት ከታቀደው 20 ነጥብ 8 ቢሊየን አጠቃላይ ገቢ ውስጥ ፤ 16 ነጥብ 7 ብር በማስገባት የእቅዱን 80 በመቶ ማከናወኑን ድርጅቱ አስታውቋል።
እቅዱን በማሳካት በኩል ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር አሁን ላይ በቴሌኮሙ በኩል መቀዛቀዝ ታይቷል።
ከገቢው ውስጥ 63 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆነውን ከሞባይል አገልግሎት የሰበሰበው ተቋሙ፤ ከዳታ እና ኢንተርኔት 28 ነጥብ 7 በመቶ እና ከዓለም ዐቀፍ ጥሪዎች 5 ነጥብ 5 በመቶ ገቢ ማስገባቱን ለማወቅ ተችሏል። ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከፍተኛ የለውጥ ሥራዎች ላይ ተጠምዶ እንደነበር ያስታወቀው ቴሌኮሙ ፤ የአገልግሎቱን ቀጣይነት የማረጋገጥ ሥራዎችና ለረጅም ጊዜ ሳይፈቱ የቆዩ ከደንበኞች ጋር የተያያዙ እንዲሁም የተቋሙ ሥራ ቀጣይነት ላይ እልባት በመስጠት አበረታች እንቅስቃሴ ማድረጉን አስታውቋል።
በተጨማሪም ተቋሙ ከነበረበት አጠቃላይ ስጋት ተላቆ ወደ ተረጋጋ የአገልግሎት አሰጣጥ ተግባሩ ለማስገባት ብዙ ሥራዎች መሥራቱን የጠቀሰው ቴሌኮሙ፤ በበጀት ዓመቱ የተጠቃሚ ብዛትን 45 ሚሊዮን ማድረሱን አስታውቋል። ይህም ከዚህ ቀደም በተቋሙ ኃላፊዎች ይነገር ከነበረው እና አገልግሎት የማይሰጡ ቁጥሮችን ጨምሮ ይነገር ከነበረው የተጋነነ የደንበኞች ቁጥር የተለየ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በ2011 መጨረሻ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር 65 ነጥብ 7 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ መነገሩን ያወሳው ኢትዮ ቴሌኮም፤ በሪፖርቱ ላይ ተካተው የቀረቡት ደንበኞች በሲስተም ላይ ያልተመዘገቡ በመሆናቸው ቁጥሩን በ30 ነጥብ 2 ሚሊዮን ከፍ እንዲል ማድረጉንም ጨምሮ አስታውቋል።
በዝርዝር ሲቀመጥ፤ የተንቀሳቃሽ ስልክ ድምጽ ተጠቃሚዎች 39 ነጥብ 5 ሚሊዮን የደረሱ ሲሆን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 19 ነጥብ 5 ሚሊዮን መሆኑን ተቋሙ ገልጿል። በዚህም መሰረት የአጠቃላይ የቴሌኮም ስርፀት በአገር ዐቀፍ ደረጃ 43 ደርሷል ሲል ተቋሙ ይገልፃል።
በመጀመሪያው ስድስት ወራት ውስጥ ከፍተኛ የታሪፍ ቅናሽ ያደረገው ተቋሙ፤ ወደ 11 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱ የተገለፀ ሲሆን ይህም የዕቅዱ 91 በመቶ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ቅናሽ ታይቶበታል።
በተጨማሪም በግማሽ ዓመቱ ውስጥ 4 ቢሊዮን ብር ግብር እና 3 ቢሊዮን ብር የትርፍ ክፍፍል ለመንግሥት ገቢ ማድረጉን ያስታወቀው ተቋሙ፤ የአገልግሎት ጥራት ማሻሻል፣ አዳዲስ አገልግሎት ገበያ ማቅረብ፣ ወጪ ቆጣቢና የውጭ ምንዛሪ ማመንጨት ሥራዎች ላይ ብዙ ተግባራቶች እንዳከናወነ ገልጿል። የፋይበር መስመሮች መቆራረጥ፣ የቴሌኮም ማማ መሰበር እና የኃይል አቅርቦት መቆራረጥና የሰው ኃይል አቅም ውስንነት በዋናነት ያጋጠሙ ችግሮች ናቸው ሲል ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011