የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል እርምጃ እየተወሰደልኝ አይደለም ሲል ወቀሰ

0
454

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል በተደጋጋሚ ቁጥራቸው የበረከቱ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን እና ግብይቶችን በመረጃ አስደግፌ ለሚመለከተው አካል ባቀርብም እርምጃ አልተወሰደልንም ሲል ወቀሰ።

ማዕከሉ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በሥልጣን ላይ እያሉ በተደጋጋሚ ‹‹የሕገ ወጥ ዝውውሩን እና ግብይቱን ምንጮች በተጨባጭ መረጃ አስደግፌ ሪፖርት ባደርግም ምላሽ ሳይሰጠኝ ቀርቷል›› ብሏል። በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን ሕገ ወጥ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገራት ገንዘቦች ዝውውር አስቀድሞ መከላከል ይቻል ነበር ሲሉ የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ኪዳነማሪያም ገብረፃዲቅ መግለፃቸውን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተስፋየ ዳባ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። አሁንም ቢሆን የተደራጁ መረጃዎችን ወደ እርምጃ የመቀየር ክፍተት መኖሩን ዋና ዳይሬክተሩ ለቋሚ ኮሚቴው አሳውቀዋል።

ማዕከሉ በውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመስክ ምልከታ በተደረገበት ወቅት ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሮችንና ሽብርተኞችን በገንዘብ ለመርዳት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ጠንክሮ መስራት እንዳለበት የተጠቆመ መሆኑን ተስፋየ ገልጸዋል። እንደሰብሳቢው ማብራሪያ ማዕከሉ በበጀት ዓመቱ ግማሽ ላይ 309 የሚሆኑ ተጠርጣሪ ግብይቶችን የያዘ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 21 ወንጀል ነክ ፣ 7 በሪል ስቴት ግብይት፣ 7 በሒሳብ ባለሙያዎች፣ 14 በፌደራል ፖሊስ ላይ የተለያዩ አስፈላጊ መረጃዎችን መሰብሰብና ማደራጀት መቻሉን ገልፀዋል።

ሽብርተኝነትን በገንዘብ ለመርዳት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር በአዋጅ ቁጥር 780/2005 የተቋቋመው ይህ ማዕከል በዋናነት መረጃን የመሰብሰብ፣ የማከማቸት፣ የመተንትን፣ ማሰራጨትና ቁጥጥር የማድረግ ኃላፊነቶች አሉት። ይሁን እንጂ ማዕከሉ በአዋጅ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ 300 ሺሕ ያህል ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን ለመቆጣጠር ቢሰራም ለማዕከሉ ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠቱ እና በተለያዩ አካላት ተፅዕኖ ስር በመሆኑ ምክንያት የተፈለገውን ለውጥ ለማምጣት አለመቻሉን ለማወቅ ተችሏል።

በተያያዘ ኢትዮጵያ የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ ጥረት እያደረገች ባለችበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር መኖሩ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ እምነት እንደሚያጡ በቋሚ ኮሚቴው ተነስቷል።

የማዕከሉ ተጠናክሮ አለመሥራት ሽብርተኞች የገንዘብ ድጋፍ ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ከውጪ ምንዛሪ የምታገኘውን ጥቅም በእጅጉ እንደሚቀንስ ተገልጿል። ቋሚ ኮሚቴው ማዕከሉ ያለበትን የሰው ኃይል እጥረት እና የመረጃ ትንተና ክፍተት በመረዳት በበጀት ዓመቱ ክፍተቶችን በመሙላት በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይደርስ መሥራት እንዳለበትም አሳስቧል።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here