የተራዘመ ጦርነት የኢትዮጵያን ችግር ያባብሳል

0
1552

ኢትዮጵያ የገጠማት ጦርነት አሁን ላይ ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥሯል። አንድ ዓመት ያስቆጠረው ጦርነት መነሻውን በትግራይ ክልል ቢያደርግም፣ በአሁን ወቅት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ የተራዘመ ጦርነት ሆኗል። ከአንድ ዓመት በፊት በክልሉ መዲና በሆነችው መቀሌ የተጀመረው ጦርነት፣ አሁን ላይ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ውስብስብ ችግር ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል። የጦርነቱ መራዘም በተለይ ጦርነቱ በደረሰባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለከፋ ረሃብ፣ ለመፈናቀል እና ለንብረት ውድመትና ዘረፋ ዳርጓቸዋል።

የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ባሳለፍነው ሐሙስ በወቅታዩ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫ፣ “በአሁኑ ሰዓት ጦርነቱ እየተካሄደ ያለው በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ ነው። በዚህ አሸባሪና ወራሪ ቡድን ከፍተኛ ሰብዓዊና ንብረት ውድመት፣ ዘረፋ፣ ሥነ ልቦናዊ ጫና እየተፈጸመ የሚገኘው በአማራ እና በአፋር ሕዝብ ላይ ነው። ወራሪው ኃይል ከበባ በመፍጠሩ ምክንያት ከሰባት ሚሊዮን በላይ የአፋርና አማራ ሕዝብ በምግብ ዕጥረት፣ በመድኃኒት አቅርቦት ችግር እየተሰቃየ ይገኛል” የሚል ሐሳብ ተካቷል።

ከዚህ የመንግሥት መግለጫ መረዳት የሚቻለው ህወሓት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ከተፈናቀሉት ዜጎች በላይ ቡድኑ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የቀሩ ዜጎች ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ነው። በአማራ እና በአፋር ክልሎች በህወሓት ቁጥጥር ሥር በሚገኙ አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ አለመቻሉም ተገልጿል።

ጦርነቱ በዚህ ከቀጠለ በከፋ ችግር ውስጥ የሚገኙ የሰባት ሚሊዮን ዜጎችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ መገመት አዳጋች ነው። በመሆኑም መንግሥት የመጨረሻ አቅሙን ተጠቅሞ ጦርነቱ ባልተዛረመ ጊዜ በማጠናቀቅ በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ሊታደግ ይገባል። የሰሜኑ የኢትዮጵያ ከፍል ጦርነት ገና እንደተጀመረ የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል በ“ሕግ ማስከበር ዘመቻ” ሲሰማራ የተራዘመ ጦርነት እንዳይሆን ብዙዎች ሲመክሩ እና ስጋታቸውን ሲገልጹ ነበር። ይሁን እንጅ ጦርነቱ የተራዘመ መሆኑ አልቀረም፤ ምንም እንኳን አሁንም እየቀጠለ ያለ ጦርነት ቢሆንም፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹኅን ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ንብረታቸው ወድሟል፤ እንዲሁም ከጦርነቱ መሽሽ ያልቻሉ ዜጎች በረሃብ፣ በውሃ ጥምና በሕክምና ዕጦት ችግር ላይ ወድቀው ይገኛሉ።

አንደኛ ዓመቱን ባሳለፍነው ጥቅምት 24/2014 ያስቆጠረው ጦርነት ለስምንት ወራት በትግራይ ክልል ተገድቦ የቆየ ቢሆንም፣ የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ሕግ ለማስከበር አሰማርቶት የነበረውን የመከላከያ ኃይል ሰኔ 21/2013 የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ በማስወጣቱ ህወሓት ኃይሉን አደራጅቶ የአማራ እና አፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢዎችን በወረራ ይዟል።

የፌዴራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ ክልል ሲወጣ መጠበቅ የነበረበትን አዋሳኝ አካባቢዎች ባለመጠበቁ ህወሓት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ለመግባት ዕድል በማግኘቱ ጦርነቱ እንዲስፋፋ ሆኗል። የፌዴራል መንግሥት በወቅቱ ከትግራይ ክልል ከወጣበት ምክንያት አንዱ የውጭ ጫናዎች በመብዛታቸው ነበር።

ይሁን እንጅ የውጭ ጫናው የረገበው ለአንድ ሰሞን ነበር። የጦርነቱ መራዘም በመንግሥት ላይ የሚደርሰውን ጫና የሚበረታው እንጅ የሚያለዝበው አይደለም እና የውጭ ጫናውን ተቋቋሞ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ይልቁንም እየበረታ የመጣው የውጭ ጫና ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር እየተባባሰ ስለሚቀጥል ጦርነቱን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ኢትዮጵያን ከውጭ ጫና እና ጣልቃ ገብነት መጠበቅ ይገባል።

የህወሓት ታጣቂዎች በደረሱባቸው በአማራ እና በአፋር ክልሎች የሚገኙ አካባቢዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን እና የመንግሥትን ንብረት እየዘረፉ እና እያወደሙ መቀጠላቸው ደግሞ አሁናዊ ጦርነት ከሚደርሰው ችግር በተጨማሪ በወደፊቱን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ የከፋ ነው።

ጦርነት ከሚያስከትለው ሰብዓዊ ኪሳራ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራው ለረጅም ዓመታት የማያገግም ጠባሳ ጥሎ ያልፋል። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ደግሞ ለጦርነትና ለሰብዓዊ ድጋፍ ከሚወጣው ወጭ በላይ ለዓመታት የለሙ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብቶች እየወደሙ ነው። ጦርነቱ በዚህ ከቀጠለ የወደፊቱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፋ ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል። በመሆኑም በኹለት እግሩ ያልቆመውን ኢኮኖሚ ከከፋ አዘቀት ለመታደግ ያልተራዘመ ጦርነት ወሳኝ ነው።

ህወሓት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መግባት ከጀመረበት ከሐምሌ 2014 ወዲህ እየተስፋፋ የመጣውን ጦርነት ለመመከት ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና ከመከላከያ ሠራዊት በተጨማሪ የሕዝብ ትብብር እንደሚያስፈልግ የገለጸው መንግሥት፣ ሕዝቡ ወደ ጦር ግንባር እንዲዘምት እና ከመከላከያ ጎን እንዲሰለፍ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው። በዚህም ክልሎች ወደ ጦር ግንባር እየተቀላቀሉ ነው ተብሏል።

መንግሥት ለሕዝብ ያቀረበውን “የክተት ጥሪ” እና “አገርን ከመፍረስ የመታደግ የሕልውና ዘመቻ” በአግባቡ በመምራት ጦርነትን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል። ጦርነቱ ኢትዮጵያ የመታደግ ነው ከተባለ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ኹሉም ክልሎች የችግሩ ተቋዷሽ መሆናቸውን በተጨባጭ እንዲያሳዩ ማድረግ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

አሁናዊ ጦርነቱ ያለው በአማራ እና በአፋር ክልሎች ቢሆንም፣ ችግሩ ኹሉንም የሚያጣቅስ መሆኑን በመገንዘብ፣ ክልሎች በደስታ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በችግርም ጊዜ እርስ በርስ ተጋሪ መሆናቸውን በተግባር ማሳየት ይኖርባቸዋል። መንግሥት ያቀረበውን “የክተት ጥሪ” ሕዝብ ተሳትፎ በአግባቡ በመምራት የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ካልተቻለ፣ የጦርነቱ ዕድሜ በተራዘመ ጊዜ የመሰላቸት እና ያለመተማመን ችግር እንዳይፈጠር ከወዲሁ መጠንቀቅ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።

የዚህ ጦርነት መራዘም ለኢትዮጵያ አሁን ካለው ወቅታዊ ችግር በተጨማሪ ወደፊት የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተጽዕኖ የከፋ እንደሚሆን አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር መረዳት ይቻላል። በመሆኑም ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰባት ችግር በላይ የወደፊቱ እንዳይብስባት በምንም መንገድ ቢሆን ባልተራዘመ ጊዜ ጦርነቱን ማጠናቀቅ ተገቢ መሆኑን አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here