የጎዳና ተዳዳሪዎችን “እያፈሱ” ማቋቋም

0
991

የጎዳና ሕይወትን ሕይወቴ ብለው የሚኖሩ ዜጎችን ማየት የተለመደ የዕለት ትዕይንት በሆነባት አዲስ አበባ፥ የከተማ መስተዳድሩ መልሼ አቋቁማለሁ በማለት ሥራውን በይፋ ያስተዋወቀው በቅርቡ ነው። ይህንኑ ተከትሎ በአዲስ አበባ ያሉትን የጎዳና ተዳዳሪዎች ኑሮ ምን እንደሚመስል፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን መልሶ ለማቋቋም ከዚህ ቀደም የተሠሩ ሥራዎችና የገጠሙ ፈተናዎችን እንዲሁም አሁን የተቋቋመው ትረስት ፈንድ እና ውጥኑን በመቃኘት ስንታየሁ አባተ ይህንን ሐተታ ዘ ማለዳ አቅርቧል።

ተስፋዬ አበበ (የአባቱ ሥም የተቀየረ) በሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት የነበረውን የአንድ ዓመት ከስድስት ወራት እስር ጊዜ ጨርሶ ተወልዶ ወዳደገባት አዲስ አበባ ከመጣ ገና ሳምንቱ ነው። ይሁንና ከእስር ተፈቶ ሲመለስ ‘እንኳን ለቤትህ አበቃህ፣ እንኳንም ደስ አለህ’ ብሎ የተቀበለው የለም፤ ይልቁንም ከ1999 ጀምሮ የተለማደውን የጎዳና አዳር እንደ አዲስ ጀምሯል። ባምቢስ አካባቢ በሚገኘው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አዲሱ ሕንፃ ፊት ለፊት ከምትገኝና በእንጨት ከተሠራች ባለ መደገፊያ የመንገደኞች ማረፊያ ወንበር ላይ ኩርምት ብሎ ያገኘነው ተስፋዬ ቀርቦ ብሶቱን የሚያደምጠው ሰው ማግኘት ይፈልጋል። ይሁንና አዲስ አበቤው ለጎዳና አዳሪዎች ባለው አረዳድ ምክንያት ፍላጎቱ ምላሽ አላገኘም። የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ተስፋዬን ቀርቦ በጠየቀው ወቅት ያለማመንታት ነበር ያለፈባቸውን የሕይወት ስንክሳሮች መዘርዘር የጀመረው። ተስፋዬ ውልደትና ዕድገቱ በአዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ ነው፤ ኑሮውም ከቤተሰቦቹ ጋር የነበረው ወጣት በተለያዩ ምክንያቶች ከ1999 ጀምሮ የጎዳና ሕይወትን መለማመድ እንደጀመረ ይናገራል። “በራሴም ችግር ከቤተሰብ ጋር እየተጣላሁ አልፎ አልፎ ጎዳና ላይ አድር ነበር” የሚለው ተስፋዬ “ከ2004 ወዲህ ግን ሙሉ በሙሉ ጎዳና ላይ ወጣሁ” ይላል።

“በ2004 ሙሉ ለሙሉ ጎዳና ላይ የወጣሁበት ምክንያት ቤታችን ለልማት ተብሎ በመፍረሱ ነው” የሚለው ወጣት ተስፋዬ ቤታቸው ከመፍረሱ በፊት ከቤተሰብ ጋር ባይሥማማም ጎዳናው ሲሰለቸው ወደቤት ይገባ እንደነበር ያነሳል። የቀበሌ ቤታቸው ከመፍረሱ ጎን ለጎን ከቤተሰብ ጋርም መሥማማት ባለመቻሉ ቤተሰብ እየከሰሰው ሳይቀር ቀናትን በፖሊስ ጣቢያ ይታሰር እንደነበር ይገልጻል። በዚህ ሒደት ከቤተሰቡ ጋር መቃቃር ውስጥ በመግባትም አንድ ጊዜ በቤተሰቡ ተከሶ ለ15 ቀናት በፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ሲፈታ ዳግም ወደ ቤተሰቦቹ ላይመለስ መለያየቱን አይዘነጋም።

ከሸዋሮቢት እንደተፈታ ተመልሶ ወደ አራት ኪሎ ማቅናቱን የገለጸው ተስፋዬ “የሰፈር ልጆች እንዴት ባደግክበት አካባቢ ወንጀል ትሠራለህ ብለው አባረሩኝ፣ በዚህም የተለያዩ ቦታዎች እያደርኩ ነው” ሲል አክሏል። “መነን አካባቢ አንዲት አክስት አለችኝ፤ እሷ ጋርም ገና አልሔድኩም። አሁን እየጠበቅሁ ያለሁት ሐሙስ (ጥር 30) ከባሕር ዳር የሚመጣ ያጎቴ ልጅ አለ እሱን ነው” ይላል። የአጎቱ ልጅ ምን እንዲያደርግለት እየጠበቀ እንደሆነ የጠየቅነው ተስፋዬ “አግዞኝ የሆነ ሥራ ያስጀምረኛል ብዬ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ምን እንደማደርግ አላውቅም ሲል” ተስፋና ስጋት የሚፈራረቅበትን ፊቱን እያሸ ያወራል።

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጀመረውን “የጎዳና አዳሪዎች ማፈስ ሰምቻለሁ። ትናንትም (ጥር 28) ቦሌ መድኃኔዓለም ቤተክርሲቲያን ነበር ያደርኩት ‘አፈሳ አለ’ ሲሉኝ ነው ዛሬ ወደዚህ የመጣሁት” ሲልም አጫውቶናል። ለምን የአስተዳደሩን ተግባር እንደሸሸው የጠየቅነው ተስፋዬ ከዚህ በፊትም አፋር አሜባራ ሔዶ እንደሠለጠነና በሠለጠነበት ሙያ ወደ ሥራ የሚስገባው በማጣቱ ዳግም ወደ ጎዳና እንደተመለሰ በመግለጽ ሌላ ታሪክ አከለልን።
እኛም መልካሙ ነገር እንዲገጥመው ተመኝተንለት ተስፋዬን ከያዛት በባለ አንድ ብር ጥቁር ፌስታሉ ቋጠሮ ጋር ትተነው ሔድን።

አዲስ አበባና የጎዳና ኑሮ
አዲስ አበባ በተለይም ምሽት ላይ ሰዎች ኋላቸውን ባለማመን በፍጥነት እየተገላመጡ የሚሔዱባት ከተማ ከሆነች ውላ አድራለች። የሰዎች ፍርሐት የሚመነጨው ከተለያዩ ጉዳዮች ቢሆንም አንዱ ምክንያት በጎዳና አዳሪዎች ላለመዘረፍ መሆኑ እሙን ነው። አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም አዲስ አበባን እየፈተኑ ስላሉ ወንጀሎች በተመለከተ በጻፈችው ትንታኔ ያነጋገረቻቸው የፀጥታ አስከባሪ አባላት በሥራቸው አንዱና ዋና ፈተና የሆነባቸው የጎዳና አዳሪዎች ስለመሆናቸው መናገራቸው ይታወሳል። አባላቱ እንደሚሉት ከሆነ ቀን ላይ ተደብቀው የሚውሉ ጎዳና አዳሪዎች ማታ ላይ በየምሽት ቤቱ ሲጠጡና ሲጨፍሩ አምሽተው ወደ ቤታቸው የሚሔዱ አዲስ አበቤዎችን ማጅራት በመምታት ተግባር ተጠምደዋል። ይህም ከፀጥታ ስጋትነት አልፎ የሰዎችን ሕይወት እስከመንጠቅ እንደሚደረስ ነው አዲስ አበባን 24 ሰዓት በፈረቃ የሚጠብቁት የፖሊስ አጋዥ ኃይሎች የሚገልጹት። ስለዚህም መንግሥት አንድ ሊል ይገባል የሚል እምነት አላቸው።

 

ከአስተባባሪዎች እንደሰማነው የከተማ አስተዳደሩ በመጀመሪያው ዙር ከጎዳና አነሳለሁ ብሎ ያሰበው ኹለት ሺሕ ሰዎችን ቢሆንም ያነሳቸው ሰዎች ቁጥር አራት ሺሕ መድረሱ መጨናነቅን ፈጥሯል

 

ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች እንደሚናገሩትም ሆነ አዲስ አበባን ዞር ዞር ብሎ ለሚቃኝ ሰው እንደሚታው የጎዳና አዳሪነት አሁን ላይ በዐሥር ሺሕዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የማይፈራበትና የማይታፈርበት አንዱ የሕይወት ገጽ ሆኗል።

ብዙዎች እንደሚሉት ወደ ጎዳና የሚወጡ ሰዎች የጎዳናውን ሕይወት ፈልገውት ባይሆንም፥ ሁሉም ግን ተቸግረውና ተገፍተው እንዳልሆነ ይታመናል። ቀድመን ያነሳነው ተስፋዬ እንደሚለውም ራሱን ጨምሮ ብዙዎች “በጥጋብ ወይም በራሳቸው ችግር ከቤተሰብ ጋር መሆንን አሻፈረኝ” ብለው ወደ ጎዳና ይወጣሉ።
ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ጎዳና አዳሪዎች ችግር ገፍቷቸው እንደሚወጡ ይታመናል። ከክፍለ አገር ሥራ ፍለጋን ብለው ወደ አዲስ አበባ በቡድንና ተናጠል መጥተው እንዳሰቡት ሳይሆንላቸው ሲቀር ጎዳና ቤቴ የሚሉትን ጨምሮ የቤተሰብ መበተን ጎዳና ላይ የሚያወጣቸው ኢትዮጵያዊያን ያሉትን ያህል እዚያው ጎዳናው ላይ ተወልደው ጎዳና ላይ የሚያድጉ ልጆችም ቁጥር አያሌ መሆኑ ይነገራል።

አሁን አዲስ አበባ ተሽከርካሪ በቆመ ቁጥር ከየት መጣ የተባለ ልጅ በያዛት ጨርቅ የመኪናን መስታወት አብሶ ሳንቲም እንዲሰጠው እጁን ወደ ሹፌሩ የሚዘረጋባት ሆናለች። ማስቲሽና ቤንዚን እያሸተቱ ከፀሐይና ብርድ ጋር የሚታገሉ አዳጊዎች የሞሉባት አዲስ አበባ ሰዎችን ከጎዳና በማንሳት ወደ መደበኛና ጤናማ ሕይወት ለመመለስ በግብረ ሰናይ ድርጅቶች እየታገዘች ብትሞክርም አመርቂ ለውጥ አለመገኘቱን ብዙዎች ይስማሙበታል።

ሰሞነኛው ዘመቻ
ከሰሞኑ የአዲስ አበባ አስተዳደር 50 ሺሕ የጎዳ አዳሪዎችን ከጎዳና ሕይወታቸው ለማላቀቅና ከማኅበረሰባቸው ጋር ለመቀላቀል በሚል የጎዳና አዳሪዎችን ማንሳትና በማዕከል ማሰባሰብ ጀምሯል። በዚህ ዘመቻ ላይ ያለምንም ልዩነት ጎዳና ላይ ያሉ ሁሉ ተነስተውና አገግመው ወደ ተሻለ ሕይወት እንዲገቡ ይደረጋል የሚል ተስፋም ተሰንቋል።

የጎዳና አዳሪዎቹን ሕይወት ከመቀየር ባለፈ ብዙዎች ሊቀንስ ይሆናል እንጂ ሊቀር ከቶ አይችልም የሚሉትን ልመናም ጭምር “መቅረት አለበት” የሚል አቋም ይዞ የተነሳው የከተማ አስተደዳደሩ አዲስ መርሐ ግብርን አስተዋውቋል። እስከ 14 ወራት በሚሆን ጊዜ የጎዳና አዳሪዎችን ለማንሳት ያለመው አስተዳደሩ ዕቅዱን ገቢራዊ ለማድረግ እሱ ከሚመድበው በጀት ባለፈ ፍላጎቱ ያላቸው ሁሉ እንዲረዱት የሚያስችለውን “የማኅበራዊ ትረስት ፈንድ” አስተዋውቋል። የአዲሱ መርሐ ግብር ውጤታማነት ከፍ ይል ዘንድም ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ የማኅበራዊ ትረስት ፈንዱ የበላይ ጠባቂ እንዲሆኑ ተደርጓል። አስተዳደሩ ደግሞ ለመነሻ በሚል 100 ሚሊዮን ብር መመደቡ ታውቋል። ኅብረተሰቡም 6400 ላይ Aን በመላክ ከኹለት ብር ጀምሮ እንዲያግዝ ተጠይቋል። በባንክ መርዳት ለሚፈልጉም እንዲሁ የባንክ ሒሳብ ቁጥር ይፋ ሆኗል።

እንደምክትል ከንቲባው ታከለ ዑማ ገለጻ ከሆነ በአዲስ አበባ 50 ሺሕ የሚሆኑ የጎዳና አዳሪዎች ያሉ ሲሆን፥ ሁሉንም በማንሳትና ወደ ማዕከላት በማስገባት ሥልጠናዎች እንዲያገኙ፣ እንዲሁም እንዲያገግሙና ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ይሠራል። ይህን ለማሳካት ከሰሞኑ በተጀመረው የጎዳና አዳሪዎችን የማንሳት ተግባር ስድስት ማዕከላት ተመርጠው ሥራ ተጀምሯል። ማዕከላቱን ወደ ውስጥ ዘለቆ መመልከትና ከጎዳና የተነሱ ሰዎች ማናገር “በጊዜያዊነት ለመገኛና ብዙኃን ተከልክሏል” በሚል የፖሊሶች ምላሽ ማዕከላቱን መጎብኘትና ሰዎችንም ማናገር ባንችልም ከአስተባባሪዎች እንደሰማነው የከተማ አስተዳደሩ በመጀመሪያው ዙር ከጎዳና አነሳለሁ ብሎ ያሰበው ኹለት ሺሕ ሰዎችን ቢሆንም ያነሳቸው ሰዎች ቁጥር አራት ሺሕ መድረሱ መጨናነቅን ፈጥሯል። በመሆኑም የተነሱት ሰዎች ቦታ ተፈልጎላቸውና ተረጋግተው እስኪቀመጡ ድረስ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር እንዳይገናኙ በሚል መከልከሉን የአዲስ ማለዳ ጋዜጠኛ መስቀል አደባባይ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ጀርባ በሚገኘው “ፊንፊኔ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት” ቅጥር ግቢ ተገኝቶ መታዘብ ችሏል።

የጽሑፉ አዘጋጅ በሥፍራው በተገኘበት ረቡዕ ጥር 29 ረፋድ ወትሮ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበረው ግቢ በበርካታ ፖሊሶች ዙሪያው ሲጠበቅ፣ ጎዳና አዳሪዎች በጨዋታ ጩኸት የአካባቢውን ቀልብ ሲገዙትና በሚጫወቱት የመረብ ኳስ ወደ ሌላ አዲስ ሕይወት በመሸጋገር ላይ ስለመሆናቸው መረዳት ችሏል። ቀድሞ በዚህ ሰዓት በየጥጋጥጉ ተኝተውና ሳንቲም ለማግኘት በየተሸከርካሪ መሥመር ውስጥ እየተሹለከለኩ ይታዩ የነበሩት ጎዳና አዳሪዎች ዛሬ ላይ በአንድ ማዕከል ተሰብስበው መረብ ኳስን ሲጫወቱ ማስተዋል ለብዙዎች አዲስ ዓይነት ስሜት የሚፈጥር ነው።

ከዚህ ቀደም ምን ይደረግ ነበር?
የጎዳና አዳሪነት ለኢትዮጵያዊያን ብርቅ አይደለም፤ ይልቁንም መጠኑ ይለያይ እንጂ በሁሉም የአገሪቱ ከተሞች ጎዳናን ቤቴ ብለው የሚኖሩ ሕፃናት፣ ታዳጊዎች፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና ጧሪ ቀባሪ ያጡ አረጋዊያን አሉ። ነፍሰ ጡር እናቶች ሳይቀሩ ጎዳና ላይ ውለው በሚያድሩባት ኢትዮጵያ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በግላቸውም ይሁን ከመንግሥት ጋር በመተባበር ጎዳና ላይ የወጡትን ወደ ቤት በመመለስ፣ ለመውጣት የሚዘጋጁትን ደግሞ ቀድሞ በመታደግ በኩል ሲሠሩ ነበር።
ከእነዚህም መካከል ከአውሮፓዊያኑ 2011 ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ይካሔድ የነበረው “የኮከብ ብርሃን” የተሰኘ ፕሮግራም ይጠቀሳል። “ዩኤስኤይድ” በሚሰኘው የአሜሪካ የዕርዳታ ድርጅት ይታገዝ የነበረውና “ፓክት” የተባለ ድርጅት ይሠራው የነበረው የኮከብ ብርሃን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት ይሠራ የነበረ ነው።
ፕሮግራሙ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሕፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ሲሆን ሕፃናትና ቤተሰቦቻቸው በችግር ምክንያት የከፋ አደጋ ላይ እንዳይወድቁ (ጎዳና መውጣትንም እንደሚያጠቃልል ልብ ይሏል) ባሉበት መደገፍን የሚመርጥ ነው። በዚህም የአምስት ዓመቱ ዕኩሌታ ላይ በተደረገው ምዘና በየዓመቱ ለ500 ሺሕ ከፍተኛ ተጋላጭ ሕፃናት ደጀን ለመሆን የተነሳው ፕሮግራም ከ800 ሺሕ በላይ ሰዎችን እንደታደገ መረጃዎች ያሳያሉ። ከእነዚህም ውስጥ 537 ሺሕ በላዎቹ ሕፃናት እንደሆኑ በወቅቱ የወጣው ሪፖርት ያመለክታል።

ሌላው በጦርነት ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን ለማገዝ በማለም በ1981 የተቋቋመው “ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን” የተሰኘ አገር በቀል ማኅበር ነው። ማኅበሩ በየጊዜው አቅሙን እያሳደገ ሲመጣም ዕይታውን በማስፋት እስካሁን 119 ሺሕ ዜጎችን በተለያዩ አግባቦች መደገፍ እንደቻለ የማኅበሩ የሚዲያ ዳይሬክተር ነጋሽ በዳዳ ለአዲስ ማለዳ ይገልጻሉ። ማኅበሩ በአምስት ክልሎች (ትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ጋምቤላና ደቡብ) ባሉት ማዕከላት የጎዳና አዳሪዎችን፣ ለምኖ አዳሪዎችን፣ ደጋፊ የሌላቸውን ሕፃናት እና ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በማሠልጠን እና ወደ ሥራ እንዲሠማሩ በማድረግ ሥራ መሠማራቱ ይነገራል። ሰዎች ችግር ወደ ጎዳና እንዳይገፋቸውና ከትምህርታቸው እንዳያናጥባቸው ባሉበት የሚደግፍበትም መርሐ ግብር አለው።

ኤልሻዳይ ከጎዳና አዳሪዎች ጋር በተያያዘ በስፋት የሚታወቅበት ሥራው በተለይም በአፋር ክልል አሜባራ ወረዳ በሚገኘው አዲስ ራዕይ ማሠልጠኛ ማዕከል ከአዲስ አበባና ክልል ከተሞች የሚወሰዱ የጎዳና አዳሪዎችን በማሠልጠን ወደ ሥራ እንዲገቡ ማገዝ ነው።

ለሦስት ዙሮች በተካሔደው ሥልጠና ኤልሻዳይ ከአዲስ አበባ አስተዳደርና በተለምዶ ሜቴክ እየተባለ ከሚጠራው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በትብብር ይሠራ እንደነበር ይታወቃል። እንደ ነጋሽ ገለጻ በመጀመሪያውና በኹለተኛው ዙር ማኅበሩ ሠልጥነው ወደ ሥራ እንዲሠማሩ የተሰጡትን ስድስት ሺሕ 500 የጎዳና አዳሪዎች ከአጋሮቹ ጋር በማሠልጠን ወደ ሥራ እንዲሠማሩ በማድረግ በኩል ተሳክቶለታል።

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከዓመታት በፊት በነበሩት ኹለት ዙሮች የሠልጣኞች ምረቃ ላይ ተገኝቶ የነበረ ሲሆን በኹለቱም ዙሮች ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁ ዜጎች በሠለጠኑበት ሙያ የብቃት ምዘና ወስደው ብቃታቸው በመረጋጋጡ ሁሉም ወደ ሥራ እንዲገቡ እንደሚደረግ ምርቃቱ ላይ ይገኙ በነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ እና የቀድሞው የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ቃል ሲገባ እንደነበር ያስታውሳል። ለአብነትም ብዙ ሠልጣኞች የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ በተለያዩ የመንግሥት ፕሮጀክቶቸ ላይ እንዲሠማሩ ሆኗል። የአዲስ አበባ አስተዳደርም በሹፍርና ሙያ የሠለጠኑ 290 አካባቢ ወገኖች ሥራ በመፈለግ ታክተው ዳግም ወደ ጎዳና እንዳይመለሱ በሚል መንጃ መፈቃድን በራሱ ወጪ ሸፍኖላቸው በአስተዳደሩ መዋቅር ሥር በሚገኙ ተቋማቱ እንዲቀጠሩ ማድረጉ በወቅቱ ሲያስመሰግነው ነበር። ለወራትም የቤት ኪራይ እንዳይቸገሩ በሚል እንደሚያግዛቸው ከንቲባው ቃል ገብተውላቸው ነበር። የወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትርም ሆኑ ከንቲባው ኃላፊነቱን ወስዶ በመደገፍ ሥልጠናውን አግኝተው ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ በኩል ይሠራ የነበረውን ኤልሻዳይ እና የሥልጠና ማሽሪዎችን ጨምሮ በሙያ እገዛ ያደርግ የነበረውን ሜቴክ ሲያመሰግኑ፣ በትብብር ሥራቸውም እንዲገፉበት ሲጠይቁና የወገን አለኝታነታቸውን እንዲያጠነክሩ ለዚህም መንግሥት ተገቢውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ሲገቡ እንደነበር በወቅቱ በብዙ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ሲዘገብ ነበር።

የኤልሻዳይ ሥራ ወዴት ሔደ?
ነጋሽ እንደሚሉት ኤልሻዳይ ሰኔ 30/2009 በጀመረው የሦስተኛው ዙር ሥልጠና 13 ሺሕ የጎዳና አዳሪዎችን ተረክቦ በሚፈልጉት ሙያ መስኮች ማሠልጠን ቢጀምርም ወደ ሥራ የማሠማራቱ ሒደት እንደ ቀዳሚዎቹ ኹለት ዙሮች አልጋ በአልጋ አልሆነም። የሠልጣኞቹ ቁጥር ብዙ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በወቅቱ መንግሥት ወደ ሥራ ሊያሠማራቸው የሚችል አቅም እንደሌለው በመግለጹ ሠልጣኞቹን ሥራ ማስጀመሩ ከባድ እንደነበር የሚናገሩት የሚዲያ ዳይሬክተሩ ማኅበሩ ሠልጣኞቹ በግብርና ሥራ ተሠማርተው ሀብት ንብረት የሚያፈሩበትን ፕሮጀክት ቀርፆ ለመንግሥት እንዳቀረበም ያስታውሳሉ። መንግሥት ፕሮጀክቱን ስለወደደውም ተቀብሎታል የሚሉት ነጋሽ ማኅበራቸው የቀረፀው ፕሮጀክት በግብርና ዘርፍ ላይ ልምዱ ለሌለው ሜቴክ መሰጠቱን በማንሳት ሜቴክም እንደታሰበው ሠልጣኖቹን በተቀረፀው ፕሮጀክት መሠረት በግብርናው ዘርፍ ላይ እንዳላሠማራቸው ይገልጻሉ። ከ13 ሺሕዎቹ ሰልጣኖች 10 ሺሕዎቹ መመረቃቸውን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ ወደ ሥራ ባልገቡ ቁጥር ቁጥራቸው እየቀነሰ መምጣቱንም ያክላሉ። መንግሥትም ሠልጣኖቹን ወደ ሥራ ማስገባት ካልቻለው ሜቴክ ፕሮጀክቱን ነጥቆ ለግብርና ሚኒስቴር መስጠቱንና ግብርናም ቢሆን እንደታሰበው ሥራ አለማስጀመሩን ይገልጻሉ። በመጨረሻም በጠቅላይ ሚንስቴር ጽሕፈት ቤት በኩል በተወሰደ እርምጃ ፕሮጀክቱን የቀረፀው ኤልሻዳይ በራሱ ባለቤትነት ፕሮጀክቱን እንዲተገብር ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ከታኅሣሥ 2011 ጀምሮ በአፋር ክልል ውስጥ በተዘጋጀ ቦታ 525 የሠለጠኑ ወጣቶች በግብርና ዘርፍ ተደራጅተው እንዲሠሩ እየተደረገ መሆኑን ነጋሽ ነግረውናል።

10 ሺሕ የጎዳና አዳሪዎችን አሠልጥናችሁ እንዴት 525ቱን ብቻ ወደ ሥራ እንዲገቡ ሆነ ለሚለው ጥያቄ ነጋሽ ሲመልሱም ተመራቂዎቹ ረጅም ጊዜን ወደ ሥራ ሳይገቡ በመቅረታቸው ተስፋ እየቆረጡ ስለወጡ እንደሆነ ያነሳሉ። የጠቅላይ ሚንስቴር ጽሕፈት ቤት ውሳኔ እስኪያሳልፍ ድረስ ተመርቀው ሥራን ይጠብቁ የነበሩት ወጣቶች ቁጥር በየጊዜው እየመነመነ መጥቶ ሕዳር 2011 ላይ ሦስት ሺሕ ደርሶ እንደነበር ይጠቅሳሉ። ውሳኔው ሲተላለፍም ከሦስት ሺሕዎቹ መካከል አብዛኞቹ ወደ መጡበት ክልል መሔድን በመምረጣቸው መንግሥት በነፍስ ወከፍ 9500 ብር እየሠጠ እንደሸኛቸው ያክላሉ። አዲስ ማለዳ ስለዚህ ጉዳይ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳረጋገጠችውም መንግሥት በየክልልላቸው ሔደው መቋቋም ለሚፈልገፉት ድጋፍ አድርጎ ሸኝቷል። ከእነዚህ የተረፉትና በኤልሻዳይ የግብርና ሥራ ፕሮጀክት ውስጥ መሥራት የፈለጉት 525 ሰዎች ናቸው አሁን በአፋር በግብርና ሥራ ተሠማርተው የሚገኙት ተብላል።

በመግቢያችን ያነሳነው ባለታሪክም የሦስተኛው ዙር ሠልጣኖች ዕጣ ፈንታ ሰለባ ነው፤ “ኤልሻዳይ አሜባራ ወስዶን በመካኒክነት እየሰለጠንኩ ነበር፣ ኋላ ላይ በተማራችሁበት ሥራ አታገኙም በዶሮ ወይም በከብት እርባታ ዘርፍ ተደራጁ ስንባል አልፈለግነውም፤ በዚህም ሥልጠና ላይ እያለን የ15 ቀናት እረፍት እንደተሰጠን ከጓደኞቼ ጋር ትተነው መጣን” ይላል። ተስፋዬ አሁን ላይ አስተዳደሩ የጀመረውን የጎዳና አዳሪዎች የማንሳት ሥራም በዚሁ ምክንያት በጥርጣሬ ይመለከተዋል።
ስጋታቸው ከተስፋዬ ከፍ ያሉ ወገኖች ደግሞ ተግባሩን ከዚህ ቀደም እንደነበረው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ሲመጣ ጎዳና አዳሪዎችን የማሸሽ ዓይነት ላለመሆኑ ምን ዋስትና አለ ሲሉ ሌላም ጥርጣሬ እንዳላቸው ይገልጻሉ። ለዚህ የሚያስቀምጡት መከራከሪያ ደግሞ አስተዳደሩ በደንብ ሳይዘጋጅ ሰዎችን ከጎዳና እያነሳ ነው የሚል ነው። የማረፊያ ማዕከላቱ በወጉ አለመዘጋጀታቸውን የሚገልጹ ሰዎች አስተዳደሩ “በጨበጣ” እየሠራ ነው ሲሉ ትችት ይሰነዝራሉ። በማዕከላቱ በቂ የምግብና የመፀዳጃ አገልግሎት አለመኖሩን ተከትሎ ከማዕከላት እየጠፉ ያሉ የጎዳና አዳሪዎች ስለመኖራቸውም አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ሰምታለች። አስኮ አካባቢ ያለው አንድ ማዕከልም በቂ ዝግጅት ሳይደረግበት የጎዳና አዳሪዎቹ እንዲገቡበት መደረጉን የታዘቡ ሰዎች ለአዲስ ማለዳ ስለነበረው ሁኔታ አስረድተዋል።

መንግሥት ምን እያሰበ ነው?
የጎዳና አዳሪነት ለአዲስ አበባ ብቻ የተሰጠ ሳይሆን በሁሉም ከተማ ቀመስ አካባቢዎች የሚስተዋል ነው። የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር የጎዳና አዳሪነት ላይ ያተኮረ ጥናት ማካሔዱን የሚናገሩት በሚኒስቴሩ የማኅበራዊ ደኅንነት ልማት ማስፋፊያ ዳይሬክተሩ ፈለቀ ጀምበር በሁሉም ክልል 11 ከተሞች የተካሔደውን ጥናት መነሻ አድርገው ክልሎች ወደ ጎዳና የሚወጡ ወገኖችን ከምንጩ ማድረቅ እንዳለባቸው ምክረ ሐሳብ መቀመጡን ይገልጻሉ። በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት ነጋሽ ሰዎችን ወደ ጎዳና የሚወጣቸው ማኅበራዊ ችግር ምድን ነው የሚለው ተለይቶ መፍትሔ ካልተበጀለት በስተቀር “ዛሬ 50 ሺሕ የጎዳና ተዳዳሪን ብታነሳ ነገ ከዚህ በላይ ቁጥር ያለው ሰው ጎዳና ላይ ወጥቶ ታገኛለህ” ይላሉ።

ፈለቀ እንደሚሉት የጎዳና አዳሪዎችን በማንሳትና በማቋቋም ሒደት መንግሥት በወጉ መሥራት አለበት። ቀድሞ የተጀመረው “የልማታዊ ሴፍቲኔት” መርሐ ግብር ለጎዳና አዳሪዎቹ መልሶ ማቋቋምም ማገልገል እንዳለበት ያክላሉ። የጎዳና አዳሪነትን ከምንጩ ለማድረቅ የሰዎች ሕይወት በምጣኔ ሀብት ረገድ መለወጥ አለበት የሚሉት ፈለቀ መንግሥት ድኅነትን መቅረፍ ካልቻለ ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል ያምናሉ። ሌላው አዲስ አበባና ሌሎችም ከተሞች ላይ የተሻለ ነገር አለ የሚለው የተሳሳተ ግንዛቤ መሆኑን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ አምነው ከመጡ በኋላም የጠበቁት ሳይሆን ሲቀር ጎዳና ላይ ወድቆ የመቅረት ነገር በመኖሩ ቶሎ ወደ መጡበት የመመለስ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም የሚኒስቴሩ ጥናት ምክረ ሐሳብ ማቅረቡን ይጠቁማሉ። ከክልሎች ጋር የጎዳና አዳሪዎችን ከምንጩ እንዲከላከሉ መግባባት ላይ መደረሱንም አክለዋል።

በጥናቱ መሠረት ጊዜያዊ ግጭት የጎዳና አዳሪ ያደረጋቸው ዜጎች ቁጥር ቀላል አለመሆኑን ስለማመልከቱ የሚያነሱት ፈለቀ ይህን ለመከላከል በየአካባቢው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ እንዳለው ሁሉ ማኅበራዊ ችግሮችን ከሥሩ መፍታት የሚችሉ የማኅበራዊ ባለሙያዎች እንደሚያስፈጉ መታመኑንም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ አስተዳደር ምን የተለየ ነገር አመጣ?
የአሁኑ የአስተዳሩ ዘመቻ ምን የተለየ ነገር ይዞ መጥቷል ለሚለው ጥያቄ ምክትል ከንቲባው ከዚህ ቀደም ከነበረው የያዝ ለቀቅ ሥራ በተለየ መንገድ ይከናወናል ብለዋል። ለዚህም የእምነት ተቋማት፣ ታዋቂ ሰዎችና የኪነ ጥበቡ ዘርፍ ባለሙያዎች እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች እገዛ እንዲያደርጉም ተጠይቋል። በዚህም መሠረት ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ)ን ጨምሮ “ተወዳጅ” የሚባሉ አቀንቃኞች የሙዚቃ ድግስ ሊያዘጋጁና ከኮንሰርቱ የሚገኘውን ሙሉ ገቢ የጎዳና አዳሪዎችን ለማንሳትና ለማቋቋም እንዲውል ቃል መግባታቸውንም ምክትል ከንቲባው ለአብነት አንስተዋል።

የአስተዳደሩን ሰሞነኛ ሥራ የማይቃወሙት ነጋሽ “ፕሮጀክታችንን ግን በከተማ አስተዳዳሩ ተነጥቀናል” ይላሉ። ማንም ሰው ልጆችን ከጎዳና ሲያነሳ ማኅበራቸው እንደሚደሰት ግን ደግሞ አብሮ መሥራት እንደሚፈልግም ይገልጻሉ። ታዲያ መሥራቱን ማን ከለከላችሁ ለሚለው ጥያቄ “በግልጽ ደብዳቤ ባይጻፍም ሕፃናትን ከጎዳና እንዳናነሳ ተከልክለናል፣ በዚህም ከተማ ላይ የጎዳና አዳሪዎቸ በዙ፣ ማዕከሎቻችን ደግሞ ባዶ እየሆኑ መጡ” ሲሉ ያስረዳሉ። የጎዳና አዳሪዎችን ከማሠልጠን ባለፈ ሕፃናትን የመንከባከቢያ ማዕከላት ያሉት ኤልሻዳይ ማንሳት አትችሉም ከሚለው ዕቀባ ባሻገር “ስህተታችሁ ይኼ ነው የሚለን አላገኘንም፣ ቢሮ ስንሔድ ነው ፊት የሚዞርብን፣ ሥራችን ለአገር ካልጠቀመ በደብዳቤ በቃችሁ ልንባል ይገባል አሁን ያለው ግራ የገባው ነገር ነው” ሲሉ የሚዲያ ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።

“አስተዳደሩ እኛን አግልሎ ለምን ለብቻው መሥራት እንደፈለገ አልገባንም” ያሉት ነጋሽ “ከመስከረም 23 ጀምሮ ለድጋፍ ፈላጊዎቹ የምናውለውን ልብስና የምግብ ፍጆታ የያዘው የቃሊቲው መጋዘን እስካሁን እንደታሸገ ነው” ሲሉም መንግሥትን ይወቅሳሉ። “የምግብ ዘይት የያዘን መጋዘን አሽጎ የጎዳና አዳሪዎችን ለመመገብና ማቋቋም ኹለት ብር ደግፉ ማለት ምን የሚሉት ነገር ነው” ሲሉም ይጠይቃሉ። በሌላ በኩል “13 ሺሕ የሠለጠኑ የጎዳና አዳሪዎችን በትኖ ሌላ መሰብሰቡስ ምን ይሉታል” ሲሉ ያክላሉ።

ፈለቀ በሚንስቴሩ ጥናት የጎዳና አዳሪዎችን አንስቶ ማቋቋም መንግሥት ብቻውን ሊወጣው የሚችልው ባለመሆኑ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ተባብሮ መሥራት እንዳለበት መመልከቱን ያነሳሉ።

ኅዳር 2007 የወጣው “ብሔራዊ የማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ” በገጠርም ሆነ በከተማ ለምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ችግር የተጋለጡ ወገኖችን ፈጥኖ በመለየትና በማገዝ መታደግ እንደሚገባ፣ ለዚህም እንደ ልማታዊና ማኅበራዊ ሴፍቲኔት ያሉ መርሐ ግብሮችን በስፋት ማስፈፀም እንደሚገባ እንዲሁም ከግሉ ዘርፍ ተቋማት ጋር በጥብቅ ተቀናጅቶ የማኅበረሰቡን ችግር መፍታት አንገብጋቢው ጉዳይ እንደሆነ ያሠምርበታል።

የኤልሻዳይ ፕሮግራም ከመንግሥት ጋር በነበረ ትብብር ይፈፀም ስለነበረ አልባሳትና የተወሰኑ የምግብ ፍጆታዎችን በጉሙሩክ ተወርሰው ይወገዱ ከነበሩ የሚያገኙ እንደሆነ ይገልጻሉ። በዚህ ሒደትም የተወረሱ ቶርሽን ጫማዎችን የጎዳና አዳሪዎች አድርገው ሲታዩ ከፍተኛ ባለሥልጠጣናት ሳይቀር ‘እንዴት ጎዳና አዳሪ ቶርሽን ያደርጋል’ የሚል የተሳሰተ አመለካከት እንደሚያንፀባርቁ መታዘባቸውን በመግለጽ ይህም ለልጆቹ ሥነ ልቡና ጥሩ ባለመሆኑ ሊታረም እንደሚገባው ይመክራሉ። በዚህ ሐሳብ የሚሥማሙ የሥነ ልቡና ባለሙያዎችም ከጎዳና ተነስተው በማዕከል ተሰብስበውና በፖሊስ እየተጠበቁ ሲቀመጡ ከሌሎች የመገለል ሥነ ልቦናዊ ጫና እንዳያድርባቸውም አያያዝ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያስጠነቅቃሉ።

የኤልሻዳይን ቅሬታ እንደማያውቁ የሚገልጹት የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ ማኅበሩ ቅሬታውን ቢያቀርብላቸው እንደሚመክሩበት በማስቀደም የጎዳና አዳሪዎችን ሕይወት በመቀየር ረገድ አስተዳዳሩ ከማንኛውም ግለሰብም ሆነ ድርጅት ጋር ለመሥራት እንደሚፈልግ ተናግረዋል። በጀቱ በመንግሥት ብቻ ስለማይቻልም አጋዦች እንደሚያስፈልጉ አንስተዋል።

50 ሺሕ ሰዎችን በአንዴ ማንሳት እንደማይቻል በመጥቀስ፣ በዚህ ዓመት እስከ 10 ሺሕ ሰዎችን ከጎዳና ለማንሳት ማቀዳቸውን የገለጹት ዓለምፀሐይ ሰሞኑን 2 ሺሕ ሰው ለማንሳት ቢያቅዱም ከ3100 በላይ አንስተው በማዕከላት መጨናነቅ እንደተፈጠረ አክለዋል። የሰዎች የመነሳት ፍላጎት በማየሉም በራሳቸው ፍቃድ ወደ ማዕከላት ለመግባት መጥተው የተከለከሉ እንዳሉ ገልጸዋል። ሥራቸውን ከአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ጋር የሚያገናኘው እንደሌለም አስገንዝበዋል።
አስተዳደሩ ከሚያነሳቸው ሰዎች ውስጥ ደጋፊ አልባ ሕፃናትና አረጋዊያንን ወደ ቋሚ ማዕከላት፣ መሥራት የሚችሉትን ደግሞ የሙያ ሥልጠና እየሰጡ ወደ ሥራ ለማስገባት እንዲሁም በአዲስ አበባ ካሉ የጎዳና አዳሪዎች 90 በመቶዎቹ ከክልሎች የመጡ ስለሆነ ለ45 ቀናት አገግመው ክልሎች እንዲረከቧቸውና ወስደው እንዲያቋቁሟቸው እየተሠራ መሆኑን ዓለምፀሐይ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም አስተዳደሩ ለምኖ አዳሪና ጎዳና አዳሪዎችን በአውቶቡስ እየጫነ ወደየክልላቸው ይመልስ የነበረ ሲሆን የወሰዳቸው አውቶቡስ ተመልሶ አዲስ አበባ ሳደርስ የተወሰዱት ሰዎች አዲስ አበባ እንደሚመለሱ እየተነሳ የተሻለ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ይገለጽ ነበር። ስለዚህ የጠየቅናቸው የቢሮ ኃላፊዋ ይህ ዓይነቱ አሠራር ከዚህ በኋላ እንደማይቀጥል ገልጸው ክልሎች የተረከቧቸው ጎዳና አዳሪዎች እዚያም ሔደው ጎዳና ላይ እንዳወድቁ መከታተልና ማቋቋም እንዲችሉ ምክክር እየተደረገና የመንግሥትም አቅጣጫ ይኸው እንደሆነ ነግረውናል።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here