የጎዳና ተዳዳሪነትን “በአፈሳ” ማጥፋት?

0
707

በመዲናችን አዲስ አበባ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በግድ ማፈስ፣ ለተወሰኑ ጊዜያት በእስር ማቆየት፣ ያለፈቃዳቸው ሥልጠና መስጠት እና ሌሎችም የተለመዱ ናቸው። በተለይም ደግሞ እንደሰሞኑ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ሲኖር የጎዳና ተዳዳሪዎችን አፍሶ ለተወሰነ ጊዜ ጣቢያ ማቆየት እና ስብሰባው አልፎ፣ እንግዶቹ ወደየአገራቸው ከተሸኙ በኋላ ያለምንም ካሣ ወይም የፍርድ ሒደት መልሶ መልቀቅ የተለመደ ትዕይንት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ የዴሞክራሲ መርሖች ተጥሰዋል፣ የሕግ የበላይነት ተንኳስሷል ሲሉ የተደመጡ አካሎች ኖረው አያውቁም ማለት ይቻላል።

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የጀመረው እንቅስቃሴ አለ። መስተዳድሩ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በመሰብሰብ፣ ሥልጠናዎችን በመስጠት እና መልሶ በማደራጀት ማኅበራዊ ፍትሕን አሰፍናለሁ በሚል ቀና ሐሳብ ‘ትረስት ፈንድ’ አቋቁሞ የከተማዋን ነዋሪዎችም ለማሳተፍ እየሞከረ ነው። ይህ እንቅስቃሴ ከአፍሪካ ኅብረት ዓመታዊ ጉባዔ ጋር መግጠሙ በራሱ አጠያያቂ ቢሆንም፥ ዋነኛው አጀንዳ ግን መስተዳድሩ ከጎዳና ሕይወት ሊያነሳቸው የሚፈልጋቸውን ዜጎች ፈቃድ ማክበር አለመቻሉ ነው።
አዲስ ማለዳ ለሐተታ ከአነጋገረቻቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች መካከል አንዱ ወደ መጠለያ የተወሰዱትን ጓደኞቹን “ታፈሱ” እያለ ነው የሚናገረው። እሱም “አፈሳውን” ሰፈር በመቀየር እንዳመለጠ ይናገራል። ይህ ወጣት ከዚህ በፊት በተመሳሳይ መንገድ ወደ ካምፕ ተወስዶ የተሰጠው ሥልጠናም ምንም ስላልፈየደለት በዚህኛውም ላይ እምነት የለውም። ሌሎቹም ተመሳሳይ ስጋቶች ሊኖሯቸው ይችላሉ። ሆኖም “ታፍሰው” ወደ ጊዜያዊ መጠለያ ስለተወሰዱ በፈቃዳቸው የመስተዳድሩን እንቅስቃሴ መቀላቀላቸውን ማረጋገጥ አልተቻለም፤ ጋዜጠኞች ወደ ጊዜያዊ መጠለያ እንዲገቡም አለመፈቀዱ ጊዜያዊ መጠለያው ውስጥ የገቡት ሰዎች ሙሉ ፈቃዳቸውን እንዳልሰጡ ላለው ጥርጣሬ ማጠናከሪያ ነው።

በዴሞክራሲያዊ ስርዓት እና በሕግ አግባብ የጎዳና ተዳዳሪዎችን አስገድዶ መመለስ አይቻልም። መንግሥት ማኅበራዊ ፍትሕን ማስፈንና የእነዚህን ዜጎች ሕይወት የማሻሻል ኃላፊነት ቢኖርበትም፥ ይህንን ለማድረግ የጎዳና ተዳዳሪዎቹን ሙሉ ፈቃድ ማግኘት አለበት። ይሁን እንጂ ዜጎቹ በተለምዶ እንደወንጀለኛ የሚቆጠሩበት ልምድ አለ። ጎዳና ላይ ተዳዳሪ ስለሆኑ ብቻ በሕግ ጥሰት እስካልተያዙ ድረስ እንደነጻ ሰው የመቆጠር መብታቸው አይገፈፍም። በልመና መተዳደርም ቢሆን በሕግ እስካልተከለከለ ድረስ መብታቸው ነው። ልመናን “ራስን የመግለጽ ነጻነት” ነው ብለው የሚከራከሩም አሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here