ዳሰሳ ዘ ማለዳ (ጥር 25/2012)

Views: 259

ባሳለፍነው ሳምንት በሁከት ውስጥ የነበረቸው ሐረር ከተማ ዛሬ ጥር 25/2012 አንፃራዊ  መረጋጋት ቢታይባትም ነዋሪዎቹ ግን ከሥጋት ነጻ አለመውጣታቸውን ለአዲሰ ማለዳ ተናገሩ። በዚህም ሳቢያ ቁጥራቸው 200 የሚጠጉ ነዋሪዎች በሥጋት በከተማው በሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን ተጠልለው እንደሚገኙ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪዎች ተናግረዋል። በከተማው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት፣ ባንኮች እንዲሁም ወደ አዲሰ አበባ የሚወስዱ መንገዶችን ጨምሮ መከፈታቸውንና በከተማውም የትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። በአሁን ወቅት በከተማዋ የክልሉን ልዩ ኃይል ጨምሮ ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች በስፋት እንደሚታዩም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ከዚህ በኋላ ‹‹ምን እንደሚፈጠር ምንም እርግጠኛ አይደለንም›› ብለዋል። ባሳለፍነው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞን የቴሌኮም አገልገሎት  መቋረጥና መንግሥት በነዋሪዎቹ ላይ የሚወስደውን እርምጃ ለመቃወም በተደረገ እንቅስቃሴ በሐረር ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት መፈጠሩ ይታወሳል። (አዲሰ ማለዳ)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

ሶማሊያ በከፍተኛ ሁኔታ አዝርእትን ሊያወድም የሚችለው አንበጣ በሶማሊያውያን የምግብ ደኅንነት ላይ አደጋ ደቅኗል በማለት የብሔራዊ አደጋ አዋጅ ማወጇን የሶማሊያ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። የተባበሩት መንግሥታት በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ የተከሰተው መንጋ በአገራቱ 25 ዓመታት ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው ያለ ሲሆን፣ ምርት ከሚሰበሰብበት ሚያዚያ ወር በፊት የአንበጣ መንጋውን በሶማሊያ ለመቆጣጠር እንደማይቻል ተነግሯል። በተመሳሳይ በኬንያ ይህን መሰል የአንበጣ መንጋ መከሰቱን የምግብ እና ግብርና ድርጅት (ፋኦ) የጠቀሰ ሲሆን፣ ኬንያ ችግሩ ሲገጥማት ከ70 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ይፋ አድርግዋል። በሶማሊያ ባለው የጸጥታ እክል በአውሮፕላን በመታገዝ ጸረ አንበጣ መድኃኒት ርጭት ማካሄድ አልተቻለም። (ቢቢሲ)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

ቁጥራቸው እየበዛ የመጣው ኢትዮጵያውያን የሆኑ ቤተ እስራኤላውያን እና የሩስያ ስደተኞች አይሁዳውያን ናቸው ተብለው ወደ እስራኤል መግባታቸው ትክክል እንዳልሆነ እና እስራኤልንም የአይሁድ መንግሥት ናት ብለው እንደማይቀበሉ የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት መሐሙድ ኣባስ ተናገሩ። አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን የነበሩት ሩስያውያን በአሁኑ ወቅት ኹለት ሚሊዮን መድረሳቸውን የጠቀሱ ሲሆን፤ ቀደም ሲል ቁጥራቸው አነስተኛ የነበረው የቤተ እስራኤላውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም አስታውቀዋል። የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ሬዩቭን ሪቪሊን በበኩላቸው ‹‹የአይሁዳውያን መንግሥት እኛ ነን እንጂ ሌላ መንግሥት የላቸውም። ሁሉም ዜጎች ለእኛ አኩል ናቸው።›› ሲሉ ምላሻቸውን ለፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት መስጠታቸውን ታይምስ ኦፍ እስራኤል አስታውቋል። (አዲሰ ማለዳ)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በሕገወጥ መንገድ የኢትዮጵያን ፓስፖርት ለማግኘት የሞከሩ ከ20 በላይ የጎረቤት አገራት ዜጎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን  አስታወቀ። በሕገወጥ መንገድ ለውጭ ዜጎች የተሰጡ 29 ፓስፖርቶችም በኤርፖርትና በኢንተርፖል ዳታ ቤዝ ውስጥ በማስገባት አገልግሎት እንዳይሰጡ መደረጉ ተጠቅሷል። የኢምግሬሽን የዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ደሳለኝ ተሬሳ እንደገለፁት፤ ከ20 በላይ የጎረቤት አገር ዜጎች የተለያዩ ማስረጃዎች፤ ማለትም የቀበሌ መታወቂያና የልደት ሰርተፊኬት በማቅረብ በሕገወጥ መንገድ የኢትዮጵያን ፓስፖርት ለማግኘት ሲሞክሩ በኤጀንሲው ሠራተኞች ተይዘው በሕግ ተጠያቂ ሆነዋል። (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኮሮና ቫይረስ አራት ሰዎች ተጠርጥረው በለይቶ ማቆያ ማአከል ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ገለጸ። ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ሦስቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ በቦሌ ጨፌ ለይቶ ማቆያ ማእከል ክትትል እየተደረገላቸው ነው ተብሏል። ሌላኛው ተጠርጣሪ ቻይናዊ ሲሆን እርሱም በአክሱም ለይቶ ማቆያ ማእከል ክትትል እየተደረገለት እንደሆነ ተገልጿል። የአራቱም ተጠርጣሪዎች የደም ናሙናቸው ተወስዶ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ ዝግጅት መጠናቀቁንም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል። ባሳለፍነው ሳምንት አራት በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ ኢትዮጵያውያን፣ በለይቶ ማቆያ ማእከል ክትትል ሲደረግላቸው ቆይተው፣ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኮ የተመረመረው የደም ናሙና ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን በማረጋገጡ ከማእከሉ መውጣታቸው ይታወሳል። (አዲሰ ማለዳ)
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን በይፋ ለመመስረት የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የመስተዳድሩ የሕዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገነነ አበራ ተናገሩ። በአሁኑ ወቅትም የክልሉን ሕገ መንግሥት ማርቀቅን እና በታችኛው እርከን የሚኖረውን የአስተዳደር መዋቅር ማዘጋጀትን ጨምሮ የክልል ምስረታውን ለማከናወን የሚያስፈልጉ ቅደመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አስረድተዋል። የክልላዊ መንግሥት ምስረታውን ወደ ተግባር ለማሸጋገር የብሔሩ ምሁራንና የፖለቲካ ሊኂቃንን ጨምሮ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አባላት የተካተቱበት ራሱን የቻለ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ የዝግጅት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል። (ዶቸቬለ)
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል የከተማ አስተዳደሩ በተጠባባቂነት ልዩ ተብለው የሚያገለግሉ 20 ፈጥኖ ደራሽ አዳዲስ አውቶቡሶችን ዛሬ ጥር 25/2012 ሊያስገባ መሆኑ ተገለፀ። እስከ አሁን የነበረው አሰራር ተሽከርካሪዎችን ከመስመር ላይ በማዞር ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ባለበት አካባቢ እንዲሰማሩ ማድረግ እንደነበር በመግለፅ፤ አሁን ግን እነዚህ ልዩ ተብለው በተጠባባቂነት የሚገቡት 20 አዳዲስ አውቶቡሶች ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ባለበትና ሰልፍ በበዛበት በየትኛውም አካባቢ ተዘዋውሮ ለመሥራት የተዘጋጁ መሆናቸውን ገልፀዋል። (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com