የኖቤል ሽልማት በተለያዩ ዘርፎች መሰጠት ከተጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። በእነዚህ ዓመታት በሳንይስም ሆነ በተለያዩ ዘርፎች አስተዋጽኦ ላደረጉ ሰዎች ከሚሰጠው የዕውቅና ሽልማት በላይ፣ የብዙዎችን ትኩረት የሚይዘው ለሠላም ላበረከቱት አስተዋጽኦ እየተባለ በየዓመቱ ሽልማቱ የሚሰጣቸው ግለሰቦች ናቸው።
ኔልሰን ማንዴላን ለመሳሰሉ ዕውቅ ሰዎች መርጠው ሽልማቱን የሚሰጡት ምዕራባውያኑ በመሆናቸው የእነሱን ዕይታ ብቻ ያማከለ ወገንተኝነት የሚታይበት እንደሆነ ብዙዎች ስሞታ ሲያቀርቡ ይሰማል። ለምሳሌ፣ የነፃነት ተምሳሌት ተደርገው በብዙዎች ዘንድ የሚሞገሱትን ኔልሰን ማንዴላን የሸለሙትና መልሰው መላልሰው የሚያደንቁት፣ ነጮች ጥቁሮች ላይ የሠሩትን ግፍ ጭቁኖችን ወክለው በጅምላ ያለ ካሳ ይቅር ስላሉ ነው ብለው የአድናቂዎቻቸውን ተንኮል የሚያነሱ አሉ። በአንጻሩ እነ ሮበርት ሙጋቤ ለዓመታት አገራቸውን በሠላም አኑረው፣ አላግባብ በልጽገው የነበሩትን የቅኝ ገዢ ወራሾች ሀብት በመንጠቅ ለድሃው ፍትሓዊ በሆነ መንገድ ለማከፋፈል በመሞከራቸው የተነከሰባቸው ጥርስ እስካሁን አልተላቀቀም።
አፍሪካን በጠላትነት የሚመለከት ወገን ለአፍሪካ የሠራን ሳይሆን ለእነሱ የሠራን አድንቀው ኹሉም እንዲያደንቀው መሞከሩ የተለመደ ነው። በሌላ በኩል፣ የሕዝብ ድጋፍ ያለው መሪንም ሆነ ግለሰብን ሆን ብሎ ማኖ እንደማስነካት፣ ይሸልሙና ወይም ያደንቁና በፈለጉበት መንገድ እንዲሄድ ቦይ ሲቀዱለትም ይስተዋላል። ከእንዲህ ዓይነት ተሸላሚ፣ አሊያም ከእንዲህ ዓይነት ባለሙያ እንዲህ ማድረግ አይጠበቅም እያሉ ከዜጎቻቸው የማይጠብቁትን ሌላው ላይ ጫና ለመፍጠር ይጠቀሙበታል።
ጥሩ ስም የሌለው ለስሙ ይጨነቃል ብለው ስለማይጠብቁ፣ ስም ሰጥተው በማጀገንም ወይም ያለምክንያት ዝናን በመስጠት ስሙ እንዳይጠፋበት የሥነ-ልቦና ጫና ለማድረግ እንደሚሞክሩም የሚናገሩ አሉ። የኖቤል ሽልማት የተሰጠውም፣ “እንዲህ ማድረግ የለበትም” እያሉ አገር እየወደመም ቢሆን፣ ጦር ማዘዝ የለበትም የሚል ዕሳቤ ያለው አጀንዳን ሲያራምዱ ማየት የተለመደ ነው። በቅርቡ በማይናማሯ አንሳን ሱኪ ላይ ተመሳሳይ ከሕዝቧ የማራቅ ተግባር ሊፈፅሙ መሞከራቸውን እየጠቀሱ የሚናገሩ አሉ።
የሩዋንዳውን ዕልቂት ያስቆሙትና አገራቸውን ከዘመናት ጦርነት አውጥተው ወደ ሠላም ያሸጋገሩት ፖል ካጋሜ የኖቤል ሽልማት እስካሁን ያልተሰጣቸው ፈረንሳይና አጋሮቿ ዘመናዊ ቅኝ ግዛትን ለመቀጠል የሚያደርጉትን ቀድመው ተረድተው ስለተጋፈጡዋቸው መሆኑን ጉዳዩን የሚከታተሉ ይናገራሉ።
ስለኖቤል ሽልማት ይህን ያህል ያልናችሁ ሠሞኑን የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር በምዕራባውያን ሚዲዎች “ተሸላሚ የጦር ዘማች ሆነ” የሚል የማሸማቀቅ ዓላማ ያለው ዘገባ ማውጣታቸውን ተከትሎ የነበረውን ሁኔታ መነሻ በማድረግ ነው። ፈንጂን ፈብርኮ ብዙ ሰው እንዲጨረስበት ምከንያት በሆነ ሰው ስም የሚሰጥ ሽልማትን የወሰደ ሰው፣ እንዴት ለአገሩ ሲል ይዘምታል ሲሉም በርካታ ምላሽ አስተናግደዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ያስገኘው ሠላምን የሚያደፈርስ ሲመጣ እያየ ዝም ብሎ አገሪቱ በጦርነት ስትታመስ ማየት ለሠላም መቆም የመሰላቸው ካሉ ሽልማቱ ጥንቅር ብሎ ይቅር በማለት የተናገሩ አሉ። አንዳንዶች ሽልማቱ ከፈለጉ ይመለስላቸው ቢሉም፣ ኹለተኛ ዙር መጠበቅ እንጂ የምን መሸነፍ ነው፤ ወንድ ከሆኑ መጥተው ለመንጠቅ ይሞክሩ ሲሊ የተደመጡም አሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014


