ማኅበራዊ ፍርሃት (ሶሻል ፎቢያ)

0
973

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ያምሮት የኹለተኛ ዲግሪዋን ልታጠናቅቅ አሥራ አንደኛው ሰዓት ላይ ነች። የመመረቂያ ጽሁፏን በጥንቃቄ ጨርሳ ለማቅረብ ደፋ ቀና እያለች ከርማ እነሆ ቀኑ ደረሰ። በዕለቱ በመንፈስም በሞራልም እራሷን አዘጋጅታ ጥናቷን ወደምታቀርብበት ክፍል ገባች። ልክ ወደክፍሉ እንደገባች፣ 4 ዶክተሮች ከአማካሪዋ ጋር ተሰይመው በትኩረት ይከታተሏታል። ኮምፒውሯን ለመክፈት ወደጠረጴዛው ስታመራ፣ እግሯ አልታዘዝ አላት። እንደምንም ኃይሏን አሰባስባ፣ ጠረጴዛውን ተጠጋችና ኮምፒውተሯን ከፈተች። የከፈተችበት እጇ የከዳት መሰላት። ልቧ በአፏ አፈትልኮ ሊወጣ ተናነቃት። ኹኔታዋን ለተመለከተ፣ ጥናቷን ልታቀርብ የተዘጋጀች ሳይሆን ፣ ፍርድ ቤት ቆማ የሞት ፍርድ ሊፈረድባት የተዘጋጀች ምስኪን ሴት አስመስሏታል።

አስተማሪዎቿ ትዕግስታቸው በመሟጠጡ ፣ ጥናቷን ይዛ እንድትወጣ፣ በተጨማሪም ራሷ የሠራችው እንዳልሆነ አስረግጠው ነገሯት። ያምሮት፣ ጥናቱን የሠራችው እራሷ እንደሆነች ብታውቅም፣ ይሄንን ለአስተማሪዎቿ ለማስረዳት አንድ ቃል ማውጣት ስላቃታት እንደሌባ ኮስምና ከክፍሉ ወጣች። በቀጥታ ወደቤተክርስቲያን በመሄድ ስቅስቅ ብላ አለቀሰች። በዶክተር ዮናስ ላቀው ከተጻፈው የአማኑኤል ሆስፒታል እውነተኛ ታሪኮች ላይ የተወሰደ ነው።

ማኅበራዊ ፍርሃት (ሶሻል ፎቢያ) አንድ ሰው በዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴው በራስ አለመተማመን፣ ራሱን ለሚኖርበት ማኅበረሰብ መግለጽ አለመቻል ማለት እንደሆነ፤ በተለያዩ የስነልቦና መፃህፍት ላይ ሰፍሮ ይገኛል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ሰዎች ዕውቀት ሳያንሳቸው፣ የሠሩትን ሥራ በአግባቡ መግለጽ ተስኗቸው ፣የጋን ውስጥ መብራት በመሆን ቀርተዋል።

የልጆች አስተዳደግ ለዚህ ቀውስ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ምሁራን ይስማሙበታል። በኢትዮጵያ የልጆች አስተዳደግ ፣ በተለይ ሴቶች በቤት ውስጥ እንዲቆዩና በጫና እንዲያድጉ መሆኑ የአደባባይ ሐቅ ነው። ሴት ልጆች ፣ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ከመሥራት በዘለለ ፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በነጻነት እንዲወያዩ እና ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ሲደረጉ አይስተዋልም። ያምሮት ከገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል በመምጣቷ የማኅበራዊ ፍርሃት ተጠቂ ሆናለች።

ይሄንን ችግሯን የተረዳ ጓደኛዋ፣ የሥነ-ልቦና ሐኪም ብታገኝ እንደምትድን ስለነገራት ፣ መፍትሔ ለማግኘት ወደ ሐኪም ዘንድ ሔዳለች። ሕክምናውን በሚዋጥ መድኃኒት ጀመረች።መድኃኒቱ ሰውነትን ዘና የማድረግ አቅም ስለነበረው ፣ ለአንድ ወር ወስዳ፣ የጤና መሻሻል ስላየች እንድታቆም ሆነ። በመጨረሻ፣ የሥነ-ልቦና ማማከር ሕክምና ወስዳ ተሽሏት ወደቀደመ ሕይወቷ ልትመለስ ችላለች። ማኅበራዊ ፍርሃት በዓለም ከ10 ሰዎች 1 ሰው ላይ የሚታይ የሥነ-ልቦና ችግር እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። መፍትሄው በሥነ-ልቦና ሕክምና እጅ ውስጥ እንዳለ ከላይ የተገለጸው ታሪክ ማሳያ ነው። ሴቶች በማኅበራዊው፣ በኢኮኖሚው እና በፖለቲካው ተሳታፊ ሆነው የራሳቸውን አሻራ እንዲያበረክቱ፣ ወደአደባባይ ወጥተው እራሳቸውን መግለጽ እንዲችሉ አቅማቸውን መገንባት አገርን መገንባት ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here