ዳሰሳ ዘ ማለዳ (ጥር 28/2012)

Views: 574

በአዲስ አበባ 120 አዳዲስ አውቶቡሶች ስራ ጀመሩ

የአዲስ አበባ ከተማን የትራንስፖርት ክፍተት የሚሞሉ አዲስ 120 አንበሳ አውቶብሶችን ወደ ስራ ማሰማራቱን አስታወቀ። በከተማዋ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ካስገባቸው አዲስ የአንበሳ ከተማ አውቶቡሶች 20 ዎቹ በልዩ ሁኔታ የሚሰማሩ ናቸው ተብሏል።በልዩ ሁኔታ አገልግሎት የሚሰጡት 20 አውቶቡሶች የትራንስፖርት ችግሩ በሚባባስበት ጠዋት ስራ መግቢያና ማታ ስራ መውጫ ሰዓት ላይ በተሻለ ሁኔታ ፈጥነው በመድረስ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የባለስልጣኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ መልካሙ ሌሊሳ ገልጸዋል።(ኢቲቪ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በኢትዮጵያ የበረሃ አንበጣን ለመከላከል ሁለት አለም አቀፍ ድርጅቶች አንድ ሚሊዮን 300 ሺ ዶላር ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሆነ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።የገንዘብ ድጋፉ የሚገኘውም ከአለም ምግብና እርሻ ድርጅት/ፋኦ/ እና ከአሜሪካ አለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ/ዮኤስኤድ/ እንደሆነ በሚኒስቴሩ የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር  ዘብዲዎስ ሰላቶ  ተናግረዋል።ቃል የተገባው የገንዘብ ድጋፍም ለመድሀኒት መርጫ መሳሪያዎች፣ ለፀረ-ተባይ መከላከያ ትጥቅ እና ለመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች ግዢ ይውላል።ፀረ-አንበጣ መድሀኒት የሚረጩ የአውሮፕላኖችን ኪራይ ለመሸፈን፣ በዘርፉ ለሚሰሩ ባለሞያዎች ስልጠና ለመስጠት እና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ ያለመ እንደሆነም ዘብዲዎስ ተናግረዋል።ከድርጅቶቹ ጋርም የድጋፍ ስምምነት ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።(ኢቲቪ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

አንድነት ፓርክ ከመጪው ቅዳሜ ጥር 30 ጀምሮ እስከ ረቡዕ የካቲት 4 ድረስ ለጎብኚዎች ዝግ እንደሚሆን ተገለጸ።በእነዚህ ቀናት ፓርኩን ለመጎብኘት ትኬት የቆረጡ ጎብኚዎች ከሀሙስ የካቲት 5 ጀምሮ ጉብኝታቸውን  ማከናወን እንደሚችሉ ፓርኩ ገልጿል።በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ የመጡትን እንግዶች የአንድነት ፓርክን ጨምሮ በከተማዋ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስጎብኘት ዝግጅት መጠናቀቅ መገለጹ ይታወሳል።(ኢዜአ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

አዲሱ የአፍሪካ ህብረት መዋቅር የሚደረግ ሽግግር ግልጽነትን ያረጋገጠ እና የሰራተኞችን መብት ከግምት ያስገባ መሆን አንዳለበት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።የአፍሪካ ሀብረት የመዋቅር ማሻሻያ የደረሰበትን ደረጀ በተመለከተ በተዘጋጀው ሪፖርት ላይ የህብረቱ አስፈጻሚ ምክር ቤት ውይይት አድርጓል። በቀረበው ሪፖርት ላይ የአባል አገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አስተያየታቸውንም ሰጥተዋል።የኢፊዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስርትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት የህብረቱ የመዋቅር ማሻሸያ በመሪዎች ጉባኤ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ግቡን እንዲመታ ግልጽነትን ባረጋገጠ መልኩ እና የሰራተኞችን መብት ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መከናወን አንዳለበት አሳስበዋል። (አዲስ ማለዳ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

የኢትዮጰያ አየር መንገድ የአውሮፕላን ጥገናን በጋራ መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት አቡዳቢ ከሚገኘው ሳናድ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር ተፈራረመ ። ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሃገራትም ጭምር የአውሮፕላን ጥገና በጋራ ለማከናወን የሚያስችል ነው ሲሉም የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ተናግረዋል።ስምምነቱ ለቀጣዮቹ 15 ዓመታት የሚቆይ ሲሆን  ከኩባንያው ጋር በትብብር ለመስራት ከስምምነት መደረሱ  የቴክኖሎጂ አቅምና ልምዱን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ሲሉም አክለዋል።የሳናድ ዋና ስራ አስፈፃሚ  መንሱር ጃንሀዲ በበኩላቸው በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ትብብር ከኢትዮጰያ አየር መንገድ ጋር በማድረጋችን ደስተኞች ነን ብለዋል።(አዲሰ ሚዲያ ኔትወርክ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ስድስት ወራት ከ104 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን ገለፀ።ለመፍጠር ታቅዶ ከነበረው አንፃር ማሳካት የተቻለው 93 በመቶውን እንደሆነ የስራ እድሉን ካገኙት መካከል 83 በመቶ ወጣቶች ሲሆኑ ሴቶች ደግሞ  የ45ነጥብ 99 በመቶ ድርሻ  አላቸው።የሥራ ዕድል ከተፈጠራለቸው መካልም የዩኒቨርስቲና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሲገኙ በጊዜ ማዕቀፉ ለ317 አካል ጉዳተኞች የስራ እድል ማመቻቸቱን ቢሮው በሪፖርቱ ጠቅሷል።ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ የከተማ ግብርና፣ ንግድ እንዲሁም አገልግሎት ዘርፉ፣ በግልና የመንግስት ተቋማት የስራ እድሉ የተገኘባቸው መስኮች ናቸው ተብሏል።በ6 ወራት ውስጥ ተደራጅተው ወደ ስራ ለገቡ ኢንተርፕራይዞች ከ877 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ለማቅረብ ታቅዶ ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ተሰጥቷል።(ሸገር ኤፍ ኤም)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በዓመት ከአንድ ቢሊየን በላይ እንክብሎችና ሽሮፖችን ማምረት የሚያስችል የመድኃኒት ፋብሪካ ሊገነባ መሆኑ ተነገረ። ዛሬ ጥር 28/2012 የመሰረት ድንጋይ የተጣለለት ይህ ፋብሪካ በ10 ሚሊዮን ዶላር መነሻ ካፒታል በአገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ባለሃብቶች በጋራ ይገነባል። አፍሪክዩር የተሰኘው ይህ የመድኃኒት ፋብሪካ ግንባታ ከ18 እስከ 24 ወራት ባለው ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሏል። ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር አንድ ቢሊዮን እንክብሎችንና ሽሮፖችን በዓመት በአንድ ፈረቃ የሚያመርት እንደሚሆን ተገልጿል። ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባም ለ109 ሰዎች የስራ ዕድል ይፈጥራልተብሎም ይጠበቃል።(ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com