በ‹#በቃ!› ንቅናቄ እሴቶቻችንንም እንጠብቃቸው!

0
1349

ተፈጥሮና ሥነ ምኅዳር በብዝኀነት ላይ ሊኖራቸው ከሚችለው ቀጥተኛ ተጽእኖ ባሻገር፣ የሰዎች አመለካከትና ማኅበራዊ ስሪት የዓለም የብዝኀነት ምክንያት እንደሆነ ይታመናል። እንጂ በሐይማኖትም ሆነ በዝግተ ለውጥ የሰው ልጅ መነሻው አንድ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህ ማለት ዜጎች በየአገራቸው ባገነኗቸው እሴቶችና አመለካከቶች ይገነባሉ ማለት ነው። መቅደስ ቹቹ ይህን ነጥብ መነሻ አድርጋ፣ አገራት በጦርነትና በኢኮኖሚ ከሚያስከብሩት ሉዓላዊነት ጎን ለጎን የተገነቡበትን እሴት አጥብቆ በመያዝና በማስተዋል በተመሳሳይ ሉዓላዊነታቸውን ማስከበር ይችላሉ ብላለች። ይህንንም እንደሚከተለው አጋርታለች።

ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ከምንም በላይ የሚያስቀድሙ ስለመሆናቸው የታሪክ ጸሐፍት በተለያየ አጋጣሚ ባሰፈሯቸው ጽሑፎች ጠቆም አድርገዋል። ከዛም አልፎ ክብራቸውን አስጠብቀውና ሉዓላዊነታቸውን ሳያስደፍሩ ሲኖሩም፣ የሚመሩባቸውና የሚግባቡባቸው እሴቶች ጠንካራና ዘመናትን የተሻገሩ ነበሩ። ይህንንም ዘመናት በዘለቀ ሥነ ቃልና ብሂል ውስጥ ከትበዉት፣ ትውልድ በቃልም በተግባርም ሀብቱ እንዲያደርጋቸው አሻጋግረውታል።

አሸናፊነትን መላበስ የኢትዮጵያውያን እሴት ነው። ‹አሸናፊ ነን! ጀግና ነን! አገራችንን ለማንም አናስደፍርም!› የሚለው የሥነልቦና ብርታት ትልቅ ዋጋ አለው። ይህ የተወረሰና ትውልድ የተቀባበለው ነው። እንደዛው ሁሉ ፍትህ፣ ታማኝነት፣ መስዋዕትነት፣ መከባበር፣ መደጋገፍ ወዘተ የአትዮጵያዊያን የተከበሩ እሴቶች ናቸው።

ኢትዮጵያዊ ካልነኩት የማይነካ፤ ከነኩት ግን እስከ ጥግ ድረስ የሚፋለምና የማይመለስ ነው። ‹በፍትህ ከተወሰደ በሬዬ፣ ያለፍትህ የሄደች ጭብጦዬ!› ይላል። የእውነትና የፍትህ ወገንተኛ ነው። ይህም ነው እስከዛሬ ድረስ ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት በተለየ ነጻነቷን ጠብቃ እንድትቆይና ምሳሌ እንድትሆን ያስቻላት። እውነትን የሙጥኝ ያለ ወድቆ አይወድቅምና!

ይህን ለመግቢያ አነሳሁ እንጂ እሴቶቻችን ኢትዮጵያዊ ስንል አብረው የሚከሰቱ የማንነት ምስሎች ሁሉ ናቸው። እሴት በቁስ አካል የሚመዘን ሳይሆን መንፈሳዊ ሀብት ጭምር ነው። እሴት የሌለው ሕዝብ እንደ ባዶ ሳጥን ነው፤ ያኖሩበትን ሁሉ ይቀበላል። እናም እንዲህ ያለውን ከእሴቱ የተፋታን አገር በቅኝ ግዛት ውስጥ ለማኖር በኢኮኖሚና በጦር ኃይል ማንበርከክ የመጨረሻው ቀላሉ ሥራ ነው የሚሆነው። ለምን ቢሉ፣ ቀድሞ ሥነልቦናውም ለውድቀት የተመቻቸና የሚቆምበት እሴት የተባለ መሠረት የለውምና ነው።

እሴቶቻችን ከየት የተቀዱ ናቸው? ኢትዮጵያውያን ብዙውን ጊዜ እሴቶቻችን የተቀዱትና የሚቀዱት ከባህልና ከሃይማኖት ነው። ታድያ እነዚህን እሴቶች ስንነጠቅና ስናጣቸው መጀመሪያ የምናጣው ለራሳችንን ያለንን ክብርና ዋጋ ነው የሚሆነው። ከዛም ብንፈልግም ባንፈልግም ለሌሎች ተላልፈን የተሰጠን እንሆናለን።

ዐይናቸውና ልባቸው የአፍሪካን ብርሃናማ ቀን ማየት የማይሻ መንግሥታት፣ በቅኝ ግዛት ወቅት አፍሪካ ብዙ እሴቶቿን እንዳትጠቀም አድርገዋታል። ይህም ቁሳዊ እንዲሁም መንፈሳዊ ሀብትን የሚጨምር ነው። እነዚህ ቅኝ ገዢዎች መጀመሪያ ያደረጉት ማዕድን ፍለጋ መሬት መቆፈር ወይም ጉልበት ብዝበዛ ጥቁሮችን ማፈስ አልነበረም። መጀመሪያ የአገራቱ ዜጎች በራሳቸው ማንነት እንዳይኮሩና የራሳቸውን አሳንሰው እንዲያዩ ነው ያደረጓቸው፤ እሴቶቻቸውን ነው የነጠቋቸው።

እሴት እንዴት ይነጠቃል ብለን እንጠይቅ ይሆናል። እንዲህ ነው፤ እንደሚገባኝ ከሆነ ‹ሠለጠንን› የሚሉ አገራት ሐይማኖት ዋጋ እንደሌለው አድርገው ለመሳል ቀን ከሌት ይለፋሉ። ባህልን ቅርስ አድርገዉት ከመጎብኘት የዘለለ የሰው ልጆች ሀብት መሆኑን እምብዛም ልብ አይሉትም። የሚያሳዝነው እኛም ይህን ተከትለን የራሳችንን ባህላዊ፣ የእነርሱን የሠለጠነ፤ የራሳችንን ኋላቀር የእነርሱን ዘመናዊ ብለን አንጠራለን። እነርሱ ‹እንዲህ በሉ!› ብለው ነግረውን አይደለም፤ ይህን እንድናስብ አድርገው ግን እየሠሩን ነው።

አውሮፓውያን ነጻነትን በእነርሱ እንድንለካ ይፈልጋሉ። ዘመናዊነትን ከምዕራባዊነት አንጻር ብቻ እንድናስብ ተደርገናል። የራሳችን የሆነውን ሁሉ ባህላዊና ኋላቀር እያልን የምንጠራ ነን። ይህን የምንልበት ሚዛን ትክክል ሆኖ ቢሆን ጥሩ ነበር። ነገር ግን ሚዛናችን አውሮፓና አሜሪካ ወይም የእነርሱ ሆሊውድ የሠራው ፊልም ነው መለኪያ መስፈርታችን።

ይኮረጃልኮ! ዓለም ዛሬ ላይ ደረሰችበት ሥልጣኔ በመወራረስና በመቀባበል ነው እዚህ የደረሰው። ሉላዊነት የበረታውና ‹ዓለም አንድ መንደር ሆነች!› ያሰኘኝ እነዚህ የምንጋራቸው አገር ከአገር የተዋዋሷቸው ጉዳዮች ናቸው። እናም እኛ ጋር ካለው የተሻለ ነገር ስንመለከት መኮረጅ ወይም መቅዳት ደንብ ነው። ግን ይህም በራሳችን መልክ ሊሆን የሚገባ ነው።

በቀደመው ጊዜ እንዲሁም ቅርብ በሚባሉ ዓመታት ከውጪ የሚመጡ ቃላትን ወደ አገርኛ ቀይሮ ወደ ጥቅም ማዋል የተለመደ ነበር። ይህንንም ለማድረግ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ምሁራን ከፍተኛ ሱታፌ ያደርጉ ነበር። ይህን በሚመለከት የሚሠራም ጉባኤም ነበር። አሁን ይህን ተነጥቀናል። እናም በራሳችን በየትኛውም ቋንቋ መግለጽ ተስኖን በፈረንጅ አፍ የምንጠራቸው ነገሮችና ነጥቦች በዝተዋል።

እሺ ቀላሉ ምሳሌ፤ አለባበሳችንን እንመልከት። ጤነኛ ኩረጃ ቢሆን የልብስ መልኮችን ወይም ዲዛይኖችን ከውጪ መዋስ ምንም ማለት አልነበረም። እንደው ባህልና ያከብራል፣ ተቀባይነት አለው ወይ የሚለውን ብናቆይ እንኳ፣ ስንኮርጅ መልኩን ብቻ ብንዋስና ጨርቁን ከራሳችን ብናደርግ ጥሩ ነበር። ግን ለምን? ዲዛይኑንም ጨርቁንም የምናመጣው ከዛው ነው። ሥልጣኔ ሊኮረጅ ይችላል፣ ዘመናዊነትንና ከጊዜው ጋር አብሮ መሄድን ከሌሎች ልንማር እንችል ይሆናል። ግን እንዲህ ባለ መልኩ ከሆነ ዋጋም የለው!
የእነርሱ ነገር ሁሉ ከእኛ የተሻለ፣ ከእኛ ነገር ሁሉ አንድም የሚመረጥ ነገር የሌለ ይመስለናል። ስህተቱ እዚህ ላይ ነው! ይህ ራሳችንን ዝቅ የማድረግና ቸል የማለት ጉዳይ እሴቶቻችንን እንዳናከብርና ምንም ሆነው እንዲታዩን የሚያደርግ ነው።

‹#በቃ›!
በኢትዮጵያ የተጀመረው የ‹#በቃ› እንቅስቃሴ አሁን ዓለምን እያዳረሰ ነው። ይህም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ እንዲሁም ሉዓላዊነት ላይ የተሰነዘረውን የውጪ አገራትን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሆኖ የተነሳ ነው። በኢኮኖሚ የእነርሱ ባሪያ መሆን ይብቃ! በእርዳታ ሰበብ የሚያደርሱት ተጽእኖ ያቁም የሚል አንድምታ ያለውም ነው። ይህንንም በርካታ የአፍሪካ አገራት ሲጋሩት ታዝበናል።

መቼም ይህም ቀን ማለፉ አይቀርም! ይሄኔ ልብ ብለን መመልከት ያለብን እንደ አገር ሉዓላዊነትና ክብር እሴትንም በዛ መንፈስ መጠበቅ እንደሚገባን ነው። አሁን ላይ አገራችን ነጥቀው መልሰው ‹ሰላማዊ አገር እንስጣችሁ! አገራችሁን ሰላም እናድርግ! አገራችሁን ሀብታምና ያደገች እናድርግ› እንደሚሉት ሁሉ፣ አሁን ነጥቀውን ነገ ደግሞ የሚሰጡን እሴት ብዙ ነው። ነጥቀው ሲሰጡን ደግሞ ብዙ ዋጋ ያስከፍሉናል።

ትዝ ይለችሁ እንደሆነ…በአገራችን የባቡር አገልግሎት ሥራ የጀመረ ሰሞን በድምጽ ማጉያው የሚወጣ አንድ መልእክት ብዙዎችን ያበሳጭ ነበር። ይህም ‹እድሜያቸው ለገፋና ለነፍሰ ጡሮች ከወንበራችሁ ተነሱ› የሚል ነበር። ይህ ታላቅን የማክበር እሴት ለኢትዮጵያውያን እንግዳ ነገር አይደለም። ግን ለምን ይህን በየባቡሩ ማስታወስ አስፈለገ? ነገሩን መንቀፌ አይደለም። የሰው አክባሪነት ቁንጮ ነን፣ ነጋሪ አያሻንም ልላችሁ አይደለም። ነገር ግን እንዲህ ቀላል በሚመስል መልኩና ትንሽ በሚመስል ደረጃ እሴትን ነጥቆ መልሶ እንካችሁ ሊባል እንደሚችል ማሳያ እንዲሆን ብዬ ነው።

አሁን ‹በዴሞክራሲ ስርዓት ፍጽምት ነኝ› የምትል በሚያስመስላት ተግባር ውስጥ የምትገኘው አሜሪካ፣ በጉያዋ የጥቁር አሜሪካውያን ስቃይና መከራ ይከሰታል። እንዲያም ሆኖ ግን ጥቁሮች ሄደው እድል የሚያገኙባት አገር መሆኗን ለማሳየት አንድ ፕሬዝዳንት የነበረውን ባራክ ኦባማን ትጠቅሳለች። ነገር ግን እንደ ጆርድ ፍሎይድ ያሉ ብዙ ጥቁር አሜሪካውያን በየእለት የሰቀቀን ሕይወትን እንደሚኖሩ ይታወቃል። ነገሩ ግን ‹አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ!› ዓይነት ስለሆነ አሜሪካንን ወዴት ሄደው ይከሷታል?

እንግዲህ እነርሱን መከተል እንደሌለብን ከዚህ በላይ ምልክት አያሻም። ወደድንም ጠላንም በድህነታች ብቻ ሳይሆን ባለማወቃችን ውስጥም በቀኝ ግዛታቸው ስር አኑረውናል። ቀን ሲወጣ ይህንንም ተጽእኖ በቃ ብለን፣ ከእነርሱ ጋር ሳይሆን ከራሳችን አመለካከትና አስተሳሰብ ጋር ልንሞግት ይገባል። የራሳችንን እሴት ጠብቀን በማሻገር ውስጥ ብቻ ነው አገሩን የሚያከብርና የሚያስከብር ትውልድ ልናገኝ የምንችለው።

አገራችንን ዳር ድንበር እንደምንጠብቅና ደኅንነቷ እንደሚያሳስበን ሁሉ፣ እንደ ማኅበረሰብ የተሠራንበት እሴት ሲላላ ዝም ማለት የለብንም፤ እንዲላላም እድል መፍጠር አይገባም። ልብ በሉልኝ! እኛ ኢትዮጵያውያን መላዕክት ነን፣ ፍጹማን ነን ማለቴ አይደለም፤ እንደዛ አይደለንምም። ነገር ግን የእኛ የሆኑና ጠንካራ የሚባሉ እሴቶች አሉን። ድክመቶችም የዛን ያህል ይኖሩብናል፤ ብዙ መሻሻል ያለበት ስርዓት አለን።

ይህን ግን የምናሻሽለው መጀመሪያ ችግሩን በማወቅ፣ ከዛም አገራዊ መፍትሄ በማበጀት ብቻ ነው። በእርዳታ አገር እንደማይለወጥ ሁሉ፣ ከውጪ በምናገኘው ‹እሴት› በሚመስለን አመለካከት ችግሮቻችን መፍትሄ አያገኙም። የሥነ ልቦና እና ሥነ አእምሮ ሰዎች በሚሰጡት የንግግር ሕክምና ላይ አጉልተው ከሚያነሱት ነጥብ መካከል አንደኛው ታካሚያቸው ለራሱ ያለውን አመለካከት እንዲያስተካክልና ጥሩ እንዲያደርግ ማበረታታት ነው። ታካሚው ወይም ምክር የሚያስፈልገው ሰው በራስ መተማመን፣ ራስን መውደድ፣ የራስን ነገር ማክበር እሴቱ እንዲያደርግ ይመክሩታል።

እንደ አገርም ይህ በሚገባ የሚያስፈልገን ነው። በተለይ አሁን የኢትዮጵያዊያን ድምጽ ከዳር እስከ ዳር ጎልቶ በአንድነት በሚሰማበት ጊዜ ላይ፣ እነዚህን እንደ አገርና እንደ ማኅበረሰብ የተሠራንበትን እሴት ማስታወስና ማጠናከር ያስፈልጋል። እናም ለሉዓላዊነታችንና ክብራችን ያነሳነውን የ#በቃን እንቅስቃሴ እሴታችንንም ለመጠበቅና ከራሳችን ጋርም ለመታገል እናውለው ለማለት ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here