የሱማሌ ክልል ምክር ቤት የ12 አባላቱን ያለመከሰስ መብት አነሳ

0
697

የሱማሌ ክልል ምክር ቤት ጥር 30 ባካሄደው ስብሰባ የ12 አባላቱን ያለመከሰስ መብት አንስቷል።

ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የምክር ቤቱ አባላት ከዚህ ቀደም በክልሉ ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ የነበሩ ሲሆኑ በክልሉ በነበረው ብሔር ተኮር ግጭት ምክንያት በሕግ የሚፈለጉ እንደሆኑ ታውቋል። በሙስና ወንጀል እንደሚጠረጠሩም ተገልጿል።

የፌደራሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በቅርቡ ሰጥቶት በነበረው መግለጫ ላይ በሱማሌ ክልል የበርካቶች ህይወት መጥፋትን ጨምሮ ከፍተኛ የሰብኣዊ መብት ጥሰት ይፈጸም እንደነበር ገልጿል። በዚህም በቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አብዲ መሀመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) መዝገብ ከተከሰሱ 47 ተጠርጣሪዎች መካከል ከ40 በላዩ በሕግ ጥላ ስር አለመዋላቸው ይታወቃል። ካልተያዙት ተጠርጣዎች ውስጥም የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናትና የቢሮ ኃላፊዎች የነበሩ ሲገኙበት አሁን ላይ በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት እንደሚገኙ መነገሩ አይዘነጋም።

ምክር ቤቱ ያለመከሰስ መብታቸውን ከነፈጋቸው 12 አባላቱ መካከልም የቀድሞዋ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሱአድ መሐመድ እንዲሁም የቀድሞው የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤና የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኢሶሕዴፓ) ሊቀመንበር መሐመድ ረሺድ ይገኙበታል።

በተጨማሪም የቀድሞ የክልሉ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አህመድ አብዲ አንዱ ናቸው። አህመድ በክልሉ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ጊዜያዊ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንደነበሩም ይታወሳል።

የቀድሞ የክልሉ የውሀ ልማት ቢሮ ኃላፊና የሶሕዴፓ ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፈርሃን አብዲ፣ የቀድሞ የክልሉ የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ መጅድ መሃመድ፣ የቀድሞ የክልሉ የእንስሳትና አርብቶ አደር ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አብዲ መሃመድ እንዲሁም የቀድሞ የክልሉ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊና የሶሕዴፓ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ኸበር አብዲም ያለመከሰስ መብታቸው ከተነሳባቸው መካከል እንደሚገኙ መረጃዎች አመልክተዋል። ያለመከሰስ መብታቸው ከተነሳባቸው መካከል በቁጥጥር ስር እየዋሉ የሚገኙ መኖራቸው እየተነገረ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here