የኢትዮጵያ ስኳር ሕመምተኞች ማኅበርን በጥቂቱ

በተለያየ ወቅትና ኹኔታ ማኅበራት የተለያዩ ዓላማዎችን ይዘው ይመሠረታሉ። በሠለጠነው ዓለም በየጊዜው ሰዎች ላይ በሚከሠቱ የጤና እክሎች ዙርያ እርስበርስ ሕሙማን የሚደጋገፉባቸውን ማኅበራት መመሥረት የተለመደ ነው። ይህም ሕሙማን በተናጥል ከሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ባሻገር በዛ ባለ ቁጥር ሰፋ ያለ ተጽዕኖን ለመፍጠር ይረዳቸዋል። ለዛሬ እንዲህ ካሉ ማኅበራት መካከል የሆነውንና በአገራችን ከሚገኙ አንጋፋ ማኅበራት አንዱን የኢትዮጵያ ስኳር ሕሙማን ማኅበርን ልናነሳ ወደናል። ከማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተናኜወርቅ ጎሹ ጋር ባደረግነው አጠር ያለ ቆይታም፣ በማኅበሩ እና ማኅበሩ እያከናወነ ባላቸው ሥራዎች ዙርያ አጠር ያለ ማብራርያ አግኝተናል።

የማኅበሩ አመሠራረት
የኢትዮጵያ ስኳር ሕሙማን ማኅበር የተመሠረተው በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ጥር 14/1976 ነው። ከስኳር ሕመም ጋር ለሚኖሩ ሰዎች መረጃ ማቅረብና እንዲያገኙ ማስቻል፣ ከሕክምና አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮችን መፍታት፣ ሕሙማኑ ስለ በሽታውና ከዛም ጋር በተገናኘ የሚገጥማቸውን ችግር በሚመለከት መወያየት የሚያስችላቸውን መድረክ ማዘጋጀት፣ ሲመሠረት ዓላማ ካደረጋቸው ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በምሥረታውም ላይ የተለያዩ አካላትን በአባልነት አሳትፏል። በዋነኝነት የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር፣ የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች እና ከስኳር በሽታ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ይገኙበታል።
ታድያ በዚህ መሠረት ከተቋቋመበትና ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እንደ ርዕይ ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረው፣ በኢትዮጵያ የስኳር ሕመም ሥርጭትን መከላከል እንዲሁም የትምህርትና ክብካቤ፣ ብሎም የልኅቀት ማዕከል መሆንን ነው። ተመጣጣኝ የስኳር ሕመም መድኃኒቶችንና ቴክኖሎጂንም ተደራሽ ማድረግና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ማስተዋወቅን ደግሞ እንደ ተልዕኮ ይዞ ረዘም ላሉ ዓመታት ሲተገብራቸው ቆይቷል።

ይህን ተከትሎ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከዓይነት አንድ የስኳር ሕመም ጋር ለሚኖሩ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሚሆኑ ሕፃናት የኢንሱሊን፣ በደም ውስጥ የስኳር መጠን መለኪያ መሣርያ ማሽን፣ ለምርመራ የሚያግዙ መሣሪያዎችን ድጋፍ ያደርጋል። ይህም አገልግሎት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ እና በማኅበሩ ቅጥር ግቢ ውስጥ ይሰጣል። እንዲሁም በክልል ደረጃ ከሆስፒታሎች ጋር በመተባበር ሕሙማኑ አገልግሎቶቹን እንዲያገኙ ይደረጋል።

በኹሉም የማኅበሩ ቅርንጫፎች በወር አንድ ጊዜ ለሕክምና ክትትል ለሚመጡ አባላት ቋሚና ተከታታይነት ያለው ትምህርት ይሰጣል። ከዚህ ጋር በተያያዘም የስኳር ሕመም ክብካቤ ጋር በተገናኘ የጤና ሚኒስቴርን በማማከር እና ለሕሙማን ድምጽ በመሆን ይሠራል። ከዛም በተጓዳኝ በዓመታዊ የስኳር ሕመም ቀን የመገናኛ ብዙኀንን (ኅትመት፣ ሥዕል፣ ድምጽ፣ ቪድዮ) በመጠቀም ለማኅበረሰቡ የስኳር ሕመም ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን ያከናውናል።

ማኅበሩ አዲስ አበባ በሚገኘው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በራሱ ባስገነባው የስኳር ማዕከል ምርመራዎችን ያደርጋል። በዛው ማዕከል ውስጥ በተጓዳኝ የዐይን ጤና ክብካቤ ይሰጣል። ይኸውም ዓይነት ኹለት የሚባለው የስኳር ሕመም ለሚያጠቃው የዐይን ክፍል እንክብካቤ የሚደረግበት ነው (ዓይነት ኹለት ዕድሜያቸው ከ30 በታች የሆኑ ሰዎችን ያጠቃል) ።

በሽታው ከስድስት ወር ዕድሜ በላይ ባለ ማንኛውም ሰው ላይ እንደመከሰቱ፣ በሠፊው ከትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበርም ይሠራል። በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አካባቢ ለታማሚ ሕፃናት ሊደረጉ በሚገባቸው ጥንቃቄዎች ዙርያ ከትምህርት ቤቶች እና ከመምህራን ጋር በትብብር የማንቃት ተግባራትን ይፈጽማል።

10 ሺሕ 500 የሚሆኑ ሕፃናት በዚህ ፕሮግራም ሥር የተካተቱ ሲሆን፣ ለእነዚህም የስኳር መመርመሪያ መሣሪያን ጨምሮ አስፈላጊ መድኃኒቶችን ያቀርባል። ይህም በየወሩ በቋሚነት የሚከናወን ነው። ነገር ግን ይህ እንቅስቃሴ እምብዛም ከአዲስ አበባ ውጭ ሲሻገር አይታይም። ለዛም ነው ማኅበሩ አሁን ላይ በአዲስ አበባ ብቻ የተገደበውን ይህን አገለግሎት በክልልሎችም የማዳረስ ዕቅድ የያዘው።

ከስኳር ሕመም ጋር ለሚኖሩ ሰዎች እና ለቤተሰቦቻቸው ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን፣ እንዲሁም ማኅበራዊ ደኅንነታቸውን ማስጠበቅ ሌላው በማኅበሩ የማይዘነጋ ተግባር ነው። ለባለ ድርሻ አካላት፣ ለምሳሌ ለጤና ሚኒስቴር እና ለመሳሰሉት የመንግሥት ተቋማት፣ እንዲሁም ለሕዝብ እና ለግል ተቋማት የቴክኒክ እና ሙያዊ ምክክር ድጋፍ ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት የሚደረጉ ምርምሮችን የማበረታታት እና የመደገፍ ሥራ ይሠራል። ከተልዕኮው ጋር የሚገናኙ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን፣ ሴሚናሮችን፣ አውደ ጥናቶችን፣ ኤግዚቢሽኖችን፣ ትምህርታዊ ስብሰባዎችን እና ሥልጠናዎችን ያዘጋጃል።

በረጅም ዓመት ጉዞው ያጋጠሙ ችግሮች!
ሠላሳ ስምንት ለሚጠጉ ዓመታት የቆየው ማኅበሩ፣ ‹የአባሎቼ ጠበቃ ነኝ› ብሎ ራሱን እንደሚጠራ ተናኜወርቅ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነግረውናል። ነገር ግን ኹኔታዎች ቀላል ሆነው አይደለም። በጉዟቸው በርካታ መሠናክሎችን እንዳለፉ ነው ተናኜወርቅ የሚናገሩት።

አንዱ ችግር የነበረው የመድኃኒት አቅርቦት መቆራረጥ ነው። በተለይም የዓይነት አንድ ስኳር ሕመምተኞች በሕይወት ዘመናቸው በጠቅላላ የ‹ኢንሱሊን› አቅርቦት ሊቋረጥባቸው አይገባም። ነገር ግን የኢንሱሊን አቅርቦት በተለያዩ ጊዜያት በአገር ውስጥ ከገበያ የመጥፋት፣ ብሎም በቋሚነት አለመገኘት ያጋጥማል። በተለይ ኮቪድ 19 ተከስቶ በነበረበት ወቅት ሕሙማኑ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው እንደነበር የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ያነሳሉ።

ሌላኛው እንደ እንቅፋት ያነሱት የአቅም ውሱንነትን ነው። ማኅበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ወደ ስድሳ ኹለት ቅርንጫፎችን በመላ አገሪቱ ከፍቶ፣ ከ32 ሺሕ በላይ አባላትን በሥሩ ይዞ ይገኛል። ሆኖም ለእነዚህ አባላቱ የሚሠጣቸውን ጥቅማ ጥቅሞች በሀብት ውስንነት ምክንያት ለማዳረስ ይቸገራል። ለስኳር ሕመም ተብለው የሚወሰዱ መድኃኒቶች በጠቅላላ የሚገቡት ከውጪ አገራት ነው። ይህም ማኅበሩ ለመድኃኒቶቹ ማስገቢያ የሚከፍለውን ወጪ ከፍ አድርጎታል።

ከማጓጓዣ ወጪ በተጨማሪ ለመድኃኒቱ ማስቀመጫ ማቀዝቀዣዎች ክፍያን ያከናውናል። እነዚህም በዛ ያሉ ክፍያዎች ከማኅበሩ አቅም በላይ እንደሆኑ ነው ሥራ አስኪያጇ ጨምረው የነገሩን። ታድያ እነዚህን ችግሮች ለመጋፈጥ፣ ለመቋቋምና ለማሸነፍም ማኅበሩ የተለያየ የመፍትሔ መንገዶችን እንደወሰደም ነግረውናል።

የወደፊት ዕቅዶች
ማኀበሩ በበሽታው ሥርጭት ልክ ጠንካራና ተገዳዳሪ ሥራን እየሠራ፣ እንዲሁም በሚፈለገው መጠን ተደራሽ እየሆነ ነው ለማለት ያስቸግራል። ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ጨምሮ ዝቅተኛ የሆነ የኢኮኖሚ አቅም ነው። በአንጻሩ ታድያ ማኅበሩን ለማሳደግና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ያደርጋሉ።

በቀዳሚነት ከአባላቱ በየወሩ መዋጮን መሰብሰብ ነው። ይህም ከ5 እስከ 15 ብር የሚደርስ ሲሆን፣ ይህ ግን ወጪዎችን ለመሸፈን ከሚያስፈልገው በእጅጉ ያነሰ እንደሆነ ተናኜወርቅ ያስረዳሉ። ስለዚህም ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚገጥሙትን ችግሮች በውጪ አገራት ከሚገኙ አጋር ድርጅቶች ልገሳ እና ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ በሚገኝ ድጋፍ ለመቅረፍ እየጣረ ይገኛል።

ለወደፊትም ማኅበሩ በዘላቂነት የስኳር ሕመምተኞች ክብካቤ እና ድጋፍ ላይ ከአሁን በላቀና በሠፊው እንደሚሠራ ነው ተናኜወርቅ የሚጠቁሙት። አሁን እየተገለገሉበት ባለው ማለትም ቦሌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ቦታ ላይ ባለ ሰባት ወለል ሕንጻ የመገንባት ዕቅድም ማኅበሩ አለው። ሕንጻውም የራሱ የሆነ የስኳር ሕመምተኞች የሚታከሙበት ክኒሊክ፣ ቤተ መጻሕፍት እንዲሁም የጥናት ማዕከላትን አቋቁሞ በበሽታው ዙርያ የተለያዩ ጥናቶችን ለማካሄድ የሚረዳ ክፍል ይኖረዋል ተብሎ ታቅዷል።

በአገር ዐቀፍ ደረጃ መንግሥት ሕክምናው ላይ ያለውን ተሳትፎ ማረጋገጥ እና ሙሉ በሙሉ ማሳደግ እንደ ዋነኛ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው። ሌላው ማኅበሩ ከሕመሙ ጋር ለሚኖሩ ሰዎች ነጻ የሕክምና እና የመድኃኒት አቅርቦት መገኘቱን የሚያረጋግጥበትን መንገድ በሠፊው እያፈላለገ ይገኛል። ለዚህም በአገር ውስጥ ድጋፍ የሚያገኙበትን መንገድ መፈለግ ቅድሚያ የተሠጠው ነው።

ይህ እውን እንዲሆንና የማኅበሩን ውጤታማነት ከፍ ለማድረግ ማኅበሩ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ እና የገቢ ማሰባሰቢያ ተግባራት ውስጥ በሰፊው መሳተፍን ከዕቅዱ መካከል አድርጎ ጽፎታል። እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ ከማኅበሩ አባላት አልፎ፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ተግባራትን ለመደገፍ ለሚሹ ማንኛውም አካላት በሩ ኹሌም ክፍት እንደሆነ ተናኜወርቅ አክለው አስታውቀዋል።

በዓለም ላይም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የስኳር ሕመም ተጠቂ ናቸው። ከእነዚህም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በአዳጊ አገራት ውስጥ የሚገኙ መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች ይገልጻሉ። ታድያ ይህ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሕሙማን ቁጥር እየጨመረ የመጣውና አሳሳቢነቱ ያየለው የስኳር በሽታ፣ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ያለ ሕመም ነው።

ባሳለፍነው ወር ኅዳር 4/2014 የዓለም ስኳር ቀን ተከብሮ ነበር። ‹የስኳር ሕመም ሕክምናና እንክብካቤ ተደራሽነት አሁን ካልተተገበረ መቼ?› የሚል መሪ ሐሳብም ነበረው። በዚህ ዕለትም በመንግሥት በኩል የጤና ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሠጥቶ እንደሚሠራ፣ ስለ በሽታው ግንዛቤ መስጠትን ጨምሮ የሕክምና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ላይ እንደሚተኩር በጤና ሚኒስቴር በኩል ተገልጿል።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here