መነሻ ገጽአምዶችዓውደ-ሐሳብአውቆ የተኛው ዲፕሎማሲ

አውቆ የተኛው ዲፕሎማሲ

ዲፕሎማሲ ለአንድ አገር ኅልውና ልክ የመከላከያ ኃይልን ያህል አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል፡፡ በኃይል ብቁ ሆኖ መገኘት የመጠበቁን ያህል በሥነ-ልቦናና በመረጃም ኹሌ ዝግጁ ሆኖ መገኘት ከየትኛውም መንግሥት ይጠበቃል፡፡ ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዲፕሎማሲ ረገድ የሚፈለገውን ያህል እንቅስቃሴ ባለማድረጓ አሁን ለገባንበት ችግር እንደአንዱ መንስዔ ይቆጠራል፡፡ አሁን አሁን በዘርፉ እየታዩ ያሉ መሻሻሎች ቢኖሩም፣ ከዚህ በበለጠ መሠራት እንዳለበት ከምዕራባውያኑ ፍላጎት አንፃር እያስተያዩ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ሐሳባቸውን እንዲህ አስፍረውታል፡፡

የሠጥቶ መቀበል የዘመናችን ዲፕሎማሲ፣ ‹‹ከእኛ ጋር ያልሆነ ጠላታችን ነው›› ወይም ደግሞ፣ “ከባልሽ ባሌ ይበልጣል” ከሚሉት አንሥቶ፣ የአገርን ሉዓላዊነት ያከበሩ እና በትክክልም የዘመናዊት ዓለም ነጸብራቅ የሆኑ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎችን እንመለከታለን።
ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ፣ ዓለም አሁን ያላትን ቅርጽ መያዟ ዕውን ሲሆን፣ አሰላለፋቸውን በሚመቻቸው እና አሻግረው ባመለከቱት የተስፋ መዳረሻ ሊወስዳቸው በሚችለው መንገድ በመቀየስ መደበኛ የርዕዮት ዓለማዊ ለውጥ ያደረጉትን አገራትን መቁጠር ይቻላል።
ኢትዮጵያስ የዲፕሎማሲ ታሪኳ ረጅም ዓመታትን ወደ ኋላ የሚመዘዝ አይደለምን? ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በንግድም ሆነ በፖለቲካ ሩቅ ምሥራቅን ያቀኑ፣በመካከለኛው ምሥራቅ የተምነሸነሹ፣ ፋርስን ያደረጁ ብርቱ ቀደምቶች ኢትዮጵያን አስተዳድረው ለተተኪው አስተላልፈው አላለፉምንʔ

እንዲያው ዘመናትን አልፈን ተወረወርን እንጂ፣ በዓለም መንግሥታት (ሊግ ኦፍ ኔሽን) ምሥረታ ላይ ብቸኛ ጠይም የቆዳ ቀለም ባለቤት ኢትዮጵያዊው ንጉስ አጼ ኃይለሥላሴ በግርማ የተሰየሙበተ ሁነኛ ኹነትም ነበር። ይህን የኋላ እና የመጣንበትን ታሪክ መጥቀሳችን፣ አሁን ላለንበት እና ልናነሳው ለወደድነው ሐሳባችን የማዕዘን ድንጋይ በመሆን ያገለግለናል በሚል ታሳቢ ነው።

አንድ ዓመትን ደፍኖ በጊዜ ዑደት እያዘገመ የሚገኘው የሰሜኑ ጦርነት፤ ኢትዮጵያ፣ ጠቅላዩም እንዳሉት፣ ወዳጅ እና ጠላቷን የለየችበት እና ኹነኛ አጋሮቿን የምትመዘግብበት የችግር ወቅት እንደነበር ኹላችንም አንሥተውም። እንዲያው ዓለም፣ በተለይም ደግሞ ምዕራቡ፣ አይናችሁን ላፈር በሚል እና የፌዴራሉ መንግሥት የትኛውም ዓይነት ሐሳብ አይጥመኝም በሚልም፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ከአስተዳዳሪው መንግሥት ለሚሄድለት ሪፖርትም ሆነ መረጃ የዝሆን ጆሮ የያዘበት አስገራሚ ወቅት እንደነበር እና እንደሆነም እንታዘባለን።

በመጀመሪያዎቹ ወራት ወደ መንግሥት ይወረወሩ የነበሩት ውርጅብኞችም ቀላል አልነበሩም። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዴት ሥራውን አይሠራም፣ እንዴትስ ለዘመናት እንደ አገር የገነባነውን ዲሞክራሲ በህወሓት ጥቂት ቡድኖች አስበልቶ ኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ኪሳራ ላይ ይጥላታል የሚሉ ውንጀላዎችም የተሠነዘሩባቸው ጊዜያት ጥቂት አልነበሩም። በእርግጥ በውጭ ጉዳይ እና በተለያዩ የዓለማችን አገራት ተሰባጥረው የሚገኙት የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደሮች ምን እየሠሩ እንደነበርም ጠይቀንበታል።

በሕግ ማስከበሩ ዘመቻ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት፣ ከህወሓት ዘንድ የታየው በተለያዩ አማራጮች ጉዳዮችን ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የማድረስ ሥራ በተሳካ ሁኔታ የተሠራ ነው ቢባል ስህተት አይሆንም ነበር። የህወሓት ደጋፊዎች ከ‹ትዊተር እስከ ፌስ ቡክ› ብሎም በተመረጡ ሥፍራዎች የጎዳና ላይ አሳዛኝ ትርዒቶችን በማካሔድ ‹‹የአገር ቤት አሁናዊ ኹኔታ ይህን ይመስላል፤ የፌዴራል መንግሥትም እንዲህ ዓይነት ግፍ ፈጽሞብናል›› በሚል ኡኡታቸውን አሠምተው ነበር። በአንጻሩ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ኹልጊዜም እንደሚለው ‹‹እውነት ከእኔ ጋር ናት›› ያለ ይመስል፣ አዲስ አበባ ተቀማጭ ከሆኑ አምባሳደሮች ጋር ከመወያየት እና ስለኹኔታው ወቅታዊ መረጃ ከማድረስ ይልቅ፣ ወይም ደግሞ በየዓለማቱ ባሠማራቸው አምባሳደሮች አማካይነት የኢትዮጵያን እውነት ከማስረዳት ይልቅ ዝምታን እና ምንም እንዳልተፈጠረ ነባራዊ ሥራውን የቀጠለበት ወቅትም ነበር።

የሆነው ሆኖ ግን ለዲፕሎማሲ መቼም ቢሆን ረፍዶ አያውቅም እና በከፍተኛ ጩኸት እና ትችት ከሠመመን የነቃው ውጭ ጉዳይ፣ ሠፋፊ ሥራዎችን እና ከፍተኛ የሚሲዮኖች፣ አምባሳደሮች እና ቋሚ መልዕክተኞች ሹም ሽር ወይም መተካካት ያከናወነበት ሥራ አመርቂ ነበር። ይሁን እነጅ የሰጥቶ መቀበል እና በኹለት፣ ብሎም ከዛም በላይ በሆኑ አገራት መካከል በመከባበር እና በመደጋገፍ የሚገነባው የዲፕሎማሲ መርህ ግን ኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ በእጅጉ ተለወጠ። የኹለት አገራት መከባበሩ እና መደማመጡ ሳይሆን፣ ሉዓላዊነት ጥሶ በአገር የውስጥ ጉዳይ ላይ እንደፈለጉ ለመፈትፈት ያሰፈሰፉ፣ ረብጣ ዶላራችንን የምናፈሰው ጠኔያችሁን ለማራገፍ ወይም ጠግባችሁ የእኛን ትዕዛዝ አልቀበልም ልትሉ ብቻ ሳይሆን፣ ከፈጣሪ እኩል እንድታመልኩን ነው ባይ የበለጸጉ አገራት ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ።

በዚህም አልበቃም፤ የዲፕሎማሲው ጉዳይ ርቆ ተቀብሮ የሉዓላዊነት ጉዳይ ወደ መሆን ደረሰ። በእርግጥ የዲፕሎማሲ አንደኛው እና ዋነኛው ጠቀሜታ የአገርን ሉዓላዊነት በሠላማዊ እና በሰለጠነ መንገድ የማስከበር እና የማስጠበቅ ሒደት ቢሆንም፣ የዲፕሎማሲው መንሻፈፍ ግን የሉዓላዊነትን ጉዳይ አደጋ ውጥ የጣለ ነበር።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሆነ ጠቅላላው የመንግሥት የትኛውም ሕዋስ፣ አገርን በዲፕሎማሲም ሆነ በየትኛውም አግባብ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ መንቀሳቀስ በጀመረበት ወቅት ታዲያ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እና ያደጉት አገራት የዝሆን ጆሮ በመስጠት አይናቸውንም ጆሯቸውንም ወደ ህወሓት ቅሬታ ብቻ አዘንብለው የአንድ ወገን ችግርን ለመስማት ከጀሉ። ከፌዴራል መንግሥት የሚላከው እና የሚነገረው የተቀናጀ መረጃ ተቀባይነት ብቻም ሳይሆን፣ እንዲያውም በቃላት ሥንጠቃ መንግሥትን መልሰው ለመሞገት የሚነሱበት ግብዓት ከመሆን የዘለለለ ጠቀሜታ አልነበረውም። አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም ነው እና ተረቱ፣ ከፍየሏ በላይ ለሆነው ለቅሷቸው ዕውነታውን ከራሳቸው አልፈው በዓለም ሚዲያም ተንሻፎ እንዲቀርብ በማድረግ ሠፊ ሥራዎችን በኢትዮጵያ ላይ ሲሠሩ ተስተውለዋል።

አሁንም ቢሆን የዲፕሎማሲው ኹኔታ ከድጡ ወደ ማጡ እንደሆነ ማሳያዎችን መጥቀስ ላያስፈልግ ይችላል። አሁንም አውቆ የተኛውን ዲፕሎማሲ ለማንቃት መጣር ከድካም ባለፈ ጠብ የሚል ነገር እንደማይኖርም አያጠራጥርም። በሠላሙ እና በፍቅር ወቅት የተገባውን ቃል በዚህ ወቅት በማጠፍ ኢትዮጵያን ለማሽመድመድ የተሄደበት መንገድ በእጅጉ የሚገርም ነው። አጎዋን ጨምሮ፣ ሌሎች በሥምምነት ላይ የተመሠረቱ ቃል ኪዳኖችን ቃሌን አላከበርክም፣ በውስጥ ጉዳያችሁ ላይም ገብቼ አላቦካሁም በሚል መሠረዝ በየትኛውም የዲፕሎማሲ ርብርብ ሊታከም እና ሊፈወስ የሚችል አይደለም።

ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በሚል በተለያዩ አገራት፣ በአመዛኙ በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ዜጎችን ከእሥር ቤት እና ከእንግልት በማውጣት ወደ አገር መመለስን ብቸኛ ሥራዬ ብሎ ያያዘ የሚመሰስለው ውጭ ጉዳይም፣ አሁን የገጠመው ችግርም ቀጣይ አሰላለፉን እና የውጭ ግንኙነት መርሁን ቆም ብሎ የሚከልስበት እንደሚሆን አልጠራጠርም። በእርግጥ በውጭ አገራት ያሉ ዜጎች ወደ አገር ውስጥ የሚልኩት የውጭ ምንዛሪ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ንግድ መጠን ባስመዘገበችበት ዓመት እንኳን ልትደርስበት የማትችለው እንደሆነ እንገነዘባለን። ነገር ግን፣ ዲፕሎማሲውን ከዚህ በላይ በማድረግ አገራት ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርጉት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለራሳቸውም ጠቃሚ አማራጭ መሆን እስኪችል ድረስ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን መቀየስ ግዴታ ነው።

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ወይም ቢዝነስ ዲፕሎማሲን በመትለም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን፣ ምርት እና ምርታማነትን በማጎልበት የውጭ ገበያን ለማዳረስ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶች እና እረፍት አልባ ቀናት ከፊታችን ሊኖሩን ይገባል። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ደሀን ማንም አይፈልገውም። በመሆኑም ከኢትዮጵያ ለውጭ አገራት የሚላኩት ምርቶች ከአሰፈላጊነታቸው የተነሳ ዲፕሎማሲውን የጀርባ አጥነት በመሆን ሊያግዙት ይገባል። የምዕራባውያን ዐይን ማረፊያ ለመሆን የቻልነው አንደኛው ምክንያት ምን ነበር ብለን መጠየቃችን አይቀርም መቼም።

አንደኛው እና ዋነኛው ሽብርተኝነትን መዋጋት በሚለው ጉዳይ ነበር። ይህን ጉዳይ ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያን ያልረገጠ እና ዲፕሎማሲውን ለማጠንከር ያልፈለገ አገር ይኖራል ለማለት አይቻልም። አሁንም ይህ ገመድ በጥቂቱም ቢሆን ምዕራባዊያን ከኢትዮጵያ ጋር ላላቸው የመነመነ የዲፕሎማሲ ጅማት እንዳይበጠስ የያዘ ጉዳይ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።

ለዚህም ነው ኢትዮጵያን መያዝ የሕልውናቸው መሠረት መሆን እስኪጀምር ድረስ ኢትዮጵያ በኹሉም ዘርፍ መጎልበቷ ግዴታ ነው የምንለው። በሌላስ በኩል አውሮፓውያን አገራት አውቆ ለተኛው ዲፕሎማሲ የማንቀቂያ ደወል የሚሆናቸው በተቃራኒው የኢትዮጵያ አለመርጋት እና መቸገር ለቀጠናው ችግር እንደሚሆን እና ይህም ደግሞ ከምሥራቅ አፍሪካ ወደ እነዚሁ አገራት በባህር ለሚጎርፈው ስደተኞች ቁጥር መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በማሰብ ለተኛው ዲፕሎማሲያቸው አንድ ዐይን መከፈት ምክንያት ነው።

በመሆኑም ሐሳቡን ስንጠቀልል፣ የአገርን ዲፕሎማሲ ስኬት በሚፈሰው የዕርዳታ መጠን መለካት የኪሳራዎች ኹሉ ቀዳሚ እንደሚሆን ይታሰብበት። እውነት ነው ደሀ አገር ነው ያለን፤ ከድህነት ለመውጣት ደግሞ የበለጸጉ አገራት ዕርጥባን በእጅጉ ይጠቅመናል። ነገር ግን ዛሬ የሚሠፈርልን ስንዴ ነገ በአንድ ኪሎ ስለተጨመረ ኢትዮጵያ ከለጋሽ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ሰላማዊነትን እንዲለካ ማድረግ አያስፈልግም። የሩቅ ምሥራቋን እና የዓለም ከፍተኛ ምጣኔ ሀብት ባለቤቷን ቻይናን በጥንቃቄ በመያዝ ከኃይል ይልቅ ዲፕሎማሲው ይሻለናል በሚል የሚለማመጡት አገራት፣ የቻይና አካሔድ ተመችቷቸው ወይም ጥልቅ ፍቅር ይዟቸው ሳይሆን፣ በቻይና እና በምዕራባዊያን አገራት መካከል ያለው በቢሊዮን ዶላሮች የሚገመተው የንግድ ግንኙነት አንዱ እና ዋነኛው ነው።

ከላይ እንደጠቀስኩት ምዕራባውያን አገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አውቀው አስተኝተውት፣ ከኢትዮጵያ በኩል የሚደረገው የማንቃት ሙከራ ጉንጭ አልፋ ነው የሚሆነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ መኖር የሌሎችም የኅልውና መሠረት እስኪሆን ድረስ በቀዳሚነት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ለማጠንከር በጥብቅ እንዲሠራ ምክረ ሐሳብ ማስቀመጥ እወዳለሁ።


- ይከተሉን -Social Media

ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች