ቡና በ13 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ አሳየ

0
574

በዘንድሮ የበጀት ዓመት ለውጭ ገበያ የቀረበው የኢትዮጵያ የቡና ዋጋ በ13 ዓመታት ውስጥ ትልቅ የተባለ የዋጋ መቀነስ እንደታየበት የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የእርሻ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ሳኒ ረዲ እንደተናገሩት በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ሕገ ወጥ ነጋዴዎች የቡና ዋጋን በአገር ውስጥ እንዲጨምር በማድረግ ወደ ውጭ በሚላከው ዋጋ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲያድርበት ሆኗል። ይህም በሕጋዊ መንገድ ቡናን ወደ ውጭ የሚልኩ ነጋዴዎችንም እያዳከመ እንደሆነ ገልፀዋል።

ከዋጋው መቀዛቀዝ ጋር በተገናኘ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ለአዲስ ማለዳ እንደገለፀው በዓለም ዐቀፍ ገበያ የቡና ዋጋ በተከታታይ ዓመታት እየቀነሰ እንደመጣ ተናግረው በኢትዮጵያ ቡና ላይም የዋጋ መቀነስ እንዲታይ አድርጓል ብሏል። የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ግዛት ወርቁ “በተከታታይ ዓመታት የዋጋ መቀዛቀዙ እየታየ የመጣ ቢሆንም የዘንድሮው የቡና ዋጋ መውረድ ግን ከምንጊዜውም በላይ ነው” በማለት የሁኔታውን አሳሳቢነት ገልጸዋል። ይሁንና በኢትዮጵያ ቡና ላይ የታየውን የዓለም ዐቀፍ ዋጋ መቀዛቀዝ በሚኒስትር ዲኤታው የተጠቀሰውን ምክንያት ግዛት ወርቁ አይቀበሉትም። ሥራ አስኪያጁ የቡና ዋጋ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርበው ለውጭ ገበያ ከሚቀርብበት በተሻለ ዋጋ እንደሆነና፤ የውጭ ምንዛሪ ለአገሪቱ ለማስገኘት በሚል እሳቤ እንጂ የውጭ ገበያው በዋጋ በልጦ እንዳልሆነ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዐሥራ ሦስት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ነው የተባለውና በኢትዮጵያ ቡና የዓለም ዐቀፍ ዋጋ ላይ ለተከሰተው መቀዛቀዝ መፍትሔ ካልተሰጠው በቀጣይ ዓመታት ኢትዮጵያ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ገቢ በእጅጉ እንደምታጣ ሳኒ ረዲ አስታውቀው፥ ለዚህም ደግሞ ሚንስትር መሥሪያ ቤቱ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ትልቅ ርብርብ እያደረገ እንደሆነም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበሩ በበኩሉ በ‘ልዩ ቡና’ ወደ ዓለም ዐቀፍ ገበያ መግባትን እንደመፍትሔ ጠቁሟል። ግዛት ስለ ልዩ ቡና ሲያብራሩ ዱካው የሚታወቅ (‘ትሬስኤብል’) ቡና ከየትኛው ገበሬ እንደተመረተ ከማወቅ ጀምሮ እስከ ዓለም ዐቀፍ ገበያ እስኪደርስ ድረስ ያለው ሒደቱ የሚታወቅ ቡና ማቅረብ ከተቻለ ዓለም ዐቀፍ ዋጋው እንዲያንሰራራ ማድረግ ይቻላል ብለዋል። ግዛት አያይዘውም የዓለም ዐቀፍ የቡና ገበያ ለንደን ላይ ቢሆንም ዋጋ የሚወጣለት ኢትዮጵያ ግን የኒውዮርክን ገበያ እንደምትከትል ገልጸዋል። ነገር ግን ልዩ ቡና በማቅረብ ግን በቀጥታ ከዓለም ዐቀፍ ቡና ቆልተው ከሚያቀርቡ ድርጅቶች ጋር የንግድ ትስስር መፍጠር እንደሚቻል አስታውቀዋል። ይህም በለንደንና በኒውዮርክ ከተሞች ከሚተመነው የዓለም ዐቀፍ የቡና ዋጋ ከ50 በመቶ በላይ ጭማሪ ዋጋ እንደሚኖረው ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here