. በ27 ዓመታት ውስጥ በዓይነቱ የመጀመሪያው ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብትና ማኅበረ ፖለቲካ በምን አቅጣጫ መሔድ እንዳለበት ይመልሳል ተብሎ የሚጠበቅ የ10 ዓመት እቅድን ለማዘጋጀት መንግሥት ጥናት አድረጎ መጨረሱን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለፁ።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት በተሰጠ አቅጣጫ መሰረት የተጀመረው ጥናቱ መጀመሪያ የ15 ዓመት ዕቀድ ለማውጣት ታስቦ የተጀመረ ቢሆንም ወደ 10 ዓመት ዝቅ እንዲል ተደርጓል። ለዚህም እንደምክንያት የተገለፀው የኹለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መገባደድ እንደሆነ ማወቅ ተችሏል።
በፕላንና ልማት ኮሚሽን የኮሚሽኑ የቴክኒክ ጉዳዮች ዋና አማካሪ የሆኑት አባስ መሐመድ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት በሚቀጥሉት ዐሥር ዓመታት ሊያገጥሙ የሚችሉ ዕድሎችና ተግዳሮቶች አንድ ዓመት አካባቢ በፈጀ ጥናት የተለየ ሲሆን ዕቅዱን ለማዘጋጀት ቅድመ ሁኔታዎች ተጠናቀዋል።
በሚቀጥሉት ዐሥር ዓመታት በተግባር ላይ ከሚውሉት የሦስተኛው እና አራተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶችን ለማዘጋጀት እንደ ግበዓት እና መነሻ ይሆናል የተባለው ዕቅዱ፤ አገሪቷን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የዐሥር ዓመት እቅዱን ለማዘጋጀት ጥናት በተደረገበት ወቅት እንደ አንጎላ፣ ጋና እና ቬትናም ያሉ አገራት ልምዶች ከግምት ውስጥ እንደገቡ ታውቋል። በተጨማሪም የግሉ ዘርፍ በአገሪቷ ያለውን ተሳትፎ ለመጨመር እና ይህንን በተግባር ላይ ለማዋል አቅጣጫ ለማስቀመጥ ይረዳል የተባለው ጥናቱ፤ የአገሪቷ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንዴት መሔድና ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር መራመድ እንዳለባቸው በዕቅዱ እንደሚካተት ምንጮቻችን ገልፀዋል።
በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ተጠናቆ በ2012 ለሕዝብ ይፋ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ዕቅዱ በ10 ዓመት ውስጥ ሊተገበሩ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ፕሮግራሞችንና የረጅም ጊዜ የሐሳብ ረቂቆች እንደሚካተቱበት ተገልጿል። በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ከተዘጋጀው የመጀመሪያው አምስት ዓመት ዕቅድ አንስቶ በኢትዮጵያ የተለያዩ የረጅምና የአጭር ጊዜ ዕቅዶች መተግበራቸው ይታወቃል። ለአብነትም ወታደራዊው የደርግ መንግሥት በሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የ10 ዓመት ዕቅድ ለመተግበር እንቅስቃሴ ተጀምሮ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣንን ከተቆጣጠረ በኋላ ደግሞ የዘላቂ ልማት እና ድኽነት ቅነሳ ፕሮግራም እና ዕቅዶች እስከ 2003 ድረስ መተግበራቸው ይታወሳል። ከዚያም፤ ለማሳካት አዳጋችና የተለጠጡ ዕቅዶች የተካተተባቸው የመጀመሪያውና ኹለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች በተግባር ላይ ውለዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የ100 ቀናት ዕቅድ እያንዳንዱ የፌዴራል መንግሥት ተቋም እንዲያዘጋጅ አቅጣጫ በሰጡት መሰረት በተግባር መዋሉ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ተቋማት የዕቅዳቸው ግማሽ እንኳን ለማሳካት መቸገራቸውን ለፓርላማ ማሳወቃቸው አይዘነጋም።
በሌላ በኩል፤ እንደ ፕላንና ልማት ኮሚሽን አማካሪው አባስ ገለፃ ከሆነ በዝግጅት ላይ ያለው የ10 ዓመት ዕቅድ በ27 ዓመታት ውስጥ በዓይነቱ የመጀመሪያው ነው። ከዚህ ቀደም ይወጡ ከነበሩት ዕቅዶችም ግብ በመምታት ደረጃ አዲስ የሚወጣው ዕቅድ የተሻለ እንደሚሆን ይጠበቃል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት አጥላው አለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው የ10 ዓመቱ ዕቅድ መውጣቱን ቢደግፉም አገሪቷ እስከ 20 ዓመታት የሚደርስ የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ ሊኖራት እንደሚገባ ገልፀዋል። አክለውም አሁን የሚዘጋጀው ዕቅድ በአካባቢ ጥበቃ፣ ግብርና፣ ቤቶች ልማትና ሰፈራ አገሪቷ ሊገጥማት የሚችሉትን ነገሮች ማካተት እንደሚገባው ገልፀዋል። በተጨማሪም ዕቅዱ ከላይ ወደ ታች የሚወርድ ብቻ መሆን እንደሌለበት እና ከታች መዋቅር ወደ ላይ መውጣት እንዳለበት ገልጸዋል። አለበለዚያ አፈፃፀሙ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል ብለዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011