የመከላከያ ሠራዊቱ መልሶ ግንባታ ለአገር ፍቅር እና ለሕዝብ ደኅንነት!

0
699

ሰሞኑን ሲከበር የሰነበተው 7ኛው ‘የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ቀን’ ማሳረጊያውን ሐሙስ፣ የካቲት 7 በደማቅ የአከባበር ሥነ ስርዓት አዳማ ላይ ማካሔዱ ይታወሳል። መዝጊያው ዝግጅትም ላይ የሠራዊቱን ብቃት የሚያሳይ ወታደራዊ ትርዒት በማሳየት ለሕዝቡ የመከላከያ ሠራዊቱ ቁመናን በግርድፉ ለማየት ዕድል ሲፈጥርለት ለሠራዊቱ ደግሞ ሕዝቡ በሠራዊቱ ላይ ያለውን እምነት እና የአለኝታነት ስሜት እንዲያዳብር ይረዳል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ይሁንና በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩም መዘንጋት አይገባም።

በመሠረቱ የአንድ አገር መከላከያ ሠራዊት አባል መሆን ከፍተኛ ክብር ያለው ሙያ ነው። ለአገር ዘብ መቆም መልካም ዜጎች ሁሉ የሚመኙት ተግባር ነው። አንድ አባል ቃለ መሐላ ፈፅሞ የመከላከያ ሠራዊት መለዮ ከለበሰ በኋላ ተራ ዜጋ አይደለም። አገሪቷ በዜጎቿ ማየት የምትፈልጋቸውን መልካም ዕሴቶችን ሁሉ በወታደሮቿ ማየት ትሻለች፤ ለሕዝብ ተቆርቋሪነት፣ አገር ወዳድነት፣ ፍትሐዊነት፣ ጀግንነት፣ ታማኝነት አገር እና ሕዝብ ከወታደሮቹ የሚጠብቁት ነገር ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም ቢሆን ከዚህ የተለየ ነገር አይጠበቅበትም።

የየትኛውም አገር መከላከያ ሠራዊት ለአገሩ ከምንም ነገር የሚበልጠውን ሕይወቱን መስዋዕት ለማድረግ የማይሰስት ለመሆኑ በተግባር ማየት ይቻላል። ሙያው ከሚያስቀምጣቸው መሥፈርቶች መካከል ትልቁ እና ዋነኛውም ይኼው ነው። በርግጥ ይህ መስዋዕትነት እንዲሁ በከንቱ እንዳይቀር መከላከያ ሠራዊቱ የተመሠረተበትን መርሕ በትክክልና በኃላፊነት መንፈስ እንዲወጣ ይጠበቅበታል፤ ሕዝባዊ እና ሕገ መንግሥታዊ ወገንተኝነትቱ ጥያቄ ውስጥ ሳይገባ ማለት ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መርሖዎች የአገሪቱን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በአቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚሰጡትን ተግባሮች ማከናወን፣ በማንኛውም ጊዜ ለሕገ መንግሥት ተገዥ መሆንና ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገንተኝነት ነጻ መሆን አንዳለበት በማያሻማ መልኩ አስቀምጧል። የመከላከያ ሠራዊት ዕሴቶች ተብለው የተቀመጡት ከራስ በፊት ለሕዝብና ለአገር ጥቅም፣ ምን ጊዜም የተሟላ ስብዕና፣ ያልተሸራረፈ ዲሞከራሲያዊ አስተሳሰብ እንዲሁም በማንኛውም ግዳጅ ወይም ተግባር የላቀ ውጤት ናቸው።

በርግጥ የኢትዮጵያ በመከላከያ ሠራዊት በመርሑ በመመራትም ሆነ ዕሴቶቹን በማስጠበቁ ረገድ የሚነሱበት ብዙ ጥያቄዎች አሉ። ከሚነሱበት ጥያቄዎች መካከልም በዋናነት የመከላከያ ሠራዊቱ ስብጥር፣ አደረጃጀት፣ የአመራር ብቃትና ውክልና እንዲሁም ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ወገንተኝነት አቋም ማሳየት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። መከላከያ ሠራዊቱ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሥልጣን በትጥቅ ትግል ከተቆጣጠረ በኋላ መልሶ ሲዋቀር በአንድ የትጥቅ ትግል ውስጥ በነበሩ ሰዎች መልሶ ስለተገነባ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት አለበት እየተባለ ሕዝባዊ አመኔታውን ማጣቱ አንዱና ትልቁ ድክመቱ ነው። ኹለተኛው እና ሌላኛው ድክመቱ ደግሞ ውስጥ ለውስጥ የተዘረጋ የሙሰኝነት እና የጥቅመኝነት ሰንሰለት ሰለባ መሆኑ ነው።

በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተመዘገበ ያለው ሁለንተናዊ የፖለቲካ ለውጥ በብዙ መስኮች መሻሻያ እያደረገ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። በዚህ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የመከላከያ ሠራዊት፣ የደኅንነት እና የፖሊስ ተቋማትም ተቋዳሽ እንዲሆን በመደረግ ላይ ለመሆኑ ማሳያዎች ሥራዎች እንዳሉ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

አሠራሩንና ክኅሎቱን ዘመኑ የሚጠይቀውን ከማድረግ ባሻገር፥ ማንኛውም ሠራዊት በመሠረቱ ብቃትና ዕውቀት እንዲሁም የአገር ፍቅር ባላቸው አባላትና አመራሮች መመራት ይገባዋል በማለት አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። በዚህም ረገድ የአመራሮች ሹመት፣ ስንብትና አዳዲስ አመራሮችን ወደፊት ማምጣት ጅማሮዎች እንዳሉ የተረዳችው ጋዜጣችን፥ ጅምሮቹን እያበረታታች፣ ለዚህ የመልሶ ማዋቀር ሒደት ከላይ የተጠቀሱት የአገር ፍቅር፣ ሙያዊ ብቃት እና ክኅሎት፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት እንዲሁም ከሙስናና ጥቅመኝነት ትሥሥሮሽ ነጻ መሆን መሠረታዊ መርሖዎች መሆን እንዳለበት ለማሳሰብ ትወዳለች።

በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎችን ተከትሎ ተቋማዊ ለውጥ በተግባር እየታየና ውጤት እያስመዘገበ ለመሆኑ መከላከያ ሠራዊቱ በተሠማራበት የግዳጅ ቦታዎች እያሳየ የመጣው ሕዝባዊነት ጥሩ ምስክርነት ይሰጡታል። በፊት ያደርገው እንደነበረው ተቃውሞ ስለተነሳ ብቻ የኃይል አማራጭን ብቸኛ መሣሪያ በማድረግ ሰብኣዊ መብቶችን ይጥስ እንደነበረው ዓይነት ሠራዊት እንዳልሆነ ፍንጭ እያሳየ መጥቷል። ይህ ማለት ግን መከላከያ ሠራዊቱ ሙሉ በሙሉ የቆመለትን ተልዕኮ እየተወጣ ነው ማለት እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ በአፅንዖት ትገልጻለች፤ ነገር ግን ጅምሮቹም የሚበረታቱ መሆናቸው አይካድም።

በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲኖር የሚፈለገው ሠራዊት ታማኝነቱ ለፓርቲ ሳይሆን ለአገር፣ ለሕዝብና ለባንዲራ መሆኑ በሚገባ የተገነዘበና በተግባር የሚያታይ መሆን አለበት። ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ድንበር በንቃት የሚጠብቅ እንዲሁም ጥቃት በሚቃጣበት ጊዜ በበቂ ምላሽ የሚሰጥ መሆን አለበት። የአገር ፍቅር ስሜት ያለው፣ ሕዝብ የሚወደውና የሚያከብረው፣ የሚያምነው ሠራዊት መሆንም ይገባዋል። ይህንን ለማድረግ መንግሥት የጀመረውን የተቋሙን ማሻሻያዎች የበለጠ አጠናክሮ ሊቀጥልበት ይገባል በማለት አዲስ ማለዳ መልዕክቷን ታስተላልፋለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here