በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ 11 አዳዲስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተያዘላቸው በጀት የ311 በመቶ ተጨማሪ ወጪ ማስመዝገባቸው ተገለፀ። የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት እንዳስታወቀው ተቋማቱ በሚገነቡበት ወቅት ከዲዛይን መጣጣምና ቁጥጥር ጋር በተያያዘ ለአማካሪ ድርጅቶች እንዲከፈል ከተያዘው የጀት 28 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ቢሆንም ፤ ከአማካሪ ድርጅቶች ጋር ወደ ውል ሲገባ ግን በ117 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር መዋዋሉ እና ይህም የ89 ሚሊዮን ብር ልዩነት ማሳየቱን የኦዲት ግኝቱ አሳይቷል። ይህም በመቶኛ ሲሰላ 311 በመቶ እንደሚሆን ታውቋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ስለ አማካሪዎች ክፍያ ምላሽ ሲሰጡ 28 ሚሊዮን ብር የተጠቀሰው በ2008 ለተከናወነው የአንድ ዓመት ግንባታ ብቻ እንደሆነና 117 ሚሊዮኑ ደግሞ በአጠቃላይ ግንባታዎቹ በሚቆዩበት ዓመታት ታስቦ የተገባ ውል ነው ብለዋል።
በኦዲት ግኝቱ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆኑት ደምቢዶሎ፣ ወራቤ፣ ራያ፣ መቅደላ፣ አምቦና ቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎች ከግንባታቸው ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ዜጎች ካሳ እንዲከፈል 100 ሚሊዮን ብር በጀት ቢያዝም ተከፍሎ ተገኘው ግን 215 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን የኦዲት ግኝቱ ያሳያል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የመቅደላ አምባ ዩኒቨርስቲ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የካሳ ክፍያ ሰነድ ሳይኖር ክፍያ መፈፀሙ ተብራርቷል። በዚህም ምክንያት ተነሽዎች ተገቢውን ካሳ ካለማግኘታቸው የተነሳ ከግንባታዎች አካባቢ ባለመነሳታቸው ለግንባታዎች መንጓተት አይነተኛ ተጠቃሽ መሆኑ ተጠቁሟል። ከዚህም ጋር ተያይዞ አንዳንድ የትምህርት ግብዓቶችን ማሟላት ባለመቻሉ ተማሪዎች ወደ አጎራባች ዩኒቨርሲቲዎች እየሄሔዱ ቤተ ሙከራ እንዲጠቀሙ የሚደረግበት አሠራር እንዳለ ለማወቅ ተችሏል። ለግንባታዎች መጓተት እና የትምህርት ግብዓት አለመሟላት ጋር በተያያዘ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የ11 ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ፅሕፈት ቤት ኀላፊ ሰለሞን ደስታ ምላሽ ሲሰጡ ግንባታዎቹን መጨረሻ የጊዜ ገደብ አምስት ዓመት በሚል ቢያዝም በየጊዜው በሚያጋጥም የበጀት እጥረት በታቀደው መሰረት ማስኬድ አለመቻሉን አንስተዋል። የመንግሥት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የትምህርት ግብዓቱን እንደማያቀርብም ተናግረዋል።
በ11 ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የታየውን ከግንባታ ጋር በተያያዘ የክዋኔ ሪፖርት ላይ ተመርኩዘው ዋና ኦዲተሩ ገመቹ ዱቢሶ እንደተናገሩት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ወደ ግንባታ ከመግባቱ በፊት በዕቅዱ ውስጥ ሊያጋጥሙ ይችላሉ የሚላቸውን እንቅፋቶች ማካተት ላይ ክፍተት እንደነበረበትና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተናብቦ የመሥራት ችግርም እንደነበረበት ተናግረዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011