በአማራ ክልል በደባርቅ ከተጠለሉት በስተቀር በጦርነቱ ሳቢያ ተፈናቅለው የነበሩ ኹሉም ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸው ተገለጸ

0
672

የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን በጦርነቱ ምክንያት በክልሉ ውስጥ ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ተጠልለው የነበሩ ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል ሲል አሳውቋል።

ጦርነቱ ወደ ደቡብ ወሎና ሰሜን ሸዋ ተስፋፍቶ በነበረበት ወቅት የተፈናቃዮች ቁጥር ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ደርሶ እንደነበርና ከእነዚህ መካከል ኹለት በመቶ ማለትም ከ45 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ተጠልለው ይገኙ እንደነበር ተነግሯል።
ይሁን እንጂ፣ አሁንም በደባርቅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ከ5 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ተጠልለው እንደሚገኙ ነው የተገለጸው።

በክልሉ ከቀያቸው ተፈናቅለው ከነበሩት ዜጎች መካከል በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ተጠልለው የነበሩትን ጨምሮ ከ500 ሺህሕ በላይ ሰዎች መንግሥት ባዘጋጀው ትራንስፖርት ወደ ቀያቸው መመለሳቸው ተሰምቷል።

በመሆኑም፣ በክልሉ በጦርነቱ ሳቢያ 9.1 ሚሊዮን ሕዝብ ለከፋ የምግብና መድኃኒት ችግር ተዳርጎ እንደነበር እና አሁንም በተለቀቁ አካባቢዎች ማኅበረሰቡ ምርት አምርቶ ራሱን እስከሚችል ድረስ በአጠቃላይ 11.4 ሚሊዮን ሕዝብ የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ነው የተመላከተው።

ለዚህም ለአንድ ወር ብቻ 1.2 ሚሊዮን ኩንታል እህል ያስፈልጋል ተብሏል።

የመልሶ ማቋቋም ሥራ ለማከናወን፣ በህወሓት ኃይሎች ተይዘው በነበሩ አካባቢዎች የደረሰው የጉዳት መጠን እየተጠና መሆኑም እንዲሁም ተመላክቷል።

በክልሉ በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) እና ቀይ መስቀል በተለያዩ አካባቢዎች ተሰማርተው ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውም ተጠቅሷል።
ሆኖም በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች አሁንም የከባድ መሣሪያ ትንኮሳዎች መኖራቸውን ተከትሎ እየተፈናቀሉ ያሉ ዜጎች መኖራቸው ይነገራል።

ይሁን እንጂ፣ የተፈናቀሉ ዜጎች ከየት አካባቢ የተፈናቀሉ እንደሆኑ የተጠየቀው ኮሚሽኑ፣ ጦርነት እስካልቆመ ድረስ መፈናቀልና የዜጎች ስቃይ አይቆምም በማለት አካባቢዎቹን ከመጥቀስ መቆጠቡ ነው የተነገረው።


ቅጽ 4 ቁጥር 167 ጥር 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here