የሰንደቅ ትንቅንቅ

0
677

ሠሞኑን የበዓል ወቅት እንደመሆኑ አነጋጋሪ ሆኖ የቆየውም ከአውድ ዓመቱ ጋር ግንኙነት ያለው የሠንደቅ ዓላማ ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ከመነጋገሪያነት አልፎ መጎዳጃ መሆን ከጀመረ ጥቂት የማይባሉ ዓመታት አልፈዋል። ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ መውጣቱን ተከትሎ ለዘመናት የቆየውና በየስርዓቱ መለያ ሲጨመርበት የነበረው የሠንደቅ ዓላማው መደብ ላይ ኮከብ መካተቱን የማያውቅ ኢትዮጵያዊ የሚኖር አይመስልም። ይህ ጭማሪ ግን ከመነሻው ጀምሮ ተቃውሞ ሲገጥመው የነበረ ነው። አፋሮች ‹እንኳን እኛ ግመሎቻችን ያውቁታል› ካሉለትና ከጥንቱ ሠንደቅ ጋር እያነፃፀሩ፣ መንግሥት የሚጠቀምበትን የሚቃወሙት በርካቶች ናቸው።

‹ባለኮከቡን ሠንደቅ ዓላማ ይህን ያህል ዜጎች ይመርጡታል፣ እነእገሌም ይወዱታል› ብሎ መናገር ባይቻልም፤ በተለያዩ አገራዊ አጋጣሚዎች ማን ምን ዓይነቱን ይዞ እንደሚወጣ በማየት ግን መገመት ይቻላል። መንግሥታዊ ጥሪን ተከትሎም ሆነ በክብረ በዓላት ወቅት በፍተሻ የሚገባባቸው ላይ፣ “አምባሻው” እየተባለ የሚገለፀው ኮከብ ምልክት ያለበት ሰንደቅ ዓላማ የሚታይ ቢሆንም፣ በነፃ ታድሎ እንኳ በኩራት የሚያውለበልበው ምን ያህሉ እንደሆነ ለማወቅ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የታዩ ምስሎችን መለስ ብሎ ማየት ማስረጃ ይሆናል የሚሉ አሉ።

በአንፃሩ፣ “ልሙጥ” ወይም “ንጹሁ” ተብሎ የሚታወቀውንና ሦስቱ ቀለማት ብቻ ያሉበትና አያት ቅድመ አያቶቻችን እኩል ሠንደቃችን ብለው የሞቱለት ነው በማለት ያነጻጽራሉ። እነዚህም እንደሚሉት፣ ሕዝቡ በራሱ ተነሳሽነት በገንዘቡ እየከፈለ የሚገዛውና በነፃ የማያገኘው እንደመሆኑ በበርካቶች በፍቅር መውለብለብና መለበሱን፣ ብዙ ነገር ሲደረግ መታየቱን በማውሳት ያለውን የተቀባይነት አድማስ ለማመላከት ይጥራሉ።

ያም ሆነ ይህ፣ ከፊሉ በፍቅር ዓላማዬን የሚወክለው ሠንደቄ ይህ ነው ብሎ የሚወደውን ሲያንጸባርቅ፣ የተወሰነው ደግሞ በጥላቻም ይሁን ለመለየት የእኔ የሚለውን ያገዝፋል። እንደአገር አንድ የሚያደርግ ጉዳይ መሆን የነበረበት ቢሆንም፣ ለመለያያና ለመተናነቂያ እየሆነ የመንግሥት እርምጃ ጉዳዩን የበለጠ እያወሳሰበው ይገኛል። በአንጻሩ አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀ ቡድን መገለጫዎች ውጭ የየትኛውንም አገር ሠንደቅም ሆነ የተፈለገውን ዓርማ መያዝ እየተቻለ፣ ከፊል ሕዝብ የሚወደውን ሠንደቅ ቢያንስ እንዴት የሁሉም ከተማ ናት በምትባለው መዲና መያዝ ይከለከላል ብለው የሚሞግቱም አሉ።

ኮከቡ የሚወክለው ማኅበረሰብ አለ ቢባልም፣ ይፋ ከመሆኑ በፊት እነዚሁ አካላት ጠይቀው ሳይሆን ባለአምስት ኮከብ እንዲገባ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ታዘው እንደነበር በኮከቦች ዓይነት ብቻ ተወዳድረው የተሸነፉ የስዕል አስተማሪ መናገራቸው ይታወሳል። ይህን ሁኔታ በርካቶች ባያውቁም ኮከብ ይሁን መባሉን በማስመልከት ብዙዎች ግምታቸውንም ሆነ እምነታቸውን ያስቀምጣሉ።

አንዳንዶች ሰብዓ ሰገልን የመራቸውን ኮከብ እንዲወክል የተደረገ ነው ሲሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ ከእስልምና ምልክት ጨረቃና ኮከብ ላይ የተወሰደ ነው ይላሉ። ሆኖም የሐሳቡ ጠንሳሽ ምን አስበው እንደመረጡት እርግጠኛ ሆኖ የሚናገር የለም። አንዳንዶች በአሜሪካ እገዛ ለሥልጣን ስለበቁ፣ የእሷ ተላላኪ እንደሆኑት በርካታ አገራት ተገደው ነው ይላሉ። የእሷን ባንዲራ መገለጫ ምስለኔዎቿ መንግሥታት በየሠንደቆቻቸው ላይ እንዲያካትቱ ታዘው ነው አሁንም ያው ቀጥሎ ያለው የሚሉ ቢኖሩም፣ ሌሎች ደግሞ ከሠይጣናዊ አምልኮ ጋር ያገናኙታል።

ያም ተባለ ይህ፣ የሠንደቅ ዓላማ ጉዳይ ሠሞኑንም እንደ አዲስ አገርሽቶ ፖሊስ መግለጫውን እንዲያሻሽል እስከማድረስ አምርቷል። ሆኖም ነጠቃው ግን እስከ መሸጫ ሱቆች ውስጥ በመዝለቁ ነገሩን ይበልጥ አክርሮታል ሲሉ ማርገብ የነበረበትን መንግሥት እንደቆስቋሽ አድርገው የሚከሱት በርካቶች ናቸው። መውቀስ ብቻ ሳይሆን በየመሃል የሚለጠፉ ጭማሪዎችን እንደምሳሌ በማንሳት ለበርካት ቀልዶች መንስዔ አድርገዉታል።

ኢትዮጵያዊ መልኩን መቀየር እንደማይቻለው ሁሉ ለ30 ዓመታት ያህል በግድ ሠንደቁንም ለመቀየር የተሄደበት መንገድ እንዳላዋጣ ከመማር ይልቅ፣ ደጋግሞ እየሞከሩ ይበልጥ ከሕዝብ መተናነቁ፣ “ያልነቁ አለቁ” ከማስባሉ በፊት ይታሰብበት።


ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here