የእለት ዜና

ሕገወጥ ምንዛሬን ሕጋዊ ለማድረግ አይ ኤም ኤፍ እና ብሔራዊ ባንክ ጥናት ሊያደርጉ ነው

በሕገ ወጥ መንገድ በውጭ ምንዛሬ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ መንዛሪዎችን ሕጋዊ በሆነ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ፣ ከፊታችን ሰኞ የካቲት 16/2012 ጀምሮ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ እና ብሔራዊ ባንክ ጥናት ሊያደርጉ መሆኑ ተገለፀ።

ብሔራዊ ባንኩ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ስርዓትን ለመተግበር እየሠራ ሲሆን፣ በጥቁር ገበያ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ መንዛሪዎችን ሕጋዊ እንዲሆኑ በማድረግ ጥቁር ገበያውን ለመቆጣጠር እየሠራ መሆኑ ተገልጿል።

ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ከአይ ኤም ኤፍ፣ ከባንኩ እና ከሌሎች አገራት የተውጣጡ የፋይናንስ ቴክኒክ ባለሙያዎች ከየካቲት 16/2012 ጀምሮ ጥናት በማድረግ ፍኖተ ካርታ እንደሚያዘጋጁ ታውቋል።

ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሬ ገበያን ብሔራዊ ባንክ ሲቆጣጠር አይሰተዋልም የሚሉ ሐሳቦች በተደጋጋሚ የሚነሱ ሲሆን፣ ጥቁር ገበያው መደበኛውን የገንዘብ ዝውውር ሲጎዳው መቆየቱ በተደጋጋሚ ይገለፃል።

ብሔራዊ ባንክ በሕገ ወጥ መንዛሪዎች ላይ እርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት የለበትም ያሉት በብሔራዊ ባንክ የኢኮኖሚ ትንተና እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ሀብታሙ ወርቅነህ፣ እስከ አሁን በጥቁር ገበያው ላይ ተሰማርተው በሚያዙ አካላት ላይ እርምጃ ሲወሰድ ግን ባንኩ ሳይሳተፍ ቀርቶ አያውቅም ብለዋል።

አክለውም በጥቁሩ ገበያ ላይ ቁጥጥር ሲባዛ ገበያው በይበልጥ እየሰፋ እና ውስብስብ እየሆነ የሚሄድ በመሆኑ፣ ብሔራዊ ባንክ ጥቁር ገበያውን ለመቆጣጠር ፖሊሲዎችን በማሻሻል ሕገወጥ መንዛሪዎችን ሕጋዊ በማድረግ ድርጊቱን ለመቀነስ ጥናቱን እንደሚያከናውን ተናግረዋል።

በውጭ ምንዛሬ ዝውውር ከባንኮች በተጨማሪ የገንዘብ ወኪሎችም ጭምር ደንብ ተዘጋጅቶላቸው እራሳቸውን ችለው እንዲሳተፉ እንደሚደረግ ገልፀዋል። የሚዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱ ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ እንዲሁም በምን ዓይነት መልኩ እንደሚተገበር ለማመላከት እንደሚረዳም ተገልጿል።

ኢኮኖሚውን ከልማታዊ መንግሥት ወደ ግል ባለሀብቶች አልሚነት ለመቀየር ታስቦ የተዘጋጀው የአገር በቀል ኢኮኖሚ ለውጥ ትግበራ እንዲጠናቀቅ የሦስት ዓመታት ዕቅድ የተያዘለት ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱ ገበያ መር በሆነ መንገድ እንዲከናወን የማድረጉ ሥራም በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ከፍኖተ ካርታው ዝግጅት በኋላ የአይ ኤም ኤፍ የቴክኒክ ቡድን በየጊዜው በመምጣት በአተገባበሩ ላይ ክትትል እንደሚያደርግ ለማወቅ ተችሏል።

ቡድኑ በትግበራው ላይ ከተመረጡ የግል ባንኮች ጋር ይወያያል የተባለ ሲሆን፣ አሁን ብሔራዊ ባንኩ የሚመራባቸው እና በርካታ ቅሬታዎች የሚነሱባቸው እንዲሁም ክልከላ የሚያስቀምጡ የውጭ ምንዛሬ መመሪያዎችን በመመርመር ለውጥ አንደሚደረግባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያ ዲያስፖራው ማኅበረሰብ በኢንቬስትመንት ላይ እንዳይሳተፍ እንቅፋት የሆኑ አሰራሮች በእነዚህ ሦስት ዓመታት ይወገዳሉ ያሉት የብሔራዊ ባንክ ቦርድ አባላት እና ገዢው፣ ከአይ ኤም ኤፍ ጋር በተስማሙት መሰረት ለአልሚዎች የገንዘብ አቅርቦት የሚጨምርበት መንገድ እንደሚመቻች ገልጸዋል፡፡

በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በርካታ ጥናቶችን በማድረግ የሚታወቁት ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) በብሔራዊ ባንክ ያሉት ባለሙያዎች ከአይ ኤም ኤፍ እና ከዓለም ባንክ የመጡ መሆናቸውን በማንሳት፣ የገንዘብ ስርዓቱን የውጭ ተቋማት እንዲዘውሩት መደረጉ አግባብ አይደለም ሲሉ አሳስበዋል፡፡

እነዚህ ባለሙያዎችም የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ የሚገነዘቡ አይደሉም የሚሉት ዓለማየሁ፣ በብሔራዊ ባንክ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ችግሮችን ለመፍታት ብቁ አይደሉም ሲሉም ወቀሳ ሰንዝረዋል። ይህም ድርጊት የአገሪቱን የፋይናንስ ሉዓላዊነት የሚጋፋ በመሆኑ በትኩረት ሊታይ እንደሚገባው ጠቁመዋል።

አይ ኤም ኤፍ እና ዓለም ባንክ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን ለመደገፍ በሦስት ዓመታት ተከፋፍሎ የሚተገበር እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው የሚታወስ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com