የአገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ልምድ ሊዳብር ይገባል

0
1176

ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው ምርት ይልቅ ከውጭ ገበያ የምትሸምተው የላቀ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ይህ በዋናነት የሆነው የአገር ውስጥ ምርት አቅርቦት ከተጠቃሚው ፍላጎት ባለመጣጣሙ ይሁን እንጂ፣ ዜጎች የአገራቸውን ምርት የመጠቀም ዝቅተኛ ልምድ ያላቸው መሆኑም ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነም ይነገራል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ማኅበረሰቡ ለአገሩ ምርት ያለው ዝቅተኛ ግምት አገሪቱን የውጭ ሸቀጥ ማራገፊያ ከማድረጉም በላይ፣ በኢኮኖሚ በኩልም በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ጥገኛ እንዳደረጋት ይነገራል።

በአገሪቱ ከሚመረቱ ምርቶች ውስጥ ጥራታቸው የዓለም ገበያ መስፈርትን ያሟላና ዋጋቸውም ተመጣጣኝ የሆነ ቢኖሩም፣ ማኅበረሰቡ የአገሩን ምርት መጠቀም ላይ ያለው አመለካከት ዝቅ ያለ በመሆኑ፣ በብዛት ለምርቶቹ ቅድሚያ ሲሰጥ አይስተዋልም።

በዚህም ከአገር ውስጥ ምርቶች ያነሰ ጥራትና የበለጠ ዋጋ ያላቸው ምርቶች ከውጭ አገር የተገኙ ስለሆኑ ብቻ እንደ ልብ ሲሸጡ ይታያል። ይልቁንም በተቃራኒው የኢትዮጵያ ምርቶች ሌላ አገር ገበያ ውስጥ አዲስ የገበያ ሥያሜ ተሰጥቷቸው በውድ ዋጋ እንደሚሸጡም ጥቆማዎች አሉ።

ይህ ዜጎች የአገርን ምርት ያለመጠቀም ልማዳቸው፣ የአገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዳያድጉ፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል እንዳይኖር እና የሥራ ዕድል እንዳይስፋፋ በማድረግ በአጠቃላይ አገሪቱን በብዙ መልኩ ጎድቷታል የሚሉ በርካቶች ናቸው።

የምሥራቅ እስያ አገራት የሆኑት እንደነ ቻይና፣ ጃፓን፣ ታይላንድ እና የመሳሰሉት ከምዕራባውያን የሚደርስባቸውን ጫና ለመመከትና ሉዓላዊነታቸውን ለማስጠበቅ ትልቁ መፍትሔ ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግ መሆኑን በመረዳት፣ የአገር ውስጥ ምርትን መጠቀም መጀመራቸው ዛሬ ለደረሱበት የተሻለ አቅም ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳበረከተላቸው ይነገራል።

‹‹Asian Tigers›› በመባል የሚታወቁትና በዚሁ በምሥራቅ እስያ ክፍለ ዓለም የሚገኙት ሲንጋፖር፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋን እና ሆንግ ኮንግም የፈጣን ዕድገታቸው ዋነኛ ምስጢር የአገራቸውን ምርት፣ ቴክኖሎጂና ዕውቀት፣ እንዲሁም ሌሎች ከአገራቸው ጋር ተያያዥ የሆኑ ውጤቶችን ለማሳደግና ለመጠቀም ያሳዩት ቁርጠኝነት ነው ተብሎ ይታመናል።

እንዲሁም፣ ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አውሮፓውያንን ከገቡበት የኢኮኖሚ ድብርት ያወጣቸው ለአገር በቀል ዕውቀትና ምርት ትልቅ ትኩረት ሠጥተው መሥራታቸው ነው የሚሉ አሉ። ጦርነቱ ያደረሰባቸው ከፍተኛ ውድመት ከጦርነቱ ማግሥት በኢኮኖሚ ቀዳሚ እንዲሆኑ ያስቻላቸውን መንገድ እንዲከተሉ አስገድዷቸዋል።

ይህም የሚያስፈልጉ ነገሮችን ኹሉ በዕርዳታና በግዥ ከሌሎች አገሮች ከማስገባት ይልቅ፣ አቅማቸውን አሟጠው በራሳቸው የሰው ኃይል እና በራሳቸው ምድር ማምረትና መጠቀም ነበር። ምርቶቻቸውን ወደ ሌሎች አገራት መላክና በኢኮኖሚያቸው መፈንጠር የቻሉትም ከዚያ ቀጥሎ እንደሆነ ነው የሚነገርላቸው።

በአንጻሩ፣ በርካታ የአፍሪካ አገራት ኢኮኖሚያቸው እስካሁን በአደጉት አገራት ተጽዕኞ ሥር የሆነውና የፖለቲካ ጫናውም የበረታባቸው በኢኮኖሚ ረገድ ነጻ ስላልሆኑ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።

እነዚህ የአፍሪካ አገሮች በቀላሉ በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃና የሰው ኃይል ማምረት የሚችሉትን ምርት ሳይቀር ከውጭ ሲያስገቡ ይታያል። ይህም በውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ሳቢያ ከሚፈጥርባቸው የገበያ አለመረጋጋት በተጨማሪ፣ አገራዊ የዕውቀትና ቴክኖሎጅ ሽግግር እንዳይኖራቸው፣ ብሎም በዓለም አቀፉ ገበያ ውስጥ ድርሻ እንዲያጡ ያደርጋቸዋል።

አገራቱ በዚህ ከቀጠሉና የኢኮኖሚ ነጻነትን ማረጋገጥ ካልቻሉ፣ ከአደጉት አገራት የፖለቲካ ጫና ማምለጥ እንደማይችሉም ይታመናል።

ለኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ ምርትን መጠቀም የቅንጦት ወይም የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን፣አማራጭ የሌለው አስገዳጅ ኹኔታ መሆኑን የሚጠቁሙ አሉ። አገሪቱን ግልጽ ባልሆኑና ባልተጋገጡ ውንጀላዎች ብድር እና ዕርዳታ እንዳታገኝ፣ ኢኮኖሚያዊ ድቀት ውስጥ እንድትገባ የሚያደርጉና የኢኮኖሚ አሻጥር በመሥራት ላይ ያሉ ኃይሎች በመኖራቸው፣ የራስን ፍላጎት በራስ ምርት አቅርቦት መሙላት ይገባል ነው የሚባለው።

ይህ ድርጊት በአንድ በኩል አገሪቱ የሚደርስባትን ኢኮኖሚያዊ ጫና የሚያረግብ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ አምራች ዜጋና ኢንዱስትሪዎችን በመፍጠር ወደ ተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታመራ ይረዳታል።

ከሠሞኑ ኢትዮጵያ በይፋ ከአጎዋ ገበያ (African Growth and Opportunity Act) በመታገዷ በኢኮኖሚው ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመከላከል፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመቀነስ የአገር ውስጥ ምርትን በስፋት መጠቀም ተገቢ አካሄድ መሆኑ ይነሳል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍም ይሁን በአገር ውስጥ ገበያ በብዛት የምትታወቀው በጥሬ ዕቃዎች (ጥራጥሬና ቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቆዳና ሌጦ) ይሁን እንጂ፣ የተለያዩ የፋብሪካ ምርቶችም ለውጭ ገበያ እንደምታቀርብ ይታወቃል። ከምርቶቹም ውስጥ ልብስ፣ ጫማና ሌሎች የቆዳ ውጤቶች ዋነኞቹ ናቸው።

ይሁን እንጂ የቆዳ ምርቶችን ከውጭ ገበያ ለማስገባት ኢትዮጵያ በዓመት በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እንደምታወጣ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ሆኖም ግን፣ በዘርፉ በቂ የሰው ኃይልና ጥሬ ዕቃ በመኖሩ የሚወጣውን ወጪ ለማስቀረት ቢሠራ አዋጭ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ችግሩ ግን እስካሁን አገር ውስጥ የሚመረቱ የቆዳ ውጤቶች ላይ ያለው የግብይት ሰንሠለት ውስብስብና የተበላሸ ከመሆኑ ባለፈ፣ ዜጋው የአገሩን ምርት የመጠቀም ፍላጎቱ አነስተኛ መሆኑ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም የወረደ እንዲሆን አድርጎታል።

ተገቢ የቁጥጥር ሥርዓት ባለመኖሩም፣ በሕጋዊ መንገድ ከሚገባው የቆዳ ምርት ይልቅ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደአገር ውስጥ ገብቶ የሚራገፈው ምርት በዕጥፍ የሚበልጥ በመሆኑ፣ የአገር ውስጥ አምራቾች ከገበያ እንዲወጡ የሚያደርግ እና ኢኮኖሚውንም የሚያመሰቃቅል ተግባር እንደሆነ ይነገራል።

ይህን ለመቀልበስ በአምራቾች በኩል ተደጋጋሚ አቤቱታ ሲቀርብ የኖረ ቢሆንም፣ መንግሥት ተገቢ ትኩረት ሳይሰጠው በመቆየቱ ችግሩ ሳይፈታ እንደቆየ ነው የሚገለጸው። አሁን ላይ አገሪቱ ባላት ዝቅተኛና የውጭ ጥገኛ ኢኮኖሚ ምክንያት እየጨመረ በመጣው ፖለቲካዊ ጫና ግፊትም ይሁን በሌላ ምክንያት፣ አልፎ አልፎ የአገር ውስጥ የማምረት አቅማችንንና የመጠቀም ባህላችንን ማሳደግ አለብን ሲባል ይስተዋላል።

በቅርቡም በዘርፉ (በቆዳ ምርት) ላይ የተወሰነ አስተዋጾዖ ያደርጋል የተባለ አገራዊ ፕሮጀክት ይፋ ተደርጎ ነበር።

ይህ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አምራቾች የተያዘውን የቆዳ ምርት ዘርፍ ለመታደግና ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማቃለል ይረዳል የተባለ የተማሪዎች ጫማ፣ ቦርሳ እና ቀበቶ የማምረት ፕሮጀክት ነው።

ፕሮጀክቱ በዓመት 70 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ያድናል የተባለ ሲሆን፣ 15 ሺሕ በዘርፉ የሚሠማሩ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን ይፈጥራል የሚል ዕምነት ተጥሎበታል። ፕሮጀክቱ የሚፈጥረው ከፍ ያለ የሥራ ዕድል ቁጥር እንዳለ ሆኖ፣ ስኬታማ ከሆነ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ ምንዛሪ ማመንጨት እንደሚቻልም ይነገራል።

የቆዳና ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮሚዩኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ጉዳዮች ቡድን መሪ ብሩክ ጥላሁን ጉዳዩን አስመልክቶ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ማብራሪያ፣ የቆዳ ምርት ውጤቶችን ለማሳደግ ከዚህ በፊት ጥሬ ቆዳና ሌጦን ወደ ውጭ በሚልኩ አካላት ላይ 150 በመቶ ግብር ተጥሎ እንደነበረው ኹሉ፣ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ የቆዳ ምርቶች ላይ ተመሳሳይ የግብር መጠን እንዲጣል እየጠየቅን ነው ብለዋል።

ይህም የሚሆነው በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች እያሉ ከውጭ መግባት የሌለባቸው ምርቶች በመኖራቸው መሆኑን ነው የጠቆሙት።

የምንከተለው ነጻ ገበያ በመሆኑ ወጪና ገቢውን ለማስተካከል ልናደርግ የምንችለው ታክስን መጨመር፣ እንዲሁም የእኛን ምርት መጠንና ጥራት ማሳደግ ነው ያሉት ቡድን መሪው፣ ሙሉ ለሙሉ የአገር ውስጥ ምርትን እንጠቀም ብንል በቂ አይደለም፤ ይህን ለማሳደግ ደግሞ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማብዛት ያስፈልጋል ብለዋል።

የተጀመረው ፕሮጀክት በቁርጠኝነት ተግባራዊ ከተደረገ ሠፊ ገበያ በመኖሩ (30 ሚሊዮን ተማሪዎች አሉ ተብሎ ይታመናል) በዓመት ለተማሪዎች ብቻ 60 ሚሊዮን ጥንድ ጫማዎችንና 30 ሚሊዮን ቦርሳዎችን ማምረት እንደሚቻል ተመላክቷል።

በአገሪቱ የቆዳ ውጤቶችን የሚያመርቱ በኢንዱስትሪ ደረጃ 22 ሲሆኑ፣ አነስተኛና መካከለኛ አምራቾች ደግሞ 16 ናቸው። በጠቅላላው 38 አምራች ኢንዱስትሪዎች ቢኖሩም በሙሉ የማያመርቱ ከመሆናቸውም በላይ፣ በሙሉ አቅማቸው ያመርታሉ ቢባል እንኳን በዓመት 4 ሚሊዮን ጥንድ ጫማዎችን ብቻ እንደሚያመርቱ ነው ብሩክ የገለጹት። በዚህም ሠፊ የገበያ ክፍተት መኖሩን ኃላፊው ጠቁመው፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመቀነስ ለአገር ውስጥ ምርት ትኩረት በመስጠት አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ኢንስቲትዩቱ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሰላሌ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አዲስ አበባው በበኩላቸው፣ የአገራችንን ምርት የመጠቀም ልምዳችን ዝቅተኛ የሆነው ያደጉ አገራት እኛ ላይ በሒደት በገነቡት የተዛባ አመለካከት ነው ሲሉ ገልጸዋል። በዚህም በግዙፍ አምራች ኢንዱስትሪዎቻቸው የተመረቱ ምርቶችን አርማ (ብራንድ) እና ማስታወቂያዎችን በመጠቀም ከእኛ አገር ምርት የእነሱ የተሻለ ነው ብለን እንድናምን አድርገውናል ባይ ናቸው።

አሁን ባለንበት ሁኔታ በቂ ምርት የማምረት አቅም ስለሌለንና ብዙ ምርቶቻችንም በጥራትና በዋጋ ከውጭ የሚገባውን ምርት የሚወዳደሩ ባለመሆናቸው፣ ኹሉንም ምርት በአገር ውስጥ ምርቶች እንተካ ብንል አንችልም ያሉት ተመራማሪው፣ ሆኖም ግን የረዥም ጊዜ ዕቅድ አድርገን ከያዝነው በሒደቱ ብዙ ጥቅም እናገኛለን ነው ያሉት።

የሚጣለው ታክስም በአገር ውስጥና ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍ ያለ የዋጋ ልዩነት የሚፈጥርና የአገር ውስጥ ምርቶችን ተፈላጊነት የሚጨምር መሆን አለበት ያሉ ሲሆን፣ የምንከተለው ነጻ ገበያ ነው በሚል ክልከላውን በታክስ ብቻ ማድረግም በቂ አይደለም የሚል ዕምነት ባለሙያው አላቸው።

የነጻ ገበያ መርኅ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ያለ በመሆኑ፣ መርሁን የሚከተሉ ያደጉ አገራትም ጭምር በሚያስገቡትና በሚያስወጡት ምርት ላይ ገደብ ያስቀምጣሉ ብለዋል። ስለዚህም ቀላሉ መንገድ ታክስ መጨመር፣ እንዲሁም የሚገቡ ምርቶች ላይ ኮታ ማስቀመጥ ቢሆንም፣ የአገር ውስጥ ምርትን መጠን እና የመጠቀም ልምድን በማሳደግ ነው መሻሻል የሚገኘው የሚል ሐሳባቸውን አዲስ ሰንዝረዋል።

የአገር ውስጥ ምርትን መጠቀም የአገር ፍቅር መገለጫ መሆን አለበት የሚል ዕምነት እንዳላቸውም የሚናገሩት አዲስ፣ ሰዎች የአገራቸውን ምርት በመጠቀም አገራቸውን የሚጠቅሙበት ሠፊ ዕድል መኖሩን ማስገንዘብ ያስፈልጋል ነው የሚሉት።
ሥራ አጥነትን ለመቀነስና ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሀብቶችን ለመጠቀምም በአገር ውስጥ ምርት መኩራትና ቅድሚያ መስጠት ተገቢ አማራጭ ነው ብለውታል።

መንግሥት ለዚህ ጉዳይ የሰጠው ትኩረት በጣም የወረደ መሆኑን ለመጠቆምም፣ በአገር ውስጥ በቀላሉ ሊመረቱ የሚችሉ የተለያዩ የቢሮ ወንበሮችና ሌሎች ቁሳቁሶችን በውጭ ምንዛሪ ሲያስገባ መታየቱ አግባብ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።
ታዋቂ ሰዎች እና ፖለቲከኞችም የአገራቸውን ምርት በግንባር ቀደምትነት ሲጠቀሙ በማሳየት፣ የአገር ምርትን የመጠቀም ዝቅተኛ ልማድን መቅረፍ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ተመሳሳይ ርዕስ

10 በአገር ውስጥ ምርታቸው (GDP) ሀብታም የሆኑ 10 የአፍሪካ አገሮች – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

የአገር ውስጥ ዘይት አምራቾች ለአስመጪዎች ቀረጥ መነሳቱ ችግር ሆኖብናል አሉ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በድንጋይ ከሰል ዕጥረት ምክንያት ችግር ውስጥ መግባታቸውን ገለጹ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)


ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here