የጥምቀት በዓል ገጽታ

0
2365

በኢትዮጵያ በደማቅ ሀይማኖታዊ ሥነ ስርዓት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት ውስጥ በየዓመቱ ጥር 11 የሚከበረው የጥምቀት በዓል አንዱ እና ዋነኛው ነው።

በዓሉ መከበር የሚጀምረው ከዋዜማው ዕለት ጀምሮ ሲሆን፣ የበዓሉ ዋዜማም የተለያዩ ስያሜዎች እንዳሉት የሀይማኖቱ ሊቃውንት ያስረዳሉ። በዚህም ዋዜማዋ ኤጲ ፋኒ (በጽርዕ)፣ አስተርዕዮ (በግዕዝ)፣ ገሀድ (በአማርኛ) በመባል እንደሚታወቅ እና መገለጥ ማለት እንደሆነም ጨምረው ይገልጻሉ።

እንዲሁም ከተራ ተብሎ በሚጠራው የጥምቀት ዋዜማ ደማቅ ሀይማኖታዊ ሥነ ስርዓት የሚካሄድ ሲሆን፣ ታቦታቱ ከቤተ መቅደስ ወጥተው ራቅ ብሎ ወደ ተዘጋጀላቸው ባህረ ጥምቀት የሚሄዱበት ክንዋኔ ነው። በዚህም ከቤተ መቅደስ ጀምሮ በካህናት እና በሰንበት ተማሪዎች ያሬዳዊ ዝማሬ፣ እንዲሁም በምዕመናን ታጅበው ወደ ማደሪያቸው ይሸኛሉ።

ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መሄዱን እንደሚያስረዳ ሊቃውንቱ ያስረዳሉ። በዓሉም ከጥንት ጀምሮ የኢየሱስ ክርስቶስን በዮሐንስ መጠመቅ መሠረት አድርጎ በመላ አገሪቱ በኢትዮጵያ ኦርቶክስ ተዋህዶ ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ይከበራል።

ጥምቀት በአገሪቱ በኹሉም ቦታዎች ይከበር እንጂ፣ በተለይ በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ እንዲሁም በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በተለየ ድምቀት የሚከበርባቸው ቦታዎች ናቸው።
የበዓሉ አከባበር ከሀይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር የተለያዩ ባህላዊ ክንዋኔዎች ሲከወኑበትም ይታያል።

አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ ጃን ሜዳ የበዓሉ ዕለት ተገኝታ ባደረገችው ቅኝት በርካታ ሕዝብ ተገኝቶ በዓሉን አክብሯል። ከእነዚህ መካከል በዓሉን ለማክበር በቦታው የተገኙት እና በእድሜ ሰባዎቹ አጋማሽ የሚሆኑት ግርማ ቶሎሳ ጋር አጠር ያለ ቆይታን አድርጋለች። ግርማ አስተያየታቸውን ሲያካፍሉ ንጉሡ ከመኳንንት እና መሳፍንት ጋር ሆነው የጥምቀት በዓል በቦታው መከበር ሲጀምርም ከኃይማኖታዊ ክንዋኔው በላይ ባህላዊ ክዋኔዎች ቀልባቸውን ይስበው እንደነበር መለስ ብለው አስታውሰዋል። በዚህም ትግሬው፣ ጉራጌው፣ ወሎዬው፣ ጎንደሬው፣ ኦሮሞው ሌሎችም በየራሳቸው ባህልና ወግ የተለያዩ ጭፈራዎችን እና ዘፈኖችን ይጫወቱ እንደነበር ነው ያወሱት።

ግርማ አክለውም ከጃን ሜዳ ውጭ በላስታ ላሊበላ እና በሌሎች የአገሪቱ ቦታዎች በዓሉን በድምቀት ማክበራቸውን ጠቅሰዋል። በዚህ ጊዜም አንዱ ቡድን እየጨፈረ ሲያልፍ እና እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ሲል ጸብ ይፈጠር እንደነበርና ጸቡ ግን ወደ ቁርሾ የማያመራ እንደነበር ይገልጻሉ።

ጃን ሜዳ ማለት ንጉሡ እግዚአብሔርን የሚያከብሩበት የንጉሡ ሜዳ ማለት እንደሆነ ከታሪክ አዋቂዎች አንደበት ሲነገር ይደመጣል። ጃን ሜዳም በጫካ የተከበበ እና በሳር የተሞላ ከመሆኑ ባለፈ፣ ሳሩ ለክቡር ዘበኛ ፈረሶች ይውል እንደነበርና ከ1959 በፊት በጣውላ ታጥሮ እንደሚኖር በኋላም ክቡር ዘበኛ በግንብ እንዳሳጠረው ይነገራል።

በዚህ ሜዳም ወጣቶች የተለያዩ ስፖርታዊና ባህላዊ ጨዋታዎችን ይጫወቱ፣ ክቡር ዘበኛ ሥልጠናዎችን ያደርግበት ነበር። በስፍራው ስፖርታዊ ልምምድ ካደረጉበት ታዋቂ ሰዎች መካከልም አበበ ቢቂላ እና ማሞ ወልዴን መጥቀስ እንደሚቻል ይነገራል። በኋላም ንጉሡ ቀዳማዊ ግርማዊ ኃይለሥላሴ ከመኳንንቶቻቸውና መሳፍንቶቻቸው ጋር በመሆን ጃን ሜዳ ተገኝተው የጥምቀት በዓልን ያከብሩ እንደነበር፤ የገና ጨዋታ ለሚጫወቱ ወጣቶችም ጥንጓን መትተው ጨዋታውን ያስጀምሩላቸው እንደነበር ታሪክ ያወሳል።

ሌላኛው ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ እና ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ግለሰብ፣ በቅርቡ ከውጭ አገር የመጡ ሲሆኑ ጥምቀትን ከሠላሳ ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ ያከበሩት ዘንድሮ እንደሆነ ነግረዉናል።
ግለሰቡ በ1960ዎቹ ገደማ ጥምቀት በጃን ሜዳ ሲከበር እንዲህ አልነበረም ይላሉ። በዚያን ጊዜ የነበሩ ባህላዊ ክንዋኔዎች አሁን የጠፉትም በቀሳውስቱ ጫና ነው ብለውም ያምናሉ።

ሲጀመር የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው በሀይማኖታዊ ስነስርዓቱ ብቻ ሳይሆን የተለያየ ቋንቋና ባህል ያላቸው የዕምነቱ ተከታዮች በዕለቱ ያሳዩት በነበረው ባህላዊ ስርዓት ነው ያሉት ግለሰቡ፣ ‹‹ያ ነገር አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ጠፍቶ ሳየው ከመደንገጤም በላይ በዓሉ ከዓለም ቅርስ መዝገብ ውስጥ እንዳይፋቅም እሰጋለሁ።›› ብለዋል።

በዚያን በ1960ዎቹ ወቅትም የሀርሞኒካ ጭፈራ ይጨፈር እንደነበር እና ጭፈራውም ስህተት እንዳልሆነ ገልጸዋል። ሀርሞኒካ ማለት እንኳን ለዘንድሮው በዓል በሰላም አደረሰን የሚለውን ለመግለጽ ወጣቶች ያደርጉት የነበረ ጭፈራ እንጂ ሌላ አይደለም ነው የሚሉት። በዚህም አሁን ላይ ቀሳውስቱም ይሁኑ ሌሎች የሀይማኖቱ አስተማሪዎች በሚያደርጉት ጫና በዓሉ ሀይማኖታዊ ይዘት ብቻ እንዲኖረው አድርገዉታል ባይ ናቸው።

ወጣት ዳዊት ገበያው በበኩሉ የጥምቀት በዓልን በየዓመቱ በጉጉት እንደሚጠብቀው ገልጾ፣ ባለፈው ዓመት በጃን ሜዳ ሲያከብር የሀርሞኒካ ዳንስ አጃቢ እንደነበርና አሁን ላይ ያን ሲያስብ እንደሚቆጭ ተናግሯል።

‹‹ወንዶች እና ሴቶችን በነጠላ እንሸፍናቸዋለን። ከዚያም ውስጥ ሆነው ይጨፍራሉ። ሌላ የተለየ ነገር ምን እንደሚያደርጉም አናውቅም። የደከሙት ሲወጡ የሚተኩ ሌሎች ሴቶችም ነበሩ። ይህም ከበዓሉ ጋር የሚሄድ ባለመሆኑ ከዚህ በኋላ ሀርሞኒካ በደረሰበት አልደርስም።›› ሲል ይናገራል።

የጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማም እንዲሁ በአፄ ፋሲል መዋኛ ገንዳ በድምቀት ከሚከበርባቸው ቦታዎች አንዱ ነው።

‹‹በገጠሪቱ ኢትዮጵያም እንዲሁ ጥምቀት እጅግ በሚያስደስት መልኩ ነው የሚከበረው።›› ሲሉ ሐሳባቸውን ያጋሩት ደግሞ ሰይፉ ዘለላም ናቸው። እርሳቸው ለበርካታ ጊዜያት በገጠር በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ ጥምቀትን እንዳከበሩ ገልጸው፣ በዚያ አካባቢ የከተራ ዕለት ታቦቱ ከቤተ ክርስቲያን ወጥቶ ዳገትና ቁልቁለት በበዛበት መንገድ ወደ ወንዝ እንደሚያመራ ገልጸዋል። ወንዝ ከደረሰ በኋላም ቀድሞ በወጣቶች እና በአገር ሽማግሌዎች በተተከለው የታቦቱ ማረፊያ ድንኳን ውስጥ እንደሚገባ እና ሌሊቱንም ካህናት እና ዲያቆናት ልዩ ልዩ ያሬዳዊ ዜማዎችን ሲያዜሙ እንደሚያድሩ አስረድተዋል።

የአካባቢው ምዕመናን ድግስ ደግሰው ዝክር የሚያደርጉ ሲሆን፣ ማህሌት፣ ኪዳን እና ቅዳሴም በሌሊቱ መርሀግብር ይከወናሉ ነው ያሉት። በነጋ ጊዜም ከአራቱ ወንጌላውያን ስለ ክርስቶስ መጠመቅ ምንባብ ተነቦ ካለቀ በኋላ፣ ጥምቀተ ባህሩ ተባርኮ ካህናቱ ማጥመቅ ይጀምራሉ ሲሉ ይገልጻሉ።

ከቆይታ በኋላም ታቦቱ ወጥቶ ድንኳን እስከሚነቀል ድረስ ወጣቶች የገና ጨዋታ ይጫወታሉ፣ የተለያዩ ሽሩባዎችን የተሠሩ፣ ጥፍራቸውን እንሶስላ የሞቁ፣ አዳዲስ ልብስ የለበሱ ልጃገረዶች ዘፈንና ጭፈራ ያካሂዳሉ ሲሉ በገጠር ያለውን የጥምቀት በዓል አከባበር ያስረዳሉ። በዚህም ከሚጨፍሩ ልጃገረዶች መካከል አንዱ ጉብል ዐይቶ የወደዳትን ሎሚ ይወረውርባታል አልያም አብራው እንድትጨፍር ይጋብዛታል ነው የሚሉት። በዚህ መንገድ ተዋውቀው ትዳር የመሠረቱ ብዙ ወጣቶች መኖራቸውንም አመላክተዋል።

በዚህ ዘመን በዚህ መልኩ ተዋውቆ መጋባት መቀነሱን እና አሁን ላይ የሚደረጉ በወጣቶች ዘንድ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ አለባበሶችም ይሁን የሚደረጉ አንዳንድ ክንውኖች ከድሮው የተለዩ ከመሆናቸውም ሌላ ከእሴታችን ያፈነገጡ ናቸው ሲሉም ይናገራሉ።

ስለሆነም የጥምቀት ታቦት በሚወጣበት ወቅት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚደረጉ ዝማሬ የሚመስሉ ባህላዊ ዘፈኖች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ያላቸው ናቸው የሚሉት ሰይፉ፣ በዚህ ዘመን በተለይ በከተሞች የሚታየው ግን የእኛ ያልሆነና ምንም ዓይነት መሰረት የሌለው ነው ብለውታል።

በድሮው ዘመን አንድ ወንድ አንዲት የሚወዳትን ሴት እንደሚፈልጋት ለማሳወቅ ጥምቀት እስከሚመጣ ዓመት ሙሉ ይጠብቅ እንደነበር ይነገራል። ከቤት ስለማትወጣ ሌላ ቦታ የማያገኛት ከመሆኑም ሌላ፣ ቢያገኛት እንኳን እንደሚፈልጋት መናገር አይችልም ነበር። በዚህም እንደ ጥምቀት ያሉ የአደባባይ በዓላትን መጠበቅ ይኖርበታል።

አሁን ላይ ደግሞ እንደዚያ ዓይነቱ ድርጊት የተገላቢጦሽ መሆኑን የሚናገሩ አሉ። ጥምቀት ላይ ሎሚ ቢወረወርባቸው ሴቶች ስቆ ከማለፍ ውጭ ለልጁ ፊት እንደማይሰጡት የሚገልጹ ሴቶች በርካታ ናቸው። በሌላ መልኩ ደግሞ በድሮው ጊዜ ሎሚ የሚወረወርባት ሴት አለባበሷ ስርዓቱን የጠበቀ ሆኖ፣ በጨዋነቷም የተመሰከረላት ልጃገረድ መሆን አለባት ይላሉ። በዚህ አካሄድ ቆንጆ ቢሆኑም የጥምቀት ሎሚ የማያርፍባቸው ብዙ ሴቶች አሉ እንደማለት ነው።

በዚህ ጉዳይ ደራሲ መላኩ አላምራው ‹ነፍጠኛ ስንኞች› በተሰኘ የግጥም ስብስብ መጽሐፉ (ገጽ 54) በጥምቀት በዓል ወቅት ድሮ የነበረውን እና አሁን የሚስተዋለውን በማነጻጸር በሚከተሉት ስንኞች ቋጥሮ አስቀምጦታል፤
ባህልን አክብሮ፣ ከእንስት ርቆ፣
በዓመት አንድ ጊዜ ጥምቀትን ጠብቆ፣
ከኮረዳ መሀል ከውብም ውብ መርጦ፣
ልቡ እንደወደዳት በውል አረጋግጦ፣
ሎሚ በመወርወር የሴት ደረት መትቶ፣
ውቢቷ ኮረዳም ደረቷ ሲመታ፣ ልቧ ተደስቶ፣
‘ሚኖርበት ዘመን፣
ሰው ከሰው ተጫጭቶ፣
ሰው ከሰው ተጋብቶ፣
ድሮ ቀረ ድሮ…
ሰው ከውጭ ተምሮ ባህል ተቀይሮ፣
ሎሚም ዋጋው ንሮ አልሆነም ዘንድሮ …!
ያሁኑ ጎረምሳ፣
ኮረዳ ለመቅረብ፣ ጥምቀት አይጠብቀም፣
ያው ዓመቱን ሙሉ ከሴት ጥግ አይርቅም።
የኮረዳም ደረት፣
ለጥምቀቱ ሎሚ አሻፈረኝ አለ፣
ቀድሞ ተገላልጦ አደባባይ ዋለ።

በጥቅሉ የጥምቀት በዓል ከሀይማኖታዊ ፋይዳው በተጓዳኝ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳውም እጅግ የጎላ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ነው።

በዓለም የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኒስኮ) የተመዘገበ የማይዳሰስ ቅርስ በመሆኑም በየዓመቱ በርካታ የውጪ አገር ቱሪስቶችን ወደ አገር ውስጥ የሚስብ ነው።

በማህበራዊ ዘርፍም እንደሚስተዋለው ወጣቶች በጋራ ሆነው ከከተራ በፊት ጀምሮ አደባባዮችን ሲያስጌጡ እና መንግዶችን ሲያስውቡ ይታያል። የበዓሉ ዕለትም በርካቶች ተሰባስበው በጋራ የሚያከብሩት በመሆኑ አንድነት እና ፍቅርን የሚያጠናክር ታላቅ በዓል መሆኑ ተደጋግሞ ይገለጻል።

የኢየሱስ ክርስቶስን መጠመቅ መሠረት በማድረግ የጥምቀት በዓልን ከኢትዮጵያ በተጨማሪ፣ ኤርትራ፣ ሩስያ፣ ጆርዳን እና ዩክሬንም በዓሉን በድምቀት ከሚያከብሩ አገራት ውስጥ ይገኙበታል።

ተመሳሳይ ርዕስ

በጎንደር ለሚከበረው የጥምቀት በዓል 500 ሺሕ እንግዶች ይጠበቃሉ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

የጥምቀት በዓል እና ሐርሞኒካ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

የጥምቀት በዓል ትዝታዬ በሸዋ ሮቢት እስር ቤት – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

በዓልን በሐዘን ጥላ ሥር – Addis Maleda


ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here