ዘራፊው ያለየበት ዝርፊያ

0
584

ሠሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል፣ ንብረት ተዘረፈ የሚልና ዘራፊው ማንነት ላይ ያነጣጠረ በዘመቻ መልክ የተካሔደ የቃላት ምልልስ ዋናው ነበር። ወሎ ድጋሚ ተዘረፈች ከሚሉ አንስተው፣ የደሴ ከተማ ባለሀብቶች ንብረት ተዘርፎ ተወሰደ የሚሉ ንግርቶች የብዙዎችን ትኩረት ወስደው ነበር።

ከተማውን ወሮ የነበረው ታጣቂ የህወሓት ቡድን በገፍ ጭኖ የወሠደው ንብረት ይህን ያህል ትኩረት እንዳላገኘ አስተያየታቸውን የሠነዘሩ ሰዎች፣ ከታጣቂዎቹ የተረፈውን ዘረፈ የተባለው አካል በጅምላ መፈረጁ እንዳስገረማቸው ሐሳባቸውን ሲያስደምጡ ተሰምቷል። የወሎን ሕዝብ ከመከራ ሊታደጉ ረጅም ርቀት አቋርጠው መጥተው ሕይወታቸውን የገበሩ ሰዎች፣ በሥራው አምርረው የሚጠሉት ጠላታቸው ቡድን ሲሠራው በነበረው ተግባር ላይ ይሳተፋሉ ብሎ መገመት እንደሚከብዳቸው የተናገሩ አሉ።

ንብረት ተዘረፈ የሚሉትም ሆኑ ዘራፊዎቹ ተያዙ እያሉ ጉዳዩን ሲያራግቡ የነበሩት ስማቸውን የጠቀሷቸው አካላት ያን ተግባር ስለመፈጸማቸው ምንም ማስረጃ እንደሌላቸውና፣ መካነ ሠላም ላይ ተያዘ የተባለ ነገር እንደሌለም እየጠቀሱ ሲሞግቷቸው ነበር። የወሎንና የጎጃምን ሕዝብ በማቃቃር የወራሪውን አካል አጀንዳ ለማስፈጽም የፈለጉ አካላት ናቸው ተግባሩ እንዲካሄድና ወሬው እንዲራገብ ያደረጉት በሚል አስተያየታቸውንም የሠነዘሩ አሉ።

“በኹለት የፋኖ አባላት በሚመራ አካል ነው ዝርፊያው የተፈጸመው” ብለው የሚከሱ አካላት ይህን ያሉበትንም ማስረጃ ማቅረብ ስላለመቻላቸው በእርግጠኝነት የተናገሩም ነበሩ። የትም ዓለም ላይ ያለ ዘራፊ፣ “የእነገሌ ታዛዥ ነን” እያለ እንደማይዘርፍና፣ እንደዚህ ከተባለም ሌላ ሥምን የማጠልሸት ዓላማ ያላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ መላምታቸውን ያስቀመጡ አሉ። ዝርፊያ መካሄዱ ባይካድም፣ ማን አደረገው የሚለው ነው በዚህ በጦርነትና አንድነት በሚፈለግበት ወቅት አነጋጋሪ የነበረው።

በመንግሥት አሸባሪ የተባለው ህወሓት ይህ ተፈጸመ ከመባሉና ከተማዋን ከመቆጣጠሩ አስቀድሞ፣ “ፋኖ የተባሉት ዘረፋ ላይ ይሠማራሉ” በሚል የፕሮፓጋዳ ሥራ ላይ ተጠምዶ እንደነበር በመጥቀስ፣ በአካባቢው ክፉ ወቅት ሸሽተው የነበሩት ሥማቸውን ለማደስ የተዋደቁትን እየከሰሱ ነው በማለት ዕይታቸውን ያስተጋቡም ነበሩ። ዘረፉ የተባሉት አካላትን ከሕዝብ ልቦና ለማስወጣት ከዓመታት በፊት በተመሳሳይ ጎንደር ላይ በዝርፊያ ተሠማርተዋል ተብሎ እንደነበረ ያስታወሱ ሰዎች፣ ዝርፊያውን ሲፈጽሙ ከነበሩ መካከል፣ “ፋኖ ነን” እያሉ በስማቸው ያልተገባ ተግባር ሲፈጽሙ የነበሩትን በደረሳቸው ጥቆማ መሠረት ራሳቸው ይዘዋቸው ለመንግሥት አካላት ማቅረባቸውን ያስታውሳሉ።

እንዲህ ዓይነት ወሬም ሆነ ተግባር የመንግሥትንም ሆነ የሕዝብን ትኩረት ለማስቀየስ የሚያገለግል እንደመሆኑ፣ የመንግሥት አካላት ዝም ማለታቸውን በመጥቀስ ለምን ብለው የሞገቱም አሉ። አዲስ አበባ ጭምር መኪና መዝረፍን የመሳሰለ ከባባድ ወንጀል በየቀኑ እየተፈጸመ፣ በጦር ቀጠና አካባቢ ግንባር ያሉ ዘማቾች ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ ለማንም አይጠቅምም በማለት ሒደቱን የተቹት ብዙ ናቸው።

ያም ሆነ ይህ፣ በተደራጀ መንገድ የተፈጸመም ይሁን በግለሰብ ደረጃ ዝርፊያ መወገዝ ያለበት ነው። የተለመደው የሕግ አካል አጣርቶ ውሳኔው እስኪያሳወቅ ድረስ የሥም ማጥፊያና ድጋፍ ማስጣያ መንገድ ሊሆን አይገባውም። ጦርነቱ የወንጀል መሸፈኛ እንደማይሆነው ኹሉ፣ በሒደቱ ብዙ ወንጀለኞችም ከዕስር ተፈተው ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸው ሊታወቅ ይገባል። የጋራ ዓላማን ለመሸርሸር ለሚደረጉ ዕኩይ ተግባራት ሕብረተሰቡ ቦታ ባለመስጠት የሴራ መጠቀሚያ ላለመሆን ሊነቃ እንደሚገባ በርካቶች ምክራቸውንም ለግሠዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here